ከቅርብ ግዜ ወዲህ ፌስቡክ የወቅቱን ጨቋኝ ሕወሓትን ጥሎ የቀድሞዎቹን ጨቋኞች እነ ምኒልክን አንስቷል፡፡ ነገርዬው ሲተቹት በመሣሪያ መልስ ከሚሰጥ አካል ጋር ከመታገል፣ በሕይወት ከሌሉት ወይም ቀጥተኛ ተወካይ የሌላቸው ላይ መዘባበት ይሻላል በሚል ይሁን ወይም የጥያቄው አሳሳቢነት ስር ሰዶ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም፡፡ በታሪካዊ ጭቆናዎች ትርክቶች ውስጥ ‹አንዱ በማፍረስ፣ አንዱ በመካብ፣ ሌላው ደግሞ በመገላገል› ሁሉም የያቅሙን የሞት ሽረት እያደረገ ነው፡፡
እነ አብይ አቶምሳ ‹‹የታሪክ ኢ-ፍትሐዊነት ላይ መተማመኛ ላይ
ሳንደርስ ወደፊት ንቅንቅ የለም› ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ ትላንትና ዛሬ ደግሞ የኔም ወዳጆች በያዝ ለቀቅ የከረመውን ‹‹የይቅርታ ጉዳይ››
ቀለል አርገውም ቢሆን አንስተውታል፡፡ ናትናኤል ፈለቀ ‹‹የአባት ሀብት ወይም ዕዳ ለልጅ እንደሚተላለፍ ሁሉ የአባት ትውልድ በደል
ለልጅ ትውልድ ይተላለፋልና፣ የበዳይ አባት ልጅ ትውልድ የተበዳይ አባት ልጅ ትውልድን ይቅር ቢል ምን አለበት?›› የሚመስል አማራጭ
የመፍትሔ ጥያቄ
ጠቁሟል፡፡ ማሕሌት ፋንታሁን ደግሞ ‹‹ነገሩን የተበዳይ ቦታ ሆኜ ብሆን ብዬ ሳስበው ከዚህ ትውልድም ቢሆን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ››
የሚል ጭብጥ ያለው የራሷን የይቅርታ መልዕክት
አስነብባናለች፡፡
በኔ አመለካከት የጓደኖቼ ሐሳብ ለውይይቱ
ጥሩ መንገድ ቢጠርግም፣ ይቅርታ መጠየቅ እና ምሕረት ማግኘት በአገራችን የብሔር ጭቆና ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ግለሰቦች
‹‹ይቅር ለእግዜር›› የሚፈታ አይመስለኝም፡፡ በጭቆናው ጥልቀት እና አተረጓጎም ላይ እንኳን ገና መግባባት ላይ አልደረስንም፡፡
ስለሆነም እነዚህን መጠየቅ ይቀድማል ባይ ነኝ፤
- ይቅርታ የሚጠያየቁት አካላት (የሚጠይቀው እና የሚጠየቀው) እነማን ናቸው?
- ይቅርታ የሚጠየቅበት በደልስ የትኛው ነው?
- ይቅርታ የሚጠየቀውስ እንዴት ነው?
- ይቅርታው ያለካሣ ምሕረት ያገኛል ወይ?
- ምሕረት የሚያስገኘው የካሣ ዓይነትስ ምንድን ነው?
ብዙ የአማራ ልሒቃን የነበረው የማስገበር
ሒደት አገር የማስፋት ነው እንጂ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት ለማጥፋት የተደረገ ነገር የለም፡፡ የአማራውም የኦሮሞውም ገበሬ በነገሥታቱ
ዕኩል ሲገብር፣ ሲዘረፍ እና ሲበደል ነው የኖረው ይላሉ፡፡ የኦሮሞ ልሒቃንም በበኩላቸው በሕዝባችን ላይ የደረሰው ‹የቅኝ አገዛዝ
እንጂ ተራ ጭቆና አይደለም› ከሚሉት (ሌንጮ ለታ) አንስቶ ‹የነዳግማዊ ምኒልክ የማስገበር እርምጃ ነበር፤ አገር በዚያ መንገድ
ነው የሚገነባው ቢሆንም የኦሮሞን ማንነት ግን ማጥፋቱ ፍትሐዊ አልነበረም… አሁንም ሒደቱ አልቆመም፡፡› እስከሚሉት (አቶ ቡልቻ
ደመቅሳ) እንዲሁም ‹በኦሮሚያ የማንነት ጭቆናዎች ቢኖሩም የመደብ ጭቆናውን ያክል የከፋ አልነበረም፤ የኦሮሞ ባላባቶችም የኦሮሞ
ሕዝብን በድለዋል› እስከሚሉት (ዶ/ር መረራ ጉዲና) እና ሌሎችም በከፊል የሚገናኙ እና በተለይ በአማራጭ መፍትሔዎቻቸው የሚለያዩ
ማለትም ‹መገንጠል ነው መፍትሔው› በሚሉና ‹የለም ከሌሎች ጋር አብሮ በዕኩልነት ራስን ማስተዳደር› ይሻላል የሚሉ የተለያዩ አተረጓጎሞች
አሉበት፡፡
ይቅርታ የመጠያየቅ አጀንዳ ሲመጣ በላይኛው
አንቀጽ መሠረት አማራ በዳይ፣ ኦሮሞ ተበዳይ ለማለት የሚያስችሉ በርካታ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልገናል፡፡ የአማራ ባላባቶች (ወይም
አማርኛ ተናጋሪዎች ማለትም ይቻላል - ምክንያቱም በተለይ የሸዋ ኦሮሞዎች የሚገባቸውን
ያክል እንኳን ባይሆን በሥልጣኑ ውስጥ ቦታ ነበራቸው) በማስፋፋት፣ በነፍጠኝነት (ማለትም በኦሮሞ አካባቢዎች በነፍጥ ኃይል በመስፈር
እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ጭሰኛ በማድረግ) ለሠሩት በደል አማራ በጥቅሉ ተጠያቂ መሆን ይችላል ወይ? በወቅቱ ‹‹የጨዋው ልጅ አምስት
መቶም አንሞላ›› የሚሉ ባላባቶች በነበሩበት ዘመን ብዙኃኑ የአማራ ተወላጅስ ቢሆን በጭሰኝነት እየገበረ የሚኖር ተጨቋኝ አልነበረም
ወይ? ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ መብት አራማጆች የሚያነሱት ወሳኝ መሟገቻ ‹የአማራ ብዙኃን ቢያንስ ማንነቱ አደጋ ላይ አልወደቀም፣
ይልቁንም ተስፋፍቶለት አሁንም ድረስ ስር ለሰደደው ተጠቃሚነት አብቅቶታል› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ብዙኃኑ ተበዳይ በነበረበት
ስርዓት ውስጥ በቋንቋ የሚመስሉት ሰዎች በደል በማድረሳቸው የእነርሱን በደል ተንተርሶ ይቅርታ መጠየቅ አለበት የሚለው ውኃ የማያነሳ
መከራከሪያ ሊሆን ይችላል - አንዳንዶች ግን ‹‹ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ሲባል ምን አለበት?›› ባዮች ናቸው፡፡
‹ይቅርታ ይጠየቅ - ጠያቂም አይጎዳም፣ ምሕረት አድራጊም
አይከስርም› ቢባል ደግሞ ማነው የሚጠየቀው - በጥቅሉ የኦሮሞ ሕዝብ (እና ሌሎችም የደቡብ አካባቢዎች መኖራቸው እንዳይዘነጋ) ቢባል
ማነው የሚጠይቅው - የአማራ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ ወካይ ፓርቲ (አለው?)፣ ክልላዊ መንግሥቱ (የያኔውን መንግሥት የመወከል ቅቡልነት
አለው?) በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡፡ ይቅርታ የሚጠየቅበት በደልስ የትኛው ነው፣ የመስፋፋቱ ነው? በጭሰኝነትና ማስገበሩ
ነው? ‹‹በቅኝ አገዛዙ ነው››? ወይስ አገር በቀሉን ስርዓት (እንበል ‹‹ገዳ››ን) በመተካቱ ነው?
ይቅርታው ተሳክቶ ተጠያየቁ እንበልና ከዚያ በኋላ የሚመጣው
ምንድን ነው? ሁሉም ባለበት ይረጋል ወይስ እንደአዲስ ዕቅድ ማውጣት እንጀምራለን፡፡ ለደረሰው በደልስ ካሣው ምንድን ነው?
ሕወሓት ሕገመንግሥቱ በራሱ በደሉን ሽሮ ወደአዲስ ምዕራፍ
ተሸጋግረናል ባይ ነው፡፡ በሕገመንግሥቱ የተገኘው ነገር የብሔር ፌዴራሊዝሙ ነው፡፡ ፌዴራሊዝሙ ተበዳይ ብሔረሰቦች ያለፈው በደላቸው
ባይካሥም እንደአዲስ ግን ራሳቸውን በራሳቸው መገንባት የሚችሉበትን ዕድል ይሰጣቸዋል ተብሎ ታምኗል፡፡ ሆኖም አሁንም የብሔር ጭቆናው
ቀጥሏል ብለው የሚያምኑ ልሒቃን አሉ፡፡ በተለይ የኦሮምኛ ቋንቋ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት፤ ራስን በራስ የማስተዳደሩ
ሚናም በእውነተኛ የኦሮሚያ ወኪሎች እንጂ በእጅ አዙር በሚገዙ ወኪሎች መሆን የለበትም የሚሉ (ይህ እንደተመልካቹ የሚለያይ እውነት
ይሆናል) እና ከዚያም ባለፈ ደግሞ የተቀማነው ‹‹ነጻነት›› (ወይም ራስን የቻለ አገርነት) ካልተመለሰ ጭቆናው ቀጥሏል የሚሉም
አሉ፡፡ ካሣው እንደየልሒቁ ይለያያል ማለት ነው፡፡ ምሕረቱም ምሕረት ላይሆን ይችላል፡፡
No comments:
Post a Comment