(በበፍቃዱ ዘ. ኃይሉ)
ዐቢይ አሕመድ ተቃዋሚ መስለው፣ ተቃዋሚ ለብሰው ሥልጣን ከተቆናጠጡ እነኾ ዛሬ ድፍን ስምንት ዓመታቸው።
ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወዲህ በየሁለት ዓመቱ አስተዳደራቸውን የሚገመግም መጣጥፍ እየጻፍኩ ነው። ዘንድሮም ባሕሉን ለማስቀጠል ይህንን መጣጥፍ እነኾ ብያለሁ። በቅድሚያ የቀደምት ጽሑፎቼን ዐውድና ምላሽ በጨረፍታ ላስታውሳችሁ።
ዐቢይ አሕመድ በሥልጣን ጎዳና ሁለት ዓመት ሲሞላቸው በጻፍኩት ጽሑፍ ሃይማኖታዊ ሰበካን ከአነቃቂ ንግግር ጋር በሚቀይጥ የንግግር ዘይቤያቸው አታላይ አንደበት አባታዊ (paternalistic) አገዛዝ ስርዓት እንደገነቡ ለመከራከር ሞክሬ ነበር፤ ክርክሬ መንግሥታቸው እኛን ዜጎቹን ልክ በራሳቸው መወሰን የማይችሉ ሕፃናት ይመለከተናል የሚል ነበር። ይህንን ጽሑፍ በጻፍኩበት ወቅት ዐቢይ አሕመድ በመሐል አገር ከፍተኛ ድጋፍ ስለነበራቸው፣ ምንም እንኳን ትችቴ የመረረ ሊባል የሚችል ዓይነት ባይሆንም እንዲህ ያለ ትችት ከመሐል አገር ሰው ጭራሹኑ አልተለመደም ነበርና ከአንዳንድ ወዳጆቼም ሳይቀር ብዙ ነቀፌታዎችን አስከትሎብኝ ነበር።
አራት ዓመት ሲሞላቸው የጻፍኩት ግን በተቃራኒው የመረረ ትችት ሊባል የሚችል ነበር። “ከድጡ ወደ ማጡ” የሚል ርዕስ የሰጠኹት ሲሆን፣ መጀመሪያ በፍትሕ መጽሔት ላይ የሽፋን ገጽ ታሪክ (cover-story) ሆኖ ታትሟል። ከዚያም በብዙ ዩቱብ ገጾች ተባዝቷል። በወቅቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የገባችበት ነበር። የእርሳቸውን አራት ዓመታት ስገመግመው፣ ዐቢይ አሕመድ የብልፅግና ፓርቲ ብቸኛ ሰው መኾንን “ፓርቲው ራሳችው ናቸው” በሚል በመግለጽ - ወደ ፈላጭ ቆራጭነት ማደጋቸውን፣ ትግራይ ከኢትዮጵያ ወደ መሰናበት እያመራች መሆኗን፣ ኦሮሚያ አኬልዳማ ሊያስብላት የሚያስችል በታጣቂዎችና መንግሥት መሐል የተያዘ ሕዝብ መኖሩን፣ እና የሕግ የበላይነት መንኳሰስ እና የነውጠኝነትን መንሰራፋት (እንዲሁም የእርሳቸውን አመራር “የነውጥ ቀዛፊነት” በሚል) ጠቅሼ - ለዚህ ሁሉ ዋናው ተጠያቂው እርሳቸው መሆናቸውን ደምድሜ ጻፍኩ። ይህን ጊዜ ብዙ ወዳጆቼ “ክክፉ ይጠብቅህ” ከማለት በቀር ከድምዳሜዬ እምብዛም የተለየ ድምዳሜ አልነበራቸውም።
ስድስት ዓመት ሲሞላቸው “እየሰጡ መንሳት” የዐቢይ አሕመድ የአመራር ዘይቤ ነው የሚል ትንታኔ ጻፍኩ። በስድስት ዓመታት አስተውሎቴ፣ ዐቢይ አሕመድ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና እንቅስቃሴያቸው የታሰሩ ሰዎችን ሲፈቱ አይተናል፤ መልሰው ደግሞ የርሳቸውን ፖለቲካ የሚቃወሙ ሰዎችን በየሰበብ አስባቡ በመንግሥታቸው ሲያሳስሩ አይተናል። ብዙኃንን ያስፈነደቁ የሰላም ስምምነቶች ውስጥ ሲገቡ አይተናል (ኤርትራ፣ ትግራይ)፤ እነዚያ የሰላም ሥምምነቶች መልሰው ውኃ ሲበላቸው አይተናል። እነዚህ እና መሰል የአመራር ዘዬአቸው መገለጫ - እየሰጡ መንሳት - ሊባል እንደሚገባ ትንታኔዬን አቅርቤያለሁ። ይሄም ጽሑፍ በመጠኑ አንባቢ አግኝቷል። ተባዝቷልም።
ዐቢይ አሕመድ አሁንም ገና እየተገለጡ ነው። ትንታኔያችንም ይቀጥላል።
“Lost in Transition” ባሰኘሁት መጽሓፌ ውስጥም የዐቢይ አሕመድ አነሳስ (The Rise of Abiy Ahmed) በሚል ርዕስ የ18 ገጽ ትንታኔ አስቀምጫለሁ። በዚህ ትንታኔዬ ዐቢይ በምን ዓይነት ውስጣዊ እና ውጪያዊ ትግሎች ወደ ከፍተኛው የሥልጣን ማማ እንደተወጣጡ ለመተንተን ሞክሬያለሁ። ዐቢይ አሕመድ በብዕር ሥም ያሳተሙትን “እርካብና መንበር” አንብቤያለሁ። በሥማቸው ያሳተሟቸውን “የመደመር” ተከታታይ መጽሓፎችንም አንብቤያለሁ። ቶም ጋርድነር “The Abiy Project” በሚል ርዕስ የጻፈውን ባለ ትልቅ ጥራዝ መጽሓፍም አንብቤያለሁ። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እየሰበሰቡ የሚያደርጓቸውን ንግግሮችም እያሳደድኩ፣ ጊዜ በፈቀደልኝ ቁጥር ላደምጣቸው ሞክሬያለሁ። በነዚህ ሁሉ ንባቦቼ የተረዳሁት ዐቢይ አሕመድ የፈለጉትን ከማድረግ ምንም የማያስቆማቸው ሰው መሆናቸውን ነው ማለት እችላለሁ። ከዚህ በታች የምጽፈው እና ከዚህ ውጪም የምሰጣቸው አስተያየቶች በነዚህ ጥረቶቼ የወሰድኳቸው ግምገማዎቼ መሆናቸውን ቀድሜ ለማሳወቅ እወዳለሁ።
ከ“ቲም ለማ” ወደ “መጋቢታውያን”
ለውጡን ስታስቡ ከ"ቲም ለማ" ውጪ ማሰብ ትችላላችሁ? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ይችላሉ። “የመደመር መንገድ” የሚለው መጽሐፋቸው ስለለውጡ አመጣጥ የሚተነትን ነው። ዐቢይ ለውጡን ለማምጣት የዐሥር ዓመት ሴራ እንደተሠራ ይናገራሉ። አምናቸዋለሁ። ከባድ ሚዛን “የሸዋ ፖለቲካ” ተጫዋች ናቸው። በአንድ እግራቸው ከገዢው ፓርቲ መንደር፣ በሌላ እግራቸው ከተቃዋሚዎች መንደር ቆመው ነው ጨዋታውን የተጫወቱት፤ ለዚህ ነው መግቢያዬ ላይ “ተቃዋሚ መስለው፣ ተቃዋሚ ለብሰው” የሚል ገለጻ የተጠቀምኩት። እንደ እርሳቸው አባባል እኛ “አሮማራ” የምንለው ሕወሓትን ለመገርሰስ የተፀነሰው ትብብር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ ራሺያ ሲጓዝ በዐቢይ እና ደመቀ የተጠነሰሰ ሴራ ነው። ስለዚህ ለለውጡ፣ የለማ መገርሳ ሚና እምብዛም እንዳልነበር እንደዋዛ ታልፏል። የመደመር መንገድ መጽሐፍ የለማን ስም አንድ ሁለቴ እንደዋዛ (anecdote) አንስቶ ነው የሚያልፈው። ይልቁንም መጽሓፉ ላይ ደመቀ መኮንን የተሻለ ተጠቅሰዋል። ዐቢይ፣ በዚህ መጽሐፍ ላይ “ቲም ለማ” የሚለውን የለውጥ ቡድን መጠሪያ ስም፥ “መጋቢታውያን” በሚል ሊተኩት ሞክረዋል። መጋቢት፣ እርሳቸው የተመረጡበት ወር ነው። በርግጥ ደመቀ መኮንን ከእጩነት ራሳቸውን ባልተጠበቀ መንገድ ባያገልሉ ኖሮ፣ ዐቢይ አሕመድ በሰፋ የድምፅ ብልጫ የማሸነፍ ዕድላቸው አጠያያቂ ይሆን ነበር፤ ስለዚህ የደመቀ መኮንንም መጠቀስ ትርጉም ይሰጣል። የለማ መገርሳ ግን እንደዋዛ ከታሪኩ መፋቅ በጣም አስገርሞኛል። ዐቢይ "ቲም ለማ" ከሚለው ይልቅ "መጋቢታውያን" የሚለውን መጠሪያ የወደዱት በለማ ስም መጠራቱ የእርሳችውን ሚና የሚያሳንስ ስለመሰላቸው ወይስ ከለማ መገርሳ ጋር መንገዳቸው ስለተለያየ?
