ዓርብ 14 ኖቬምበር 2025

በልማት ተነሺዎቹ ዓይን የኮሪደር ልማቱ ያበለፅጋል ወይስ ያደኸያል?

“እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ፣ እህሌ የሚደርሰው ለፍልሰታ”

(በፍቃዱ ኃይሉ) 


For English, click here.


የኮሪደር ልማቱ በተለይ የመሐል አዲስ አበባን ገጽታ እስከወዲያኛው እየቀየረው ነው። ለአቅመ ማስተዋል ከደረስኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ አዲስ አበባ በግንባታ ላይ ነች፤ ሆኖም ከ2016 ጀምሮ እያስተናገደች ያለውን ያክል የነባር ሰፈሮች መፍረስ ግን አይቼ አላውቅም። የቀድሞዎቹ ፒያሳ እና ካዛንቺስ ተሰናብተዋል፤ አዲሶቹ ገና አልተወለዱም። በአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ይኖሩ የነበሩት ብዙ ሰፈሮች ፈርሰዋል፤ በምትካቸው ማራኪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው። ያለ ጥርጥር መሐል አዲስ አበባ እያማረባት ነው፤ ቀድሞ መሐል ከተማ እናየው የነበረው ግርግር እና ማኅበራዊ ቫይብ ግን ከነዋሪዎቹ ጋር አብሮ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ፈልሷል። የመሐል ከተማው የመንገድ ጥርጊያዎቹ፣ የእግረኛ መንሸራሸሪያዎቹ፣ መናፈሻ ፓርኮቹ፣ የመኪና ማቆሚያዎቹ፣ ወዘተ አስፈላጊም ውብም ናቸው ብዬ አምናለሁ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰፈሮች ውስጥ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት የኖሩ ቤተሰቦች አሁን ወደ ከተማው ዳርቻ ተገፍተው ለመናፈሻዎቹ ቦታ ለቀዋል። አሁን በፒያሳ እና ካዛንቺስ ትልልቅና ዘመናዊ አፓርታማዎች እየተገነቡ ነው። ይህ ክስተት፣ ድሆችን ከመሐል ከተማ ገፍቶ አስወጥቶ፣ በምትካቸው ዘመናዊ አፓርትመንቶችን መግዛት የሚችሉ ባለፀጋዎችን የሚስብ ("class replacement") እየመሰለ ነው። 


በዚህ መነሻ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ከፈለግኩ የቆየሁ ቢሆንም ስፈራ ስቸር ዘግይቻለሁ። ነገር ግን ቢያንስ መሠረታዊ፣ ሕጋዊና ሞራላዊ ጥያቄዎች የማንሳት መብታችን ይጠበቃል በሚል ተስፋ ከብዙ በጥቂቱ ለመጻፍ ተደፋፍሬያለሁ። ዓላማዬ የልማት ሥራውን ማጥላላት ወይም ማወደስ አይደለም። ይልቁንም ይህ የአዲስ አበባን መልክና ገጽታ፣ የነዋሪዎቹን ባሕልና አሰፋፈር ለዘለቄታው እየቀየረ ያለ እና ምናልባትም በከተማዪቱ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጦሰኛ (consequential) ኹነት ለልማቱ ዋጋ በከፈሉት (የልማት ተነሺዎች) አንደበት ምን ዓይነት ዋጋ እንዳለው ለመጠየቅ ነው።


በግሌ ተወልጄ ያደግኩበት እና የቤተሰቦቼ እና የአብሮ አደጎቼ ቤተሰቦች መንደር በወንዝ ልማት ፕሮጀክት ሳቢያ ፈርሶብኛል፤ በምትኩ መናፈሻ ፓርክ እየተገነባ ነው። በጽሑፌ የእኛን ሰፈር ነዋሪዎች ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ሌሎችንም ምሳሌዎች በማጣቀስ “በሒደቱ የልማት ተነሺዎቹ ሕይወት ይሻሻላል (ይበለፅጋል) ወይስ ይከፋል (ይደኸያሉ)?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ። 


የኮሪደር ልማቱ እና የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ (macroeconomic implication) ምን እንደሚሆን፣ ከባለሙያዎች እንሰማለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለጊዜው ግን የኔ ዳሰሳ የልማት ተነሺዎቹን ሕይወት የሚመለከት ነው። 


መግባቢያ 


በዚህ ጽሑፍ የምዳስሰው የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የሚባሉትን በተመለከተ ነው፤ የጫካ ፕሮጀክት የመሳሰሉ ግዙፍ እና ምሥጢራዊነት የሚበዛበቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ለጊዜው በዚህ ዳሰሳ አላካተትኳቸውም። በመርሕ ደረጃ በጽሑፌ የምዳስሳቸው ሁለቱ ፕሮጅከቶች አስፈላጊነት ላይ ብዙ ጥያቄ የለኝም፤ ያሉኝም ጥያቄዎች የዚህ መጣጥፍ ዓላማ አይደሉም።


ልማት ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊም ነው። ለአንድ የመሠረተ ልማት ከአንድ አባቢ የተነሱ ሰዎች፣ በሌላ አካባቢ ሲሰፍሩ ፍላጎቶቻቸው ካልተሟሉላቸው ልማቱ ጎድሎ ይሆናል። ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ መልስ የማፈላልግለት ጥያቄ ፕሮጀክቶቹ፣ በተለይ ለልማት ተነሺ ከሆኑት ነዋሪዎቹ የቀደመ እና አሁናዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንፃር “ወደ ብልፅግና ይመራሉ” ወይስ በተቃራኒው “ሊያደኸዩ ይችላሉ?” የሚል ነው። ጽሑፉን ለመጻፍ የግል ምስክርነቴን፣ የተወሰኑ የልማት ተነሺ ሰዎች ምስክርነት፣ የዜና ምንጮች፣ እና በጉዳዩ ላይ የምርምር ሥራ እየሠሩ ያሉ ሰዎች አስተያየት በግብዓትነት ተጠቅሜያለሁ። ሐተታዬ በአዲስ አበባ ስላሉት ሁለቱ ፕሮጀክቶች (የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት) እንጂ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉትን አይመለከትም። በአዲስ አበባ ውስጥም የልማት ተነሺ ንግድ ቤቶችን ሁኔታ አልዳሰስኩም። (የሆነ ሆኖ አንባቢዎች እንዲረዱልኝ የምፈልገው ይህ ጽሑፍ በምንም ዓይነት የክስተቱን ሙሉ ገጽታ ማሳየት እንደማይችል ነው።)


ጽሑፉን የቀድሞዎቹ ሠፈሮች አመሠራረት እና ዕድገትን በመተረክ እጀምርና፣ የአፈራረሱ ሒደት፣ ለተነሺ ነዋሪዎች የተሰጠውን ካሣ እና ምትክ በመዘርዘር፣ ሒደቱ በልማት ተነሺዎቹ ኢኮኖሚያዊ ዕጣ ፈንታ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ በማሳየት ወደ መደምደሚያው እሸጋገራለሁ። 

የቀድሞ ሰፈሮች እንዴት ለሙ? 


እንደመነሻ ይሆነን ዘንድ ለቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሲባል የፈረሰውን የእኛን ሰፈር ዕድገት ታሪክ ላቅርብ። ወላጆቻችን ኑሯቸውን በእኛ ሰፈር የጀመሩት የዛሬ ሃምሳ መት ገደማ በነበረው አሠራር መሠረት፣ በወቅቱ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ምሪት በተሰጣቸው መሬት ላይ ደሳሳ ጎጆዎችን በመቀለስ ነው። እነዚህ ደሳሳ ቤቶች በሒደት እና በልጆቻቸው እገዛ ወደ ትልልቅ ቤቶችነት አድገዋል፤ ታድሰዋል፤ ፈርሰው ተሠርተዋል። የወላጆቻችንን ገቢ ለመደገፍና ለማሳደግ በየጊቢው ውስጥ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶች ተሠርተው ተከራይተዋል። ስለሆነም፣ እኔና የሰፈሬ ልጆች ልጅነታችንን ያሳለፍንበት ሰፈር፣ አሁን በፈረሰበት ወቅት ከነበረው ይዘት ጋር በእጅጉ ይለያያል። እነዚህ ቤተሰቦች ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ያለመታከት በመሥራት የአካባቢውን እሴት ጨምረውታል። የመብራትና የውሃ መሥመሮች የተዘረጉት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የተነጠፉት፣ እና የሰፈሩ መሠረተ ልማት ሁሉ የተገነባው በነዋሪዎቹ መዋጮ እና የዐሥርት ዓመታት ጥረት ነው። 


እነዚህ ሰፈሮች ከመሠረተ ልማታቸው፣ ሰፈራነታቸው ይቀድማል። የድንጋይ መንገድ ሲነጠፍ፣ የውሃ እና የመብራት መሥመር ሲዘረጋ ነዋሪዎቹ በመዋጮ፣ ወይ ሙሉውን፣ ወይ ከፊሉን ወጪ ይሸፍናሉ። ስለዚህ የቤታቸው ጣራ እና ግድግዳ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ መንገዱ ላይ፣ የውሃና ኤሌክትሪክ መሥመሩ ላይ፣ የአካባቢው ሰላም እና ማኅበራዊ ድባብ ላይ ሳይቀር መዋዕለ ንዋይ እና ጊዜያቸውን አፍስሰዋል።


ወላጆቻችን ሲያረጁ፣ ልጆቻቸው ወላጆቻቸው ጊቢ ጎጆ ቀልሰው፣ ትዳር መሥርተው፣ የልጅ ልጆች አይተዋል። ብዙ እኩዮቼ፣ እትብታቸው በተቀበረበት ሰፈራችን የልጆቻቸው እትብት ተቀብሯል። ይህ የእኛ ሰፈር የልማት ታሪክ የብዙ ሰፈሮች ታሪክ ነው። ነዋሪዎቹ ሰፈሮቹ አሁን ያላቸውን ዋጋ እንዲኖራቸው ለብዙ ዐሥርት ዓመታት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ከዋጋውም በላይ ከሰፈሩ ጋር ስሜታዊ ትስስር አላቸው። የሕይወት ትዝታቸው በሙሉ ሰፈሩ ሲፈርስ አብሮ ፈርሷል። መተዳደሪያ ገቢያቸው ከሰፈሩ ጋር የተዋሃደውም ብዙዎች ናቸው። ሰፈሮቹ ሲፈርሱ የነዋሪዎቹ መተዳደሪያቸው፣ ትዝታቸው፣ ማኅበረሰባቸው (ክፉ ቀንን በመተባበር የሚያሳልፉበት ዕድር እና ዕቁባቸው) በሙሉ አብረው ፈርሰዋል።  ምትክ ቦታ የተሰጣቸው ነዋሪዎች አዲስ ሰፈር ውስጥ አዲስ ቤቶች ገንብተው፣ አዳስ ማኅበረሰብ አኑረው፣ የድሮው ደረጃ ለመድረስ ከዚህ በፊት ወላጆቻቸው ያለፉበትን ድካም እና ዋጋ እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል። 


የሁሉም የአዲስ አበባ ሰፈሮች ውልደት ከእኛ ሰፈር ጋር ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፤ ዕድገታቸው ግን ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ አንድ ዓይነት ነው። አዲስ አበባ በተቆረቆረች ማግስት የመኳንንቱና የመሳፍንቱን መኖሪያ ቤቶች ከብበው የተፈጠሩት ሰፈሮች ዛሬም ድረስ በዚያው ሥም ይጠራሉ፤ ራስ ካሣ ሰፈር፣ ራስ ሥዩም፣ ራስ ሙሉጌታ ሰፈሮች በዚህ መንገድ ነበር የተቆረቆሩት። ፒያሳ፣ ካዛንቺስ እና መርካቶ የመሳሰሉት ሰፈሮች ደግሞ የጣሊያን የአምስት ዓመት ወረራ የወለዳቸው ወይም የቀየራቸው ሰፈራዎች ናቸው። እነ ጌጃ ሰፈር እና ጊሚራ ሰፈር ደግሞ በሰፈሮቹ ውስጥ መጀመሪያ በሰፈሩት ጎሳዎች ሥም የተሰየሙ ሰፈሮች ናቸው። በጥንታዊ የአካባቢው ሥም፣ ወይም በአካባቢው በተተከሉ ቤተ ክርስትያን እና መስኪድ ሥም፣ በአካባቢው በሚያልፉ ወይም በሚያዞሩ አውቶቡሶች ሥም፣ ለሰፈሩ ዝነኛ በነበሩ ሕንፃዎች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ኤምባሲዎች፣ የውጭ አገሮች፣ ሬስቶራንቶች፣ ቡና ቤቶች፣ የሸቀጥ ሱቆች ሥም የተሰየሙ ሰፈሮችም አሉ። ምንም እንኳን እነዚህ ሰፈሮች በጥቂት ነዋሪዎች እና በደቃቃ ጎጆዎች ቢቆረቆሩም በነዋሪዎቻቸው ጥሪት እና በማያቋርጠው የአዳዲስ ነዋሪዎች ፍሰት አድገው ተመንድገዋል። አዲስ አበባ ያለመንደሮቿ እና ነዋሪ ማኅበረሰቦቿ ምንም ናት።


ሁሉም የፈረሱት ቤቶች የግል ይዞታ አልነበሩም። አንዳንዶቹ የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶች ናቸው። እነዚህኞቹ በተለይ ደርግ ትርፍ የከተማ ቤቶች እንዲወረሱ ባወጀበት ጊዜ ወደ መንግሥት ንብረትነት የተለወጡ ናቸው። የቀበሌ እና የኪቤአድ ቤቶች በአንድ ጊቢ ብዙ ነዋሪዎች አሏቸው። ብዙዎቹ ደባሎችም (roommate) አሏቸው። ፒያሳ እና ካዛንቺስ የነበሩት እነዚህ ቤቶች በተለይ በብዛት ተዳብሎ መኖር የኢኮኖሚ ጫናን መቋቋሚያ መንገዳቸው ነበር። በተጨማሪም፣ መንደሮቹ ውስጥ በርካታ ኢመደበኛ የሥራ ዕድሎች ነበሩ። ለሰፈሩ ሰው ልብስ አጥበው፣ እንጀራ ጋግረው፣ ሕፃናት ጠብቀው፣ ወይም ትምህርት ቤት አመላልሰው፣ ፀጉር ሰርተው፣ ተላልከው፣ ደልለው፣ ጉዳይ አስፈፅመው እንጀራቸውን የሚበሉ ብዙ ነበሩ።


ስለሰፈሮች መልማት ሳወሳ ሁሉም ሰፈሮች የነበሩበት ሁኔታ ጥሩ ነበር እያልኩ አይደለም። አንዳንዶች በበይነትውልዳዊ (intergenerational) ድህነት ሳቢያ ትፍግፍግ ያሉ ጉሮኖዎች ነበሩ። ብዙዎቹ እርስበርስ ተለጣጥፈው የቆሙ ቤቶች ናቸው። ከነጠላ እግረኛ በቀር መተላለፊያ መንገድ የሌላቸውም ብዙ ነበሩ። መፀዳጃ ቤት በጋራ የሚጠቀሙ፣ መታጠቢያ ክፍል የሌላችው፣ ከነዋሪዎቹ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቦታ (space) የሌላቸውና መኪና ማስገባት የሚችል የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንኳን የሌላቸው ነበሩ። በወንዞች ዳርቻ ይኖሩ የነበሩትም አንዳንዶቹ እጅግ ለአደጋ በሚያጋልጥ አሰፋፈር ገደል ላይ ተንጠልጥለው ይኖሩ የነበሩ ናቸው። ለጎርፍ እና መደርመስ አደጋ ተጋላጭ የነበሩም ሲኖሩበት፣ ለወንዞቹ ብክለትም የነዚህ መንደሮች ቆሻሻ እና ፍሳሽ ዋነኛ ተጠያቂዎች ነበሩ። 


አሁን በከተማዋ የቀድሞ ሰፍሮች ቅንጡ አፓርትመንቶች፣ የገበያ ማዕከሎች፣ እና መናፈሻ ፓርኮች እየተገነቡ ነው። በአዲስ አበባ የሚፈስ ወንዝ ዳርቻ ወደ መናፈሻነት እየተቀየረ ያልሆነው አካባቢ በጣም ጥቂት ነው፤ የቀረውም ጊዜውን እየጠበቀ ይመስላል። መጋቢት 11፣ 2017 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ በአዲስ አበባ ብቻ ለልማት ሥራው ከቀያቸው ለተነቀሉ ሰዎችም 17 ቢሊዮን ብር ካሣ መከፈሉን ተናግረዋል። 


የኮሪደር ልማቱን እና የወንዝ ዳርቻዎች ልማቱን የሚመለከት ዕቅድ ይኖር እንደሆን ለማግኘት ብዙ ጥሪያለሁ። ሆኖም፣ ለሕዝብ ክፍት የሆነ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አልቻልኩም። ከተመራማሪዎች እንደተነገረኝ፣ የወንዝ ዳርቻዎቹን የማልማቱ ዕቅድ ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጥናቶች የተደረጉበት እንደነበረ እና የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ሲቋቋም የጥናት ሰነዶቹ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ተዛውረው፣ ዲዛይናቸው እና የሽፋን መጠናቸው በየጊዜው እየተቀያየረ ወደ ተግባር ገብተዋል። የመስቀል አደባባዩ ግንባታ እና የቤተ መንግሥቱም ወደ ሙዚየምነት መቀየር በኢሕአዴግ ጊዜ የታሰበ ነው። የመሐል ከተማ መንደሮች የሚፈርሱበት እና የሚተኩበት ዕቅድ ግን ከየት እንደመነጨ ማወቅ አልቻልኩም።


የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ


የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎቹን በጣም ይኮራባቸዋል። በኢሕአዴግ ጊዜ የመንግሥት ቴሌቪዥኖች የግብርና ውጤቶችን ማሳየት እንደ አየር ሰዓት መሙያ ያውሉት ነበር። አሁን ደግሞ እነዚህ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እና መናፈሻዎች በግብርና ውጤቶች ቦታ የቴሌቪዥን አየር ሰዓቶችን አጨናንቀዋል። የመጪው ምርጫ አስኳል እና የዚህ መንግሥት “የችሎታው ማሳያ” እንደሚያደርጋቸውም መገመት አይቸግርም።


ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከንቲባዋ በየጊዜው የሥራዎቹን አፈፃፀም ይከታተላሉ። የግንባታ ሠራተኞች ቀን ከሌሊት አያርፉም። ሌላው ቀርቶ፣ የክፍለ ከተማ አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትጋት እነዚህን የልማት ሥራዎች በፍጥነት ለመፈፀም ክትትል እና ርብርብ ያደርጋሉ። ግንባታቸው በአጭር ጊዜ የማያልቁ አካባቢዎች ደግሞ በመንገዶቹ ላይ የሚንሸራሸሩ ሰዎች እንዳያዩዋቸው ስዕል በተሳለባቸው ረዣዥም የቆርቆሮ አጥሮች ተከልለዋል። 


የውጭ አገር ጎብኚዎች እና ዲፕሎማቶች ሲመጡ እነዚህን ቦታዎች እንዲጎበኙ ይበረታታሉ። ብልፅግና ፓርቲ ራሱም ከፍተኛ አመራሮቹን ሥልጠና ሰጥቶ ሲጨርስ የሚያስጎበኛቸው፣ እነዚህን የልማት ሥራዎች ነው። ታዲያ በጥቅምት ወር 2018 መጨረሻ፣ ከሥልጠና በኋላ የወንዝ ዳር ልማቱን ከጎበኙት የብልፅግና ሰዎች አንዷ – ፈዲላ ቢያ (በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የሕዝብና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ) – የልማት ሥራው “የምድር ሥራ ብቻ ሳይሆን የሰማይም ነው” ብለውታል። እነዚያ አካባቢዎች ላይ ነው “ሰው ተፈናቀለ ተብሎ የተወራው፤ ሰው ወደ ጤናው ነው የተመለሰው” ቢባል ይሻላል ብለዋል። የእርሳቸው ንግግር መንግሥት ጥሩ እየሠራሁ ነው ብሎ ስለሚያስብ፣ ትኩረቱ ሁሉ መናፈሻዎቹ ላይ ሆኖ፣ የተፈናቀሉት ሰዎች “ውለታ ተውሎላቸዋል” በሚል ብቻ የሚታለፉበት ፈታኝ ሁኔታ ላይ ትኩረት ሳያገኙ እንደቀሩ የሚያሳብቅ ነው። 


ኢሕአዴግ ሚዲያዎችን በሁለት ይከፍላቸው ነበር፤ ‘ልማት አብሳሪ’ እና ‘መርዶ ነጋሪ’ በሚል። ብልፅግናም ይህንኑ ቀኖና ሃይማኖታዊ (superstitious) ገጽታ አባብሶት ቀጥሎበታል። አዎንታዊው ነገር ላይ ብቻ በማተኮር ብልፅግና ይመጣል ብሎ በማሰብ፣ ስኬቱ ላይ ብቻ በማተኮር ውድቀቱን እንዳላዩ ወይም አድበስብሶ ማለፍ ይመርጣል፤ ይህ የፖለቲካው ፍልስፍና ነው። በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ እና የገዢው ፓርቲ ወገን የሆኑ ሚዲያዎች፣ ልማቱን ለማሳየት የሚሞክሩትን ያህል፣ የልማት ተነሺዎቹን ሁኔታ ማሳየት አይመርጡም። ልክ እንደሚዲያዎቹ ሁሉ የመንግሥትም የትኩረት አቅጣጫም የለማው ላይ እንጂ የጠፋው ላይ አይደለም።


ምስል 1፡ የአራዳ ፓርክ በባልሥልጣናት በተጎበኘበት ጊዜ ለአጭር ጊዜ ቆሞ የነበረ ቦርድ ላይ የታተመ (ተነሺዎች ይኖሩበት የነበረ እና አሁን ተዛውረውበታል የተባለን ኮንዶሚኒየም ያሳያል፤ ነሐሴ 2017)

የልማት ተነሺዎቹ አዲስ የገቡባቸው መኖሪያዎች በፎቶ እንደሚታዩት እና መንግሥት ናቸው እንደሚላቸው የተዋቡ አይደሉም፤ የብዙዎቹ ውስጣዊ ግንባታቸውም ቢሆን ያልተጠናቀቀላቸው እና ለመኖሪያነት ብቁ ያልሆኑ ናቸው። የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶቹ ሥራ ዋነኛ ሀጢያት የልማት ተነሺዎቹ መብቶች እና ዕጣ ፈንታ የአዲስ አበባን የማስዋብ ሥራ ቅንጣት ያክል እንኳን ትኩረት አለማግኘቱ ነው። የኮሪደር እና የወንዙ ልማት ጉዳይ የልማት የሆነውን ያክል (ወይም ከዚያ የበለጠ) የልማት ተነሺዎቹ ቤት፣ እና ለመኖር የሚያስፍልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች መሟላት ጉዳይ፣ ልማት እንደሆነ መንግሥት የዘነጋው ይመስላል። 


ይህንን በተመለከተ፣ ስለ መንደሮቹ አፈራረስ እና ስለተነሺዎቹ ዝውውር ጥቂት እናውጋ።

 

የአፈራረሱ ሒደት


የሚፈርሱ ሰፈሮች ነዋሪዎች መንደራቸው እንደሚፈርስ የሚነገራቸው ይህ ነው የሚባል ተገማች ደንብ በሌለው በተለያየ የጊዜ ርዝመት ነው። ብዙዎቹ ግን “ሰፈሩ ይፈርሳል” የሚል ወሬ በተደጋጋሚ ሲሰሙ እንደከረሙ ይናገራሉ። ለምሳሌ የእኛ ሰፈር ከመፍረሱ ከዓመት አስቀድሞ (ጥቅምት 2016) በመንግሥት ኃላፊዎች አማካይነት “ለወንዝ ልማት ፕሮጀክት ይፈርሳል” የሚለው በስብሰባ ተነግሯቸዋል። በወቅቱ የካ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ነዋሪዎችን ሰብስበው ቤቶቹ ፈርሰው ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዛወሩ ሲናገሩ፣ የእያንዳንዱ ንብረት (ጣራ እና ግድግዳ) ዋጋ ተገምቶ፣ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተሰልቶ፣ ለንብረት ካሣ እንደሚከፈል፣ መልሶ መገንቢያ ቦታዎች እንደሚሰጡ፣ እንዲሁም መልሶ ለመገንባት ምክንያታዊ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ለነዋሪዎች ተናገሩ። ብዙዎቹ የሰፈራችን ነዋሪዎች በኃላፊው ቃል ኪዳን እምነታቸውን ጥለው ነበር። 


ይህ በሆነ በሳምንቱ፣ የመንግሥት ሠራተኞች በሰፈሩ እየተዘዋወሩ የሚፈርሱ ጊቢዎች ውስጥ ያሉትን የእያንዳንዱን የጣራ እና ግድግዳ፣ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ተክሎች ጭምር ግምት ለማስላት የሚያስችላቸውን መረጃና ልኬት ሰብስበው ወጡ። ከዚያም ለአንድ ዓመት ያህል፣ ከአሉባልታ በስተቀር ምንም አልተሰማም። በዚህ ጊዜ፣ በመሐል ከተማ የኮሪደር ልማት የሚባለው እንቅስቃሴ ተጀምሮ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የአዲስ አበባ የቆዩ ሰፈሮች ይፈርሱ ጀመር። 


ከአድዋ ሙዚየም ፊት ለፊት የነበሩ የዶሮ ማነቂያ ነዋሪዎች አድዋ ሙዚየም እስኪመረቅ ድረስ፣ ስለመንደራቸው መፍረስ በይፋ እንዳልተነገራቸው ነግረውኛል። እዚህ ሰፈር የሚኖሩት አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች በቀበሌ ቤት ውስጥ ስለሚኖሩ፣ አዳዲስ ወደተሠሩ ኮንዶሚኒየም እንደሚዛወሩ ተነግሯቸዋል። ካዛንቺስም፣ ፒያሳም ያሉ የቀበሌ ነዋሪዎች እንደሚነሱ በተነገራቸው ከሦስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተነስተዋል። አንዳንዶቹ ነዋሪዎች ወደ ኮንዶሚኒየም ለመዛወር ግዢ ወይም ኪራይ ምርጫ እንደሚሰጣቸው ነግረውኛል። ግዢ የሚመርጡት ለሁለት መኝታ ቤት 106 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ እና በየወሩ 5 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ነዋሪዎች በቀበሌ ቤት ውስጥ ይከፍሉ የነበሩት፣ በወር 10 እና 15 ብር ገደማ ነበር፤ አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ናቸው።


ይህ በእንዲህ እያለ፣ መስከረም 2፣ 2017፣ የሰፈራችን የቤት ባለንብረቶች በባለሥልጣናቱ ጥሪ ተሰብስበው የተፈራው ቀን እንደደረሰ በድጋሚ አወጁ። በዚህ በቃል በተሰጠ መግለጫ ላይ ከበፊቱ ያልተለየ ግርታ ተፈጠረ። ይህ በሆነ በወሩ ነዋሪዎች ለስብሰባ ተጠርተው፣ ከነርሱ መካከል የተመረጡት የምትክ ቦታ ዕጣ እንዲያወጡ ተደረገ እና ይህም ዜና ተሠራበት። ሌሎቹም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ በግላቸው፣ በክፍለ ከተማው ጽ/ቤት ዕጣዎችን አወጡ። ይሁን እንጂ በኮድ ካወጡት የምትክ ቦታ ዕጣ በቀር ምትክ ቦታው የት እንደሆነ እና ምን እንደሚመስል አንዳቸውም አያውቁም ነበር። 


በጥቅምት ወር 2017፣ የክፍለ ከተማው የካሣ ክፍያ ለቤተሰቦች ቀስ በቀስ መተላለፍ ጀመረ። የማካካሻው ክፍያ ከንብረቶቹ የገበያ ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ይሆናል። በተጨማሪም፣ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር ሎተሪ ቢያወጡም፣ አዲስ የሚሰፍሩበት ቦታ የት እንደሆነ አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ፣ ነዋሪዎቹ ቤታቸውን ለቀው በሦስት ቀናት ውስጥ እንዲወጡ የቃል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። አንዳንድ ቤተሰቦች ቤታቸውን በራሳቸው ኃይል ለማፍረስ፣ ከንብረት ካሣው ላይ የተወሰነ ገንዘብ እንዲቀነስ ተስማምተዋል። ይህን በማድረግ አንዳንድ ጠቃሚ (ቆርቆሮ፣ ፌፎ የመሳሰሉትን) ፈራሽ ንብረቶችን ለራሳቸው ማትረፍ ይችላሉ፤ ምክንያቱም የማካካሻ ግምቱ ከንብረቱ ዋጋ ያንሳል። ራሳቸው ቤታቸውን ለማፍረስ ላልጠየቁ ባለንብረቶች፣ ከማኅበረሰቡ ውስጥ የወጡ ወጣቶች በመንግሥት ክፍያ ቤቶቹን እንዲያፈርሱ የሚያደርጉበት አሠራርም አለ። ይህም በነዋሪዎቹ መካከል ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል። 


የእኛ ሰፈር እየፈረሰ ባለበት ወቅት ካዛንቺስም እየፈረሰ ነበር። ያነጋገርኳቸው ቤታቸው የፈረሰባቸው የካዛንቺስ ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ከሆነ፣ አንዳንዶቹ ስለሰፈራቸው መፍረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሙት፣ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ የሚሔደው የኮሪደር ልማት ተጠናቆ ሲመረቅ፣ በቴሌቪዥን ነው። ካዛንቺስ የቀበሌ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ወጣቶች፣ ቤታቸው ከመፍረሱ በፊት የሚዛወሩበትን ቦታ በተመለከተ፣ የቤት ጣሪያዎቻቸው ላይ በመውጣት ራሳቸውን ለመጉዳት በማስፈራራት ከመስተዳድሩ ሠራተኞች ጋር ተደራድረዋል።


ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም በደብዳቤ የሚከናወን ሥራ የለም። ነዋሪዎች እንደሚነሱ ሲነገራቸውም ይሁን ካሣ ሲገመትላቸው፣ እንዲሁም በሦስት ቀን ውስጥ ቤታቸው እንደሚፈርስ ሲነገራቸው - ሁሉም ነገር በቃል ብቻ ነው። ነዋሪዎቹ በተሰጣቸው ጊዜ ማጠር፣ በካሣ አሰጣጡ ላይ ወይም በሌላ አሠራር ጉዳይ ቅሬታ ለማቅረብ ቢፈልጉ እንኳን አንዳችም የተጻፈ ማስረጃ አይኖራቸውም። ይህንን ልበል እንጂ የፍርድ ቤት መንገዱም የተዘጋ ነው፤ አዋጅ ቁጥር 1336/2016 የልማት ሥራዎችን እግድ በፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ብቻ እንዲወሰን ያዛል። የፍርድ ቤት ፕሬዚደንቶች የመንግሥት ሹመኞች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በፓርላማ ሳይቀር እንዲህ ዓይነት አቤቱታዎች ሥራችንን ስለሚያስተጓጉሉ አንቀበልም ብለዋል። ይኼ ጽሑፍ ከተጠናቀቀ በኋላ "አአ ይዞታ ማስለቀቅና ካሳ ጉዳዮች ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ምትክ ቦታና ካሳ ቅሬታን ማየት ይችላል'' የሚል የወል መልዕክት (mass sms) ደረሰኝ። ለትላንት ረሃብ፣ ዛሬ ገበታ ማቅረብ እንደማለት።


ካሣ እና ዝውውር


የመሐል ከተማ ተነሺዎች የተዘዋወሩት ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች ነው፤ እነዚህም፣ ጉራራ፣ አራብሳ፣ ሰፈረ ማሪያም፣ ቤተል፣ ላፍቶ፣ ገላን ጉራ፣ ዓለም ባንክ አካባቢዎችን ይጨምራል።


“ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ” አዋጅ ቁጥር 1161/2011 የከተማ ቤቶች ሲነሱ ስለሚሰጠው ካሣ ዝርዝር መርሖዎችን ያስቀምጣል። ይኸውም ‘በአካባቢው ግምት የጉልበት እና ንብረት ዋጋ፣ አዲሱ ቤት እስኪገነባ ለሁለት ዓመታት ያለኪራይ ክፍያ የሚ፟ሰጥ ቤት ወይም የኪራይ ግምት በገንዘብ፣ ለመንግሥት ቤት ተከራዮችም ምትክ ቤት ከመስጠት ባሻገር የአንድ ዓመት የቤት ኪራይ ግምት የልማት ተነሺነት ካሣ ይሰጣቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የማህበራዊ ትስስር መቋረጥና የሥነ-ልቦና ጉዳት ለልማት ተነሺዎች ማካካሻ ይከፈላቸዋል’ ይላል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ሠራተኞችም በቃል ይህንን ያረጋግጣሉ። ሆኖም ተግባሩ ከዚህ ፍፁም የተለየ ነው። በአጭር ቋንቋ፣ መንግሥት ለግል ባለይዞታዎች የጣሪያና ግድግዳ ካሣ ከምትክ መሬት ጋር (የትም ቢሆን) እና ለመንግሥት ቤት ተከራዮች ምትክ (እና የእቃ ማጓጓዣ ገንዘብ) ብቻ ሰጥቶ በአጭር ጊዜ፣ ያለምንም መልሶ የማቋቋሚያ ካሣ ያሰናብታቸዋል።


ያነጋገርኳቸው ሰዎች እንደመሰከሩት፣ አሠራሩ የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎች የጣሪያ እና ግድግዳ (የንብረት ካሣ) ይሰጣቸዋል፤ በተጨማሪም ምትክ ቦታ ይሰጣቸዋል። የገንዘብ ካሣውም፣ የቦታ ምትኩም ግን እንደግል ይዞታቸው ሕጋዊነት ይለያያል። በመስተዳድሩ አሠራሮች - ካርታ ያላቸው፣ ዲጂታል ካርታ ያላቸው፣ የ97 የአየር ካርታ ያላቸው፣ ለይዞታቸው ግብር እየከፈሉ የነበሩ፣  ወዘተ  እየተባሉ እንደዓይነታቸው የተለያየ የካሣ ዓይነት ይወጣላቸዋል። ነገር ግን ለአካባቢው መሠረተ ልማት ያወጡት ወጪ ከቁብ አይቆጠርም። ለማኅራዊ ኑሮ መፍረስ ግን ጥቂት ካሣ የተሰጣቸው አሉ። ብዙዎቹ የቤት ባለቤቶች ገንዘብ ተሰጥቷቸው መሬት ሳይሰጣቸው በፊት ነው በሦስት ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የሚደረገው። 

 

ይህ አጠቃላይ አሠራሩ ሲሆን፣ ከእኛ ሰፈር ተነሺዎች መካከል የንብረት ካሣ ክፍያው ገቢ ከተደረገላቸው በኋላ የተነሱት ሰዎች በሙሉ፣ ምትክ መሬቱ የተሰጣቸው ከወራት በኋላ ነው። ምትክ መሬት እስኪሰጣቸው ድረስ ተከራይተው ይኖራሉ። ምትክ መሬት ከተሰጣቸውም በኋላም ቢሆን የካርታ እና የግንባታ ፈቃድ ማውጣት ሒደቶች ተጨማሪ ወራት ይፈጃሉ። ብዙዎቹ የካሣ ገንዘባቸውን ላለመጨረስ ሲሉ፥ መሬቱ እንደተሰጣቸው ጊዜያዊ የቆርቆሮ ቤት በመሥራት ይገቡበታል። እኛ ሰፈር ከወላጆቻችን ውስጥ አብዛኛዎቹ  መጦሪያቸው፣ በጉብዝናቸው ወራት በየጊቢያቸው የሠሯቸው የሚከራዩ ቤቶች ነበሩ። እነዚያ ቤቶች አሁን ፈርሰዋል። ስለዚህ ካሣ ከተሰጣቸው ገንዘብ ላይ እየቆነጠሩ ወራቶቻቸውን ይገፋሉ። አንዳንዶቹ የተሰጣቸውን የካሣ ክፍያ አብቃቅተው ቶሎ ቤት ካልሠሩ፣ ገንዘቡ አልቆ (በግሽበት ተዳክሞ) ወደ ቀውስ ሊገቡ እንደሚችሉ መገመት አይቸግርም።


ብዙዎቹ የቤት ባለቤቶች ልጆቻቸውም በነርሱ ጊቢ ቤተሰብ መሥርተው ይኖሩ ስለነበር፣ እነርሱም ሌላ ቤት ይከራያሉ። ሆኖም የካሣ ስርዓቱ እነርሱን አይጨምርም። የገበሬ መሬት ሲሆን ግን ይህ ስርዓት እንደሚቀየር አንዳንድ ታዛቢዎች ነግረውኛል። የገበሬ ልጆች እያንዳንዳቸው የተጨማሪ የጥገኛ ካሣ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሰምቻለሁ።


የካሣ አሰጣጡ ለሁሉም ተመሳሳይ አሠራር የለውም፤ መጀመሪያ አካባቢ ጥሩ የነበረው በኋላ እየቀነሰ ሔዷል። የወንዝ ልማት ፕሮጀክቱ የሚሠራው በአንዳንድ ኤምባሲዎች ድጋፍ ስለሆነ አንፃራዊ የተሻለ ካሣ እንደሚሠጥበትም ሰምቻለሁ። በሌላ በኩል በቅድሚያ ካሣ የተሰጣቸው ሰዎች ሙሉ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን፣ በተለያየ ቢሮክራሲያዊ ምክንያቶች የዘገዩት ደግሞ ጎዶሎ ክፍያ ተሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ የካሣው ግማሽ ብቻ ተሰጥቷቸው ግማሹን ሌላ ጊዜ እንሰጣችኋለን ተብለው የተነሱ ነዋሪዎች እኛም ሰፈር አሉ። (ካሳንቺስ መለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ፊት ለፊት ያለው ሰፈር የሚኖሩ የቤት ባለቤቶች ደግሞ) ጭራሹኑ ምንም ሳይሰጣቸው፣ ወደፊት ይሰጣችኋል ተብለው እንደተነሱ ተነግሮኛል። ምትክ ቦታ ተሰጥቷቸው፣ ነገር ግን ቦታው የሌላ ሰው ይዞታ ባለቤትነት ክርክር ተነስቶበት ድጋሚ ሌላ ቦታ የተሰጣቸውም እንዳሉ ሰምቻለሁ።


በካሣው ገንዘብ መጠን ደስተኛ የሆነ አንድም ሰው እስካሁን አልገጠመኝም። በተሰጣቸው ምትክ ቦታ ግን የተደሰቱ ብዙ ሰዎችን አግኝቻለሁ። በተለይ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ወንዝ አፋፍ ላይ የተንጠለጠለ ቤት የነበራቸው ነዋሪዎች፣ በተሰጣቸው ምትክ ቦታ ባብዛኛው ደስተኛ ይመስላሉ። ምትክ መሬት አሰጣጡ ነዋሪዎቹ እንደሚመርጡት ደረጃ፣ መሠረተ ልማት የተሟላለትም፣ ያልተሟላለትም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ ነዋሪዎቹ ቤቶቻቸውን የመገንባት እና ሰፈሮቻቸውን የማልማት ጫና ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል። 


የመንግሥት ቤት ተከራዮች እንደምርጫቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በኪራይ ወይም በረዢም ጊዜ ክፍያ ግዢ ይወስዳሉ። እኔ የጎበኘኋቸው ከፒያሳ ወደ ዓለም ባንክ አለፍ ብሎ፣ በተለምዶ “ስልጤ ሰፈር” ያለ ኮንዲሚኒየም የገቡ ነዋሪዎች አሉ። ወደ ኮንዶሚኒየሙ ሲገቡ ግንባታው አልተጠናቀቀም ነበር። የሽንት ቤት ሲንኮች የተገጠሙት እነርሱ ከገቡ በኋላ ነው፤ ከመገጠማቸው በፊት በአቅራቢያ ያለ የኦሮሚያ መንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በወረፋ ይጠቀሙ እንደነበር ተነግሮኛል። እስካሁንም መስኮታቸው መስታወት ያልተገጠመላቸው ቤቶች አሉ። ሰፈሩ ከመሐል ከተማ እጅግ የራቀ ነው። መንገዱ በቅጡ ያልተጠረገ ነበር። በክረምት ወቅት ስጎበኘው፣ ትራክተሮች መንገድ እያረሱ ስለነበር በጭቃ ተጥለቅልቆ ነበር። የውሃ እና የመብራት አገልግሎትም ከፍተኛ እጥረት እንደነበረባቸው ያነጋገርኳቸው ሰዎች ነግረውኛል። 


ምስል 2፡ “ስልጤ ሰፈር” አለፍ ብሎ ኮንዶሚኒየም የተሰጣቸው የመሐል ከተማ ተነሺዎች የሚኖሩበት ሰፈር፣ ነዋሪዎቹ ከገቡ ከአንድ ዓመት በኋላ የነበረው ገጽታ (ሐምሌ 2017)።

ምስል 3፡ አንድ አረጋዊ ያልተጠናቀቀ ኮንዶሚኒየም ከፒያሳ ተነስተው በምትክ ቤትነት ከተሰጣቸው በኋላ ውስጣዊ ግንባታውን ማጠናቀቅ ባለመቻላቸው እየኖሩበት ያለው ገጽታ (ሐምሌ 2017)። 


ቤቶቹን ለመግዛት ቅድመ ክፍያውን እና በየወሩ የሚከፈለውን ለመፈፀም የተወሰነ የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም የእፎይታ ጊዜው ቢያልቅም እስካሁንም ብዙዎች መክፈል አለመጀመራቸውን ነግረውኛል። እንዲያውም አንዳንዶች “ክፈሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሲመጣባቸው ቤታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ በመንደር ውል እየሸጡ፣ አራብሳና ኮየፈጬ አካባቢ ስቱዲዩ የመሳሰሉ አነስተኛ ክፍሎችን እየገዙ እንደሔዱ ሰምቻለሁ። 


እነዚህ ተነሺዎች በአዲሱ ሰፈር ሌሎችም ችግሮች ተጋርጠውባቸዋል። በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች አቅም በመሟጠጡ የሙሉ ቀን ትምህርት የግማሽ ቀን ሆኖ፣ የጠዋትና ከሰዓት የተደረገባቸው ተቀባይ ሰፈሮች መኖራቸውን ሰምቻለሁ። ተቀባዮቹ ሰፈሮች ይህንን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት አላደረጉም፤ የመጡትን ለማስተናገድ የሚያስችል ቢሮክራሲያዊ አቅምም ያላቸው አይመስልም። በተጨማሪም፣ በቀድሞው ሰፈራቸው ትናንሽ ኢመደበኛ ሥራዎች ላይ ተሠማርተው የነበሩት ሰዎች፣ አዲሶቹ ሰፈሮች ገና በቅጡ ስላልተደራጁ መልሰው ወደ ሥራ መሠማራት አልጀመሩም። መደበኛ ሥራ ይሠሩ የነበሩትም በቦታው ርቀት ምክንያት ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ተዳርገዋል። ሥራቸውን በርቀቱ ምክንያት የተዉም ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ።


ከፒያሳ ተነስተው ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች የተገፉት ነዋሪዎች፣ አቧሬን እንደምሳሌ በመጥቀስ ለምን በቀደሞው ሰፈራቸው መልሰው እንዲኖሩ እንዳልተደረገ ይጠይቃሉ። የአቧሬ ተነሺዎች፣ እዚያው አካባቢ ባሉ ጊዜያዊ መጠለያዎች እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ፥ በፈረሰው ሰፈራቸው ውስጥ በፍጥነት በተገነቡ እና መሠረተ ልማታቸው በተሟላላቸው ቤቶች ውስጥ መልሰው እንዲገቡ መደረጉን በመጥቀስ “እኛም እንደነርሱ ፒያሳ እና ካዛንቺስ ቤት ሊሠራልን ይገባ ነበር” ሲሉ ነግረውኛል። አንድ ተመራማሪ ይህንን ጉዳይ ሲገልጹ፣ በተለይ በፒያሳ እና ካዛንቺስ እየተደረገ ያለው ነገር ውጤቱ የሀብታም እና የድሃ ሰፈር መፍጠር ይሆናል ብለዋል። ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ሰፈሮች ከሞላ ጎደል ድሃ እና ሀብታም ተቀላቅሎ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ አሁን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ወደ ከተማው ዳርቻ በመገፋታቸው፣ መሐል ከተማው ውስጥ የሚሠሩትን ዘመናዊ አፓርትመንቶች ሀብታሞች ይገቡባቸውና በግልጽ የተለዩ የሀብታም እና የድሀ ሰፈሮች ይፈጠራሉ የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።


በሌላ በኩል ከካዛንቺስ የተነሱ አንዳንድ ነዋሪዎች የተሻለ እና መሠረተ ልማቱ የተሟላለት ኮንዶሚኒየም ውስጥ መግባታቸውን ሰምቻለሁ፤ እነዚህ ተነሺዎች በቴሌቪዥንም በተደጋጋሚ ቀርበዋል። አልፎ ተርፎም የቤት ኪራይ ውዝፍ በዝቶባቸው ከንቲባዋ ለጉብኝት ሲሔዱ ተሰብስበው አቤቱታ በማቅረብ ቅናሽ እንደተደረገላቸው ሰምቻለሁ። በተመሳሳይ ጉራራ አካባቢ የሰፈሩ ተነሺዎችም የቤት ኪራዩን በተቃውሞ መደራደር ችለዋል።


ሆኖም ካሣ እና ምትክ አሰጣጥ ስርዓቱ እንደየሁኔታው እና ቦታው የተለያየ ነው። ከፈረሰባቸው ሰፈር ብዙም ሳይርቁ ምትክ የተሰጣቸው ጥቂት ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ እኛ ሰፈር ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያን ላሉበት ቤተሰቦች ከሰፈሩ ያልራቀ እና ዋና መሠረተ ልማት የተሟላለት ሰፈር ውስጥ ምትክ ቦታ የተሰጣቸው ሰዎች አሉ፤ እርግጥ ነው እነዚህም ቢሆን በተሰጣቸው ያልተመጣጠነ ካሣ ቤት ገንብተው የአዲስ ጎጆ ወጪ ጣጣ ውስጥ ማለፍ ገና ይጠብቃቸዋል። ከፒያሳ ተነስተው ስድስት ኪሎ አካባቢ ምትክ የተሰጣቸው የመንግሥት ቤት ተከራዮችም እንዳሉ ሰምቻለሁ።


የሚበለፅጉት እና የሚደኸዩት


ከላይ የጻፍኩት እንደሚያመለክተው ከኮሪደር ልማቱ ተነሺዎች መካከል የትኞቹ ይበለፅጋሉ፣ የትኞቹስ ይደኸያሉ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቀላል መለኪያ እንደሌለ መገመት ይቻላል። ነገር ግን የሚደኸዩም የሚበለፅጉም አሉ። ቀድሞውንም ችግር ላይ የነበሩ እና በዝቅተኛ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩት ላይ ጫናው ይከፋባቸዋል። አጋዥ የሌላቸው አረጋውያን እና ሴቶች ደግሞ የገፈቱ ዋነኛ ቀማሾች ናቸው። እነዚህ ተነሺዎች አዲስ በገቡበት ሰፈር ሥራ ማግኘት ይቸግራቸዋል። መንግሥት ለሰጣቸው ኮንዶሚኒየም የኪራይም ይሁን የባለቤትነት ክፍያ መክፈል አይችሉም። ምትክ ቤቶቹ የተጠናቀቁ ባለመሆናቸው ያንን ማጠናቀቅ የሚያስችል አቅም የላቸውም። ምትክ ቦታ የተሰጣቸውም ሰዎች ቢሆኑ ቤት ሠርተው እስኪያጠናቅቁ ድረስ ወይ በተከራይነት፣ አልያም በቆርቆሮ ቤት ኑሯቸውን ይገፋሉ። በአካባቢያቸው መሠረተ ልማቶች (መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ጣቢያዎች) እስኪሠሩ ድረስ በጣም አስቸጋሪ ሕይወት ይገፋሉ። በኪራይ ቤት ይተዳደሩ የነበሩም፣ የካሣ ገንዘቡን እየቆነጠሩ ስለሚኖሩበት የቀድሞ ቤታቸውን ያክል ደግመው መገንባት ይቸገራሉ። ሌሎች የኢኮኖሚ ምንጮች የነበራቸው እና የሚያግዟቸው ሰዎች ያሏቸው ሰዎች ግን ሽግግሩን የተሻለ ሊቋቋሙት ይችላሉ። 


በጥቅሉ፣ የቤት ባለቤት የነበሩት ተነሺዎች ቀድሞ የነበሩበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ በርካታ ዓመታት ይፈጅባቸዋል። የቀበሌ ቤት በኮንዶሚኒየም የተተካላቸው ምናልባት በፍጥነት የማገገም ዕድል አላቸው። 


ይህም ሆኖ ተነሺዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ ቢሶች ናቸው ማለት አይደለም። እንዲያውም፣ በሚገርም ሁኔታ ጥቂት የማይባሉት በጣም ትልቅ ተስፋ ይታያቸዋል። አንድ ከሃምሳ ዓመት በላይ ፒያሳ የኖሩ እና ተፈናቅለው “ስልጤ ሰፈር” ያለው ኮንዶሚኒየም የገቡ አረጋዊ ቤታቸው በጣም ጎስቋላ እና መስኮት እንኳን የሌለው ነው። ነገር ግን የቤቱን ዕዳ ልጆቻቸው እንደሚከፍሉላቸው እና አዲሱ ቤታቸው ከ10 ዓመት በኋላ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጣ ሲነግሩኝ ፊታቸው በተስፋ ብርሃን ተሞልቶ ነው። ፒያሳ ይኖሩ የነበረው በወር 10 ብር ይከፈልበት የነበረ የቀበሌ ቤት ውስጥ ነው። “ይህ ሰፈር በአምስት ዓመት ውስጥ እንደ ፒያሳ የሚደምቅ ይመስልዎታል?” ስላቸው “ከፒያሳ ባይበልጥ!” ነበር ያሉኝ። በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ የነበረ ጎረቤታቸው ግን እንደርሳቸው ደስተኛ አልነበረም። “ፒያሳ እና መገናኛ እየተሯሯጥኩ ነበር የምሠራው፣ አሁን ግን የትራንስፖርት ወጪ ራሱ ራስ ምታት ነው” ብሎኛል፣ “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ፣ እህሌ የሚደርሰው ለፍልሰታ” በሚመስል ምፀት። ይህ ወጣት ከወላጆቹ የወረሰው የቀበሌ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖረው፤ የኮንዶሚኒየሙ ቅድመ ክፍያንም ይሁን የወር ክፍያዎች መክፈል ተቸግሮ እንዳልከፈለ ነግሮኛል። በዚህ ሳቢያ ቤቱን በመንደር ውል ሸጠው ከሚሔዱት ሰዎች መሐል እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ!


የእኛ ሰፈር ነዋሪዎችም በልማት ሥም ከተነሱ ሕዳር 2018 አንድ ዓመት ሞላቸው። ከነዚህ ውስጥ ከገደል አፈፍ ተነስተው፣ ከቀድሞ ቤታቸው የተሻለ ቤት የሠሩ ሰዎች አሉ። የግንባታ ፈቃድ አውጥተው ያልጨረሱም አሉ። ጨርሰው ወደ ግንባታ እየገቡ ያሉም አሉ። አሁን ከከተማ መሐል ቢርቅም፣ መሠረት ልማት ባይሟላለትም፣ የተሰጠን ቦታ ወደ ፊት ግን “እሳት የላሰ” ከተማ ይሆናል በሚል ተስፋ ሕይወትን እንዳዲስ ለመጀመር አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት የጓጉም አሉ። 


በሚገርም ሁኔታ፣ መንደሮቹ ሲፈርሱ ከጥቂት ገጠመኞች በቀር አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች በጣም ተባባሪዎች ነበሩ፤ እነዚህን ብዙ በደሎችን "ለአገር ይበጃል" በሚል በይሁንታ ያስተናገዱ ነዋሪዎችን መንግሥት የያዘበት ሁኔታ ግን የሚያሳዝን ነው። ጥቂት እምቢተኝነቶች ሲከሰቱ የፀጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ እርምጃ በመውሰድ በእስር እና ማዋከብ ነገሩን ከሥሩ ያከሽፉታል።


የነዋሪዎቹ ዝምታ በአንድ በኩል ከአቅመ ቢስነት የሚመነጭ ነው። በእምቢተኝነት ምንም አናመጣም የሚል ጥቅል አስተሳሰብ አለ። በሌላ በኩል መንግሥት ሁሉንም የማድረግ መብት እና ሥልጣን አለው ብሎ ከማሰብ የሚመነጭም ነው፤ አንድ አረጋዊ ስጠይቃቸው “መንግሥት ተነሱ ካለ ምን ማድረግ ይቻላል?” ብለውኛል። አልፎ ተርፎም፣ እምቢተኝነት የካሣ እና ምትክ ጉዳይን ሊያወሳስብ ይችላል የሚል ፍርሐት አለ። ነዋሪዎቹ ተባብረው እንኳን አቤት ለማለት እርስ በርስ አይተማመኑም፤ ሁሉም ተነሺዎች አንድ ዓይነት ቅሬታ እና አቤቱታ ስለሌላቸው ለመተባበር ይቸገራሉ። አልፎ ተርፎም የማፍረስ ውሳኔው እና ሒደቱ እጅግ የተፋጠነ ስለሆነ፣ ሰዎች ለመደራጀት እና ጥያቄ ለማቅረብ አይችሉም፤ የተመሳቀለውን ሕይወታቸውን ወደ ማስተካከል ሥራ ይጠመዳሉ። በእምቢተኝነት ለውጥ እናመጣለን ብለው ባለማመን፣ በእሺተኝነት የተገኘውን ኃይል ለማግኘት ይማልዳሉ፤ ለዚሁ ሲባል ጉቦ እስከመክፈል የሚደርሱም እንዳሉ ይወራል። ምክንያቶቻቸው ግን በእነዚህ አይወሰኑም፤ አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ሁኔታ መቀየር እንደነበረበት ያምናሉ፤ አጋጣሚውን እንደመልካም የሚመለከቱትም ጥቂት አይደሉም። የልማት ሥራውም ይሁን የነርሱ መነሳት ለበጎ እንደሆነ የሚያምኑ ብዙ ናቸው። ስለሆነም እነዚህኞቹ በአነሳስ እና ምትክ አሰጣጡ ላይ መደራደር ይፈልጋሉ እንጂ መነሳቱን መቃወም አይፈልጉም። 


ለወደፊቱ ምን ይደረግ?


ለወደፊቱ ሊደረጉ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ነገር ግን የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ አዲስ በሚገነቡት መናፈሻዎች ላይ እንጂ ለልማቱ ቦታ በለቀቁት ነዋሪዎች አኗኗር ላይ ስላልሆነ፣ የመንግሥትን ቀልብ ማግኘት ይቸግራል። ስለሆነም፣ ሚዲያዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎችም የመፍትሔ ሐሳቡ ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት ማድረግ አለባቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ በመጪው ምርጫ ብልፅግናን ለመሞገቻ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።


በዚህ ዓመት አዲስ የኮሪደር ልማት እንደማይጀመር ከንቲባዋ ተናግረዋል። ስለዚህ የመፍትሔ ሐሳቦቹን ለመተግበር ምቹ ጊዜ ነው።


በመጀመሪያ፣ ከዚህ በፊት ለልማት ተነስተው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ያሉ ነዋሪዎችን ይመለከታል። በዋነኝነት ችግሩን የሚመረምር የገለልተኛ ባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ አስቸኳይ ጥናት (rapid assessment) በማጥናት የእርምት እርምጃዎች ሊወሰዱባቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሁንም አሉ። ለምሳሌ ያክል በማይመጣጠን ካሣ የተነሱ ነዋሪዎችን የካሣ አሰጣጥ በድጋሚ በመገምገም እና አብዛኛዎቹ በጥድፊያ የተነሱ በመሆኑ የደረሰባቸው ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተገምቶ የካሣ ማስተካከያ ሊደረግላቸው ይችላል፤ እንዲሁም፣ የመሠረተ ልማት ጉዳዮች የሚገባውን ያክል ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ይቻላል። የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ ጉዳይ በአጭር ጊዜ ሊቀረፍ የሚችል መሆኑን በኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታዎች ላይ የታየውን ቅልጥፍና መጥቀስ ይቻላል። ልዩነቱ ለኮሪደር ልማቱ የተሰጠውን ያክል ትኩረት ለልማት ተነሺዎቹ አለመሰጠቱ ብቻ ነው። በተመሳሳይ የልማት ተነሺዎች የሰፈሩባቸውን አዲስ አካባቢዎችን ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ ሥራዎች በማከናወን በመደበኛ እና ኢመደበኛ ሥራዎች ላይ ተሠማርተው ገቢ የሚያገኙ ነዋሪዎች መተዳደሪያ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል።


በቀጣይ፣ በማናቸውም ሁኔታ ለልማት የሚነሱ ነዋሪዎችን በተመለከተ፣

  • መንግሥት የልማት ዕቅዱን በቀጥታ ለተጎጂ ነዋሪዎችም ይሁን ለብዙኃን በማቅረብ ማወያየት እና በዜጎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ፣ ማንም ሳይጎዳ ሁሉም የሚጠቀሙበት የልማት ሥራ ለመሥራት ነዋሪዎችን ማሳተፍ ይኖርበታል። ፕሮጀክቶቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚደረገው ርብርቦሽ የሚደነቅ ቢሆንም፣ የፕሮጀክቶቹ ዕቅድ ግን ምክንያታዊ ጊዜ ተሰጥቶት፣ በግልጽነት እና አሳታፊነት መቀረጽ ይኖርበታል። 

  • የልማት ተነሺዎች ስለተነሺነታቸው ቢያንስ ከሁለት ዓመት ቀድመው እንዲያውቁ ማድረግ፣ ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት ካሣ እና ምትክ እንዲሰጣቸው ማድረግ ይገባል። አሳማኝ አጣዳፊ ምክንያት ቢኖር እንኳን፣ ተነሺዎች ቤታቸውን መልሰው እስኪገነቡ ድረስ የሚቆዩበት/የሚሸጋገሩበት ተመጣጣኝ ቤት ወይም የኪራይ ግምት ሊሰጣቸው፣ እንዲሁም የመንግሥት ቤት ተከራዮች መሠረተ ልማት የተሟላለት ቤት ሊሰጣቸው ይገባል። 

  • የልማት ተነሺዎች ቅሬታ የማቅረቢያ መንገዶች እና አማራጮች እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ሁሉንም ውሳኔዎች በጽሑፍ ደብዳቤ ማሳወቅ። ይህ ቅሬታ ያላቸው መከራከሪያ በእጃቸው እንዲኖር ማድረግ እና ተነሺዎች መብቶቻቸውን ለማስከበር የሙስናን መንገድ መዝጋት ይገባል። 

  • ለልማት ተነሺዎች ከቀዬያቸው ሳይርቁ የሚሰፍሩበትን ቦታ እና ቤት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባል።

  • የልማት ተነሺዎች የሚዘዋወሩበት ቦታ በቅድሚያ እንደ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ እና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

12 አስተያየቶች:

  1. ሚዛናዊ ምልከታ ።!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. Thanks for sharing your insights, Great 👍

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  3. በጣም ትኩረት የተነፈገው ጉዳይ ነበር፣

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  4. Well said. I, too, am a victim of this project. One thing that urgently needs to be acknowledged is how Woreda and Subcity officials continue to burden the remaining residents. People are constantly being told to “do this,” “paint that,” contribute money for so-called neighbourhood development, or else face threats of eviction.

    Citizens are exhausted by the endless, ever-changing demands.... repainting their houses over and over, installing unnecessary wall-washing lights, and spending money they do not have on cosmetic changes that do nothing to improve their actual quality of life. None of this benefits the people who are already struggling to remain in their homes.

    What we are witnessing with the corridor project in Addis Ababa is not development rooted in community wellbeing, but pressure, intimidation, and performative beautification at the expense of citizens’ dignity. The lived experience of residents... the fear, the financial strain, the uncertainty.... is being ignored.

    Addis Ababa’s citizens need to wake up, speak up, and stand firmly for their rights. Development should empower people, not punish them. It’s time to question who this “beautification” is really for, and why the human cost is being overlooked.

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  5. ሚዛናዊና ወቅታዊ ግምገማ ነው። ሰሚ ከተገኘ የሁሉንም ጥቅም በሚዛናዊነት የሚያስጠብቅ ለተሻለ ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ የሚያነሳሳ። ነገር ግን ይህ ፅሁፍ በበጎ ስለመታየቱና ምክሩ ተቀባይነት ስለማግኘቱ እጡራጠራለሁ።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  6. በፍቄ ሚዛናዊ እይታ ነው። እናመሰግናለን። ፈረሳው የአዋጁን ድንጋጌዎችና ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትን በንብረትህ ላይ ያለን ጥበቃ የማግኘት መርህ የጣሰ እንደሆነ የሚታይ ነው። ሌላው ብታካትተው መልካም የነበረው ፈረሳው ግልጽነት ስላልነበረው ግለሰቦች የኛ አይ ፈር ስም ብለው ከፍተኛ ወጭ በማውጣት እድሳት አድርገው ወራት ሳይቆይ የፈረሰባቸው ግለሰቦች ነው። የነበራቸውን ጥሪት ያለአግባብ በቂ መረጃ ባለመሰጠቱ ብቻ እንዲባክን ሆነዋል።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  7. ስለ ፅሁፍህ እና ምልከታህ አመሰግናለው ሆኖም ግን ችግር ውስጥ የገባው(ያለው) አሁን በፈረሱት ሰፈሮቾ ውስጥ በዝቅተኛ የኪራይ ክፍያ ይኖር የነበረው ማህረሰብ አላካተተም የፈረሳው በትር እዛ አከባቢ ክፉኛ ነው ያረፈው

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  8. በፍቄ ወኔህም ብእርህም አይንጠፉ። ይህ የሁሉም ሰፈር ተመሳሳይ እጣና ታሪክ ነው። በመግቢያህ ላይ ያስቀመጥከው disclaimer እንዳለ ሆኖ በሰፊው የረሳኸው/ ያላካተትከው የሙስና ጉዳይ አለ። የምትክ ቦታውን ለመውሰድ አዲስ አበባ መሬት አስተዳደር ያለ ሙስና አብዛኛው ሰው የተቀበለውን ካሳ ከ30-70 በመቶ በጉቦ መልክ ከፍሏል። እኔ ለምሳሌ መጀመሪያ የተመራሁበት ለሚ ኩራ ገደል በመሆኑና በቤቴም ታማሚ ስላለኝ የተሻለ ቦታ እንዲቀየርልኝ ጥያቄ አቅርቤ በሃላፊዎቹ የቦታው ቅያሪ ፀድቆልኝ ቦታውን በሚያዘጋጁት ባለሞያዎች 2 ሚሊዮን ተጠይቄ አልከፍልም በማለቴ ታህሳስ ላይ የተነሳሁ እሰካሁን ምትክ ቦታውን አልተቀበልኩኝም። ይህ እንግዲህ በሃላፊዎችም ደረጃ መፍትሄ ያልተሰጠው ጉዳይ ነው። እንደኔ አይነት ብዙ ስላሉ ተጨማሪ መፃፍ ከፈለክ ለም ሆቴል ያለው አ.አ መሬት አስተዳደር ብቅ በል።
    በድጋሚ የፃፉ እጆችህ ይባረኩ!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  9. ተባረክ ... ሁሉንም ሳይድ የያዘ ሪፖርት ነው .. የገረመኝ .. መንግስቱ ከደሀ ላይ በወረሳቸው የትርፍ ቤቶች በወር አስር ብር እየከፈሉ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የራሳቸው ያልሆነ ከምስኪን ደሀ በጉልበት ተዘርፎ ተሰጥቷቸው ይኖሩ የነበሩ .. (አጭበርባሪ ብላቸው ደስ ይለኛል )..እነሱም ቤት ፈረሰብን ካሳ ካልተከፈለን ብለው ሲያማርሩ ስሰማ ለቤቱ ባለቤቶች ለተነጠቁት አዝናለሁ .. መንግስቱ ሀይለማርያምንም እረግማለሁ ... የታባቱ በሰው ሀገር እየተንጦለጦለ ሚኖረው ከደሀ ገፎ ለማይገባቸው ምስጋና ለሌላቸው ከየትም ተለቃቅመው ለመጡ ሰዎች ስለሰጠባቸው ነው .. አብቹ እንዳውም የዋህ ነው የማይገባቸውን ካሳ እና ኮንደሚንየም ሰጥቷቸዋል ..

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  10. በጣም የሚገርም እና ያልተንሸዋረረ እንዲሁም ቅንነት ያለበት እጅግ ጠቃሚ ምልከታ ነው የሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት ግብዝነት ካልያዘው በእጅጉ የሚጠቀምበት እና አካሄዱን የሚያስተካክልበት ነው ብዬ አምናለሁ እግዚአብሔር ይስጥህ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

በልማት ተነሺዎቹ ዓይን የኮሪደር ልማቱ ያበለፅጋል ወይስ ያደኸያል?

“እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ፣ እህሌ የሚደርሰው ለፍልሰታ” (በፍቃዱ ኃይሉ)  For English, click here . የኮሪደር ልማቱ በተለይ የመሐል አዲስ አበባን ገጽታ እስከወዲያኛው እየቀየረው ነው። ለአቅመ ማስተዋል ከደረ...