በፍቃዱ
ኃይሉ
፩. Independence, Freedom, Liberty (ነጻነት የቱ ነው? የቱስ አይደለም?)
"ነጻነት ውስብስብ ነው" ብዬ ልጀምር። ‘ነጻነት’ የሚለውን የአማርኛ ቃል በተለምዶ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ሦስቱንም የእንግሊዝኛ ቃላት ለመተርጎም እንጠቀምበታለን። ትርጉሙ ግን ሁሌም አጥጋቢ አይሆንም።
ቃላት ባብዛኛው ደረቅ አይደሉም ፅንሰ-ሐሳብ (concept) ያዝላሉ። የሆነ ፅንሰ-ሐሳብን የሚወክሉ ቃላቶች በሆነ ቋንቋ ውስጥ የሉም ማለት የዚያ ፅንሰ-ሐሳብ በቋንቋው ተናጋሪው ማኅበረሰብ ዘንድ እምብዛም አይታወቅም እንደ ማለት ነው። ፅንሰ-ሐሳቡን በቃላት ቀንብቦ ማስቀመጥ መቻልና ብዙኃን በየ’ለት ንግራቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ መቻል ቃሉን ከነፅንሰ-ሐሳቡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ማስረፅ ማለት ነው። ይህንን ለማስረዳት ቀላሉ መንገድ የአየር ሁኔታን መግለጽ ነው። በረዶ (Ice) እና snow (የበረዶ ብናኝ እንበለው) ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ በአማርኛ ግን የሚጠሩት በአንድ ሥም - በረዶ - ተብለው ነው። Frost (snow ወይም የበረዶ ብናኝ የለበሰ ተራራ) አመዳይ ይባላል። በአገራችን የሌለ በመሆኑ ሥሙ የውሰት እና እምብዛም የማይታወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ (መዝ 147: 16) ከመገኘቱ በቀር ቃሉም፣ ሐሳቡም በማኅበረሰቦቻችን ዘንድ የሌለ ነገር ነው። Tornado የሚለው ቃል የአማርኛ አቻ የለውም፤ ምክንያቱም በሐሳብ ደረጃም እምብዛም አይታወቅም። ሩቅ ምሥራቃውያን በየጊዜው ለሚያጠቃቸው የነፋስ እና የማዕበል ዓይነት (ነፋስን ከነፋስ፣ ማዕበልን ከማዕበል) የሚለዩባቸው እልፍ ቃላት አሏቸው። የቃላት እና ሐሳብ ቁርኝት እንዲህ ይገለጻል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ነጻነት’ የሚለው ቃል እና ፅንሰ-ሐሳብ በአማርኛ ተናጋሪው ዘንድ እንዴት ነው እየታየ ያለው? መነባንቡ (rhetoric) ብቻ ነው ወይስ ግንዛቤውም አብሮት አለ? አብረን እንፈትሽ።
ምሳሌ ፩፦
A)
Ethiopia is an independent country.
B) Zone 9 is an independent blogosphere.
C) She is an independent woman.
B) Zone 9 is an independent blogosphere.
C) She is an independent woman.
በሚሉት ሦስት ዓ/ነገሮች ውስጥ ‘independent’ የሚለው ቃል ሦስት ተለምዷዊ ትርጉሞች አሉት፣
ሀ) ኢትዮጵያ "ነጻ" አገር ናት።
ለ) ዞን ፱ “ነጻ” የጡመራ መድረክ ነው።
ቨ) እሷ “ነጻ” ሴት ናት።
ለ) ዞን ፱ “ነጻ” የጡመራ መድረክ ነው።
ቨ) እሷ “ነጻ” ሴት ናት።
ሦስቱ ቃላቶች በዐውድ (context) የተለያዩ ቢመስሉም በመሠረታቸው አንድ ናቸው። ሁሉም፣ “ማንም ላይ ጥገኛ ያልሆነ/ች” ወይም “ራሱ/ሷን የቻለ/ች” የሚለውን ሐሳብ ያዘሉ ናቸው። ነገርዬው በራስ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ወይም በሌሎች ጉዳይ ላይ አቋም ለመያዝ የማንም ተፅዕኖ የሌለበት እንደማለት ነው። መቶ በመቶ ራስን መቻል ወይም ከሌሎች ተፅዕኖ መላቀቅ የሚባል ነገር አለ ብዬ ባላምንም የሌሎችን በራስ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት በእጅጉ መቀነስ መቻልን “ራስን መቻል” ብለን ብንጠራው አይከፋኝም። በላይኞቹ ምሳሌዎች ላይ ‘independence’ ራስን መቻል ወይም ገለልተኛ የሚሉት ቃላቶች ሊተኩት ይችላሉ።