Friday, July 18, 2025

ሕጋዊ አፈና እንደገና፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ክለሳ ጉዳይ

(በፍቃዱ ኃይሉ)

[For English Click Here] ፍትሕ ሚኒስቴር በ2011 የፀደቀውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ለመከለስ ረቂቅ አውጥቶ የተመረጡ ባለድርሻ አካላትን እያወያየ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ በመጣ ማግስት የወጣው ይህ ሕግ፣ የቀድሞውን “አፋኝ” የተባለለትን አዋጅ የተካ ነበር። ይሁንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን ጨምሮ ሌሎችም በለውጡ ሰሞን የወጡት አዋጆች ቀስ በቀስ እየተከለሱ መሆኑ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። በዚህ አጭር መጣጥፍ፣ ከሕግ ማሻሻያ (legal reform) ወደ ኋላ እየተመለስንበት ያለውን አገራዊ ሒደት በወፍ በረር እቃኛለሁ። በተጨማሪም፣ የክለሳ ረቂቁን፣ ከአሁኑ አዋጅ እና ከተሻረው አዋጅ ጋር በንፅፅር በማቅረብ፣ አንባብያን ፍርዱን እንዲሰጡ ለማድረግ እሞክራለሁ።

መግቢያ

በ2010 የተቋቋመው የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ጉባዔ ደርዘን የሚሆኑ አፋኝ ሕጎችን፣ በበርካታ የባለሙያዎች ግብረ ኃይል ጥናቶች፣ በባለድርሻ አካላት ምክክር እና ይሁንታ ለመከለስ በቅቶ ነበር። የወቅቱ የፖለቲካ ለውጥ ትልቁ እርምጃም የነዚህ ሕጎች መሻሻል ነበር። ጉባዔው ከከለሳቸው ሕጎች ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ የሚዲያ እንዲሁም የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ይገኙበታል። እርግጥ ነው፣ የክለሳው መንገድ እንከን አልባ አልነበረም፤ ባለሙያዎቹ የነደፏቸው ረቂቆች መጀመሪያ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ቀጥሎም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተወሰኑ አንቀፆቻቸው ተቀይረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቁ ተደርጓል፤ እንደ “የመረጃ የማግኘት ነፃነት” ያሉ ረቂቆች ደግሞ ጭራሹኑ ሳይፀድቁ ቀርተዋል። ይሁንና በምክር ቤቱ ተረቅቀው የፀደቁት ሕጎች ግን የተሻለ ሕዝባዊ ቅቡልነት ነበራቸው። ይህ ወቅት የቀድሞውን በሕግ የመግዛት (rule by law) ወይም የሕጋዊ አፈና አካሔድ በሕግ የበላይነት (rule of law) ይተካዋል ተብሎ ታምኖ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ (የለውጡ መንግሥት ሥልጣኑን ማደላደል ሲጀምር (እና የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ሲገባ) በሕጉ መሻሻል ማንሰራራት የጀመረውን የሲቪክ ምኅዳር በሕገወጥ አካሔዱ መልሶ ያዳክመው ጀመር፤ ሕጎቹ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጣሱ ተመልክተናል። እንደ ምሳሌ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን ቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ቢደነገግም፣ ሕጉ በይፋ ተጥሶ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ተሾመው ነበር። በተመሳሳይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ድርጅትም ሕጋዊ አግባብነት የሌለውና ፖለቲካዊ መግፍዔ ያለው እግድ አምስት አገር በቀል ድርጅቶች ላይ አሳልፎ ነበር። አሁን ደግሞ ጉዳዩ ተባብሶ የተሻሻሉት ሕጎች በቅጡ ተፈትሸው፣ ውጤታቸው ሳይመዘን ለክለሳ ተዳርገዋል። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት የሚዲያ ሕጉ ክለሳ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጁ የክለሳ ረቂቅ ናቸው። የሚዲያ ሕጉ ክለሳ የአስፈፃሚውን አካል ሥልጣን በሚለጥጥ እና ምኅዳሩን በሚያቀጭጭ መልኩ መሆኑን ከዚህ በፊት ተግለጿል።

የሲቪል ማኅበረስቡ መገፋት ደረጃዎች

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መውጣት ብዙዎችን ያስደሰተ ነበር። ነገር ግን ግጭቶች እየተባባሱ ሲመጡ እና የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት መንግሥትን ለተጠያቂነት መጥራት ሲጀምሩ ግን መንግሥት ፊቱን አዙሮባቸዋል። በተለይ በትግራይ ጦርነት ወቅት ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለከፍተኛ ውክቢያ ተዳርገው ነበር። ውክቢያው ዓለም ዐቀፍ የተራድዖ ድርጅቶችንም የጨመረ ነበር። ከዚህም ጋር ሦስት ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ታግደው ነበር። በተመሳሳይ የሰላምና ልማት ማዕከል የተባለውም ተቋም ታግዶ መሪዎቹ ለተወሰነ ጊዜ ታስረው ነበር።

በኋላ ላይ የትግራይ ጦርነት በሰላም ድርድር ተፈትቶ፣ የአማራ ክልል ግጭት ካገረሸ በኋላ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ምዝገባ ባልተጠቀሰ ምክንያት አቁሞ ነበር። አልፎ ተርፎም፣ ነባር ድርጅቶች መተዳደሪያ ደንባቸውን ለማሻሻል ሲሞክሩ ከመብቶች እና ዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ ዓላማዎቻቸውን እንዲቀይሩ ቢሮክራሲያዊ ጫና ይደረግባቸው ነበር። የፀጥታ አካላት አባል ነን የሚሉ ግለሰቦች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አባላት እና አመራሮች ያዋክቡ ጀመር። በዚህም፣ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሪዎች እና አባላት ለስደት ተዳርገዋል

ይህ በእንዲህ እያለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሐምሌ ወር 2016 ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረጉት ጥያቄ እና መልስ የሰብዓዊ መብቶች አዋጅ፣ ተቋማት እና አሠራር መፈተሽ ያስፈልጋል ብለው ነበር። በዚህ ንግግራቸው፣ “እኛ ደሞዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ” ኃይል ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል አልነግራችሁም የሚል ጅምላ ፍረጃ አሳልፈው ነበር። ይህ ንግግራቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ያስደነገጠ ንግግር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ባሉ በወራት ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አምስት የሰብዓዊ መበቶች ተሟጋቾች ድርጅቶችን በሕዳር እና ታኅሣሥ ወር ላይ ፖለቲካዊ ምክንያት በመስጠት ሦስት እና አራት ወራት ታግደው እንዲቆዩ አድርጓል። እግዱ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አማላጅነት ቢነሳም፣ ከዚያ ወዲህ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ የፍርሐት ቆፈን ይዟቸው ሥራቸውን በነጻነት ለመሥራት ተቸግረዋል።

በስተመጨረሻም፣ ፍትሕ ሚኒስቴር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅ ለመከለስ ዝግጅቱን አጠናቅቆ የምክክር መድረኮችን እያመቻቸ ነው። ክለሳው፣ የሲቪክ ምኅዳሩን የሚያጣብብ ከመሆኑም ባሻገር፣ በአፋኝነቱ ከተሻረው ሕግ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ይህንን ለማሳየት፣ አራት ናሙናዎችን ወስጄ እንደሚከተለው ለንፅፅር አቅርባለሁ።

የአዋጆቹ ንፅፅር

1)    የትርጉም አሰጣጥ

ሀ) አፋኙ አዋጅ 621/2001፦ አራት ዓይነት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን (“የበጎ አድራጎት ድርጅት” በሚል) ይደነግጋል። እነዚህም “የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት” (ሁሉም አባላቱ የኢትዮጵያ ዜጎች የሆኑ እና 90 በመቶ ገቢውን ከአገር ውስጥ ምንጮች የሚያገኝ ድርጅት)፣ “የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት” (ሁሉም አባላቱ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ እና ከ10 በመቶ በላይ ገቢውን ከውጭ አገር ምንጮች የሚያገኝ ድርጅት)፣ “የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት” (በውጭ አገር ዜጎች ወይም በውጭ አገር የተቋቋመ ወይም ገቢውን ከውጭ የሚያገኝ ድርጅት) እና “ብዙኃን ማኅበራት” ናቸው።

     ይህ የትርጉም አሰጣጥ ለመብቶች ተሟጋች ድርጅቶችን የገቢ ምንጭ ለማድረቅ እና ለማግለያነት ውሏል። አዋጁ በጥቅሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን “የበጎ አድራጎት (charity) ድርጅት” በሚል ቋንቋ ይጠራቸው ነበር። ይህም ከዕርዳታ ሥራ በቀር ለሰብዓዊ መብቶች፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ ለግጭት አፈታት፣ የሕግ ሙግት (judicial advocacy) እና መሰል  አገልግሎቶች የሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጥ እና ተሟጋችነት (advocacy) ሥራዎችን ለመገደብ ውሏል። አዋጁ “የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት” ብሎ ከሚጠራቸው ድርጅቶች በቀር ሌሎች በተሟጋችነት (advocacy) ሥራ እንዳይሰማሩ ይከለክላል (አንቀፅ 14/5)። በዚህም ሳቢያ አብዛኛዎቹ የሰብዓዊ መበቶች ተሟጋች ድርጅቶች ከስመዋል፤ የቀሩትም ክፉኛ ተዳክመው ነበር።

ለ) የተሻሻለው አዋጅ 1113/2011) የተሻሻለው አዋጅ 1331/2011፦ ሁሉንም ድርጅቶች በትክክል “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች” በሚል የጠራቸው ሲሆን፣ የድርጅቶቹ “አገር በቀል ድርጅት” (በኢትዮጵያውያን ወይም በኢትዮጵያ ነዋሪ የውጭ ዜጎች አገር ውስጥ የተቋቋመ ድርጅት)፣ “የውጭ ድርጅት” (በውጭ አገር ተቋቁሞ በኢትዮጵያ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ድርጅት)፣ “የበጎ አድራጎት ድርጅት” (ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ድርጅት)፣ “የሙያ ማኅበር” (ሙያን መሠረት አድርጎ የተቋቋመ ማኅበር)፣ እና “ኅብረት” (ሁለት እና ከሁለት በላይ የሆኑ ድርጅቶች ስብስብ እና የስብስቦች ስብስብ) ናቸው። ሁሉም ድርጅቶች ለዓላማቸው መሳካት ከየትኛውም ሕጋዊ ምንጭ ገቢ ማሰባሰብ የሚችሉ ሲሆን  (አንቀፅ 63/1/ሐ)፣ የተቋቋሙበትን ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት በየትኛውም ሕጋዊ የሥራ መስክ ላይ መሠማራት ይችላሉ (አንቀፅ 62/1)። ይህ አዋጅ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በመጠኑ እንዲነቃቁ ሕጋዊ መንገድ ጠርጎ ነበር።

ሐ) የተሻሻለውን አዋጅ ለመቀልበስ የወጣው ረቂቅ፦ የተሻሻለውን አዋጅ አንቀፅ 62/5 ተሰርዞ፣ “የውጭ ድርጅቶች” ወይም በውጭ አገር ዜጎች የተመሠረቱ “አገር በቀል ድርጅቶች” በኢትዮጵያ ዜጎች ለተመሠረቱ “አገር በቀል ድርጅቶች” ለተሟጋችነት (advocacy) ወይም ምርጫ ነክ ሥራዎች የገንዘብ ወይም የሙያ ድጋፍ እንዳይሰጡ ይከለክላል። በተጨማሪም፣ አንቀፅ 62/6 ተሰርዞ አገር በቀል ድርጅቶች ለፖለቲካ አድቮኬሲ ወይም ምርጫ ነክ ሥራዎች “ከውጭ  የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ ወይም ሃብት መቀበል አይችልም” ይላል። ይህ ረቂቅ እንደቀድሞ የድርጅቶቹን ብያኔ ባይቀይረውም፣ በዜጎች እና ዜጎች ባልሆኑ ነዋሪዎች የተመሠረቱ ድርጅቶችን ልክ እንደተሻረው አዋጅ ከፋፍሎ ተመልክቷቸዋል፤ በተጨማሪም፣ የተሻረው (621/2001) አዋጅ “የኢትዮጵያውያን ድርጅቶች” ለአድቮኬሲ ሥራ ከውጭ ገቢ ማሰባሰብ ይከለክል የነበረውን፣ ረቂቁ የውጭ ድርጅቶች እና ዜጎችን አገር ውስጥና በዜጎች ለተቋቋሙ ድርጅቶች እንዳይሰጡ በመከልከል (የአገር ውስጦቹም እንዳይቀበሉ በመከልከል) ድርብርብ ክልከላ በማስቀመጥ በአፋኝነቱ ምክንያት የተሻረውን አዋጅ አንቀፆች ከበፊቱ በከፋ መልኩ መልሶ ያመጣቸዋል።

2) የተቆጣጣሪው አካል ሥልጣን

ሀ) አፋኙ አዋጅ 621/2009፦ ተቆጣጣሪው አካል (የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ኤጀንሲ)፣ በመንግሥት የሚሾሙ ሰባት አባላት ባሉት ቦርድ ይመራል (አንቀፅ 8/1)። ይህም አስፈፃሚው የመንግሥት አካል በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ፍፁማዊ የበላይነት እንዲኖረው አድርጎ ነበር። በውጤቱም ሲቪክ ምኅዳሩ ሲጣበብ፣ ለተቆጣጣሪው አካል ሠራተኞች የሙሰኝነት መንገድ ጠርጎ ነበር።

ለ) የተሻሻለው አዋጅ 1113/2019፦ ተቆጣጣሪው አካል (የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን)፣ ሦስት በዐቃቤ ሕግ የሚሰየሙ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ ሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ አንድ በዐቃቤ ሕግ የሚሾም ባለሙያ፣ ሁለት የአካል ጉዳተኛ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ሁለት የሴቶች መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ተወካዮችን የያዘ 11 አባላት ባሉት ቦርድ ይመራል (አንቀፅ 8/1)። ይህ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ተቆርቋሪ የሆኑ አካላት ዘርፉን የመቆጣጠር ዕድል እንዲኖራቸው እና ከመንግሥት የአፈና እርምጃ እንዲከለሉ ለማድረግ ያስትችላል ተብሎ ታምኖበት ነበር።

ሐ) የተሻሻለውን አዋጅ ለመቀልበስ የወጣው ረቂቅ፦ ተቆጣጣሪው አካል በፍትሕ ሚኒስቴር የሚሰየሙ አራት የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የሚሰየም አንድ ባለሙያ፣ እና ሁለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ይኖሩታል። ይህ ክለሳ የተሻረውን አፋኝ ሕግ አሠራር መልሶ የሚያመጣ ነው።

3) ምዝገባ እና ፈቃድ

ሀ) አፋኙ አዋጅ 621/2009፦ ድርጅቶች በየዓመቱ የሥራ ክንውን እና የሒሳብ መግለጫ ሪፖርቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ፣ በየሦስት ዓመቱ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ ያስገድዳል (አንቀፅ 76/1)። ይህም በድርጅቶቹ ላይ አላስፈላጊ ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር አስፈፃሚው አካል (በተቆጣጣሪው አካል በኩል) የማይፈልጋቸውን ድርጅቶች ፈቃድ እንዳያድስ ዕድል ሰጥቶት ነበር።

ለ) የተሻሻለው አዋጅ 1113/2019፦ ፈቃድ ማሳደስ የሚለው አንቀፅ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል። ይህም በአስፈፃሚ አካል ሥልጣንን አላግባብ የመጠቀም ችግር በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል።

ሐ) የተሻሻለውን አዋጅ ለመቀልበስ የወጣው ረቂቅ፦ (አንቀፅ 70/3ን በመጨመር) ድርጅቶች በየዓመቱ የሥራ ክንውን እና የሒሳብ መግለጫ ሪፖርቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ፣ በየአራት ዓመቱ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ ያስገድዳል። ይህም የተሻረው አፋኝ ሕግ አሠራርን መልሶ በማምጣት ለአፈና እንዲሁም ለሙስና መንገድ ይጠርጋል።

4) እገዳ እና ስረዛ

ሀ) አፋኙ አዋጅ 621/2009፦ ማንኛውም ድርጅት የሕጉን ድንጋጌዎች መተላለፉ ከተረጋገጠ (አንቀፅ 74/2) እና በተቆጣጣሪው አካል ትዕዛዝ እርምት ሳያደርግ ከቀረ (አንቀፅ 92/1/ሀ) እና ሌሎችም ምክንያቶች ጉድለቶቹን እስኪያስተካክል ድረስ ፈቃዱ ሊታገድ ይችላል። በኤጀንሲው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ድርጅት ለቦርዱ ይግባኝ ማለት ይችላል (አንቀፅ 104/2)፣ በቦርዱ ውሳኔም ቅር ከተሰኘ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ይችላል (አንቀፅ 104/3)፣ በይግባኝ ክርክር ላይ ያለ ድርጅት ውሳኔ እስከሚያገኝ ያልተመዘገበው እንዳልተመዘገበ፣ የታገደ ወይም የተሰረዘ ድርጅት እንዳልታገደ ወይም እንዳልተሰረዘ የመቆጠር መብት አለው (አንቀፅ 104/4)። ይህ ድንጋጌ ምንም እንኳን የእግድ እና ስረዛ ሥልጣን ለኤጀንሲው አላግባብ ሰጥቶ ድርጅቶቹ ላይ አላስፈላጊ ጫና ቢያሳድርም፣ በየ15 ቀኑ መቅረብ የሚችል የይግባኝ ስርዓት መኖሩ እንደ መልካም ሊታይ ይችላል።

ለ) የተሻሻለው አዋጅ 1113/2019፦ ተቆጣጣሪው አካል “የምርመራ ሥራውን ሲያከናውን ከባድ የሕግ ጥሰት መፈፀሙን ሲያረጋግጥ እና በዚህም ምክንያት የድርጅቱን እንቅስቃሴ ማገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው” በባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ከሦስት ወር ያልበለጠ እግድ ድርጅቱ ላይ ሊጥል ይችላል። ሆኖም፣ ቦርዱ በሦስት ወር ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠበት እግዱ ይነሳል (አንቀፅ 77/4)። የታገደው ድርጅት በቦርዱ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማለት ዕድል አለው። ይህ አሠራር ምንም እንኳን በተግባር የተጣሰባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ በሕግ የበላይነት ለሚሠራ ስርዓት ለድርጅቶቹ በቂ የጥበቃ መንገድ ሰጥቷል፤ በተጨማሪም፣ የድርጅቶቹ እግድ መልስ እስኪያገኝ የሚቆይበት ጊዜ የተራዘመ መሆኑ ድርጅቶቹን አላስፈላጊ ጫና ውስጥ ይከታል። 

ሐ) የተሻሻለውን አዋጅ ለመቀልበስ የወጣው ረቂቅ፦ የአሁኑ አዋጅ በአንቀፅ 77/4 “አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያረጋግጥ” ይል የነበረውን “ሲያጋጥም” በሚል የሚተካው ሲሆን፣ የባልሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር “እስከ ሦስት ወር የሚደርስ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፎ ምርመራ ሊያደርግ ይችላል፤ ሆኖም ምርመራው በሦስት ወር የእግድ ጊዜ ውስጥ ካልተጠናቀቀ ቦርዱ እግዱን ለተጨማሪ ሦስት ወራት ሊያራዝመው ይችላል፤” ይላል። አልፎ ተርፎም፣ በአንቀፅ 77/5 ላይ “ቦርዱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል” በማለት ቀድሞ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት ይግባኝ ማቅረብ ይቻል የነበረውን ሰርዞታል። ይህ በአፋኝነቱ ከተሻረውም አዋጅ በላይ አፋኝ አሠራር ሲሆን፣ ድርጅቶቹ በምርመራ ሥም ባልተረጋገጠ ማስረጃ ለተራዘመ ጊዜ ታግደው እንዲቆዩ (እና በዚህ ሳቢያም እንዲፈርሱ) ለአስፈፃሚው አካል ዕድል ይሰጣል። ብሎም፣ መሠረታዊ የሆነውን ለፍርድ ቤት ይግባኝ የማለት መብት ይነፍጋል።

ከላይ በንፅፅር እንዳየነው፣ ረቂቅ አዋጁ በ2001 የፀደቀው እና አፋኝ ነው በሚል በ2011 የተሰረዘውን አዋጅ መንፈስ መልሶ ያመጣ ከመሆኑም ባሻገር አንዳንድ አንቀፆቹ አፋኝነቱ በብዙ ጥናቶች ከተረጋገጠው ከቀድሞ አዋጅም የከፋ አፋኝነት ባሕሪ የተላበሱ ናቸው።

መውጪያ

ሕጋዊ አፈና ነውጠኝነትን ያባብሳል!

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ማፈን ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደማያመጣ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታይቷል። ይልቁንም የነውጠኝነት ባሕል የበለጠ እንዲጎለብት መንገድ ይከፍታል። እንደሚታወሰው፣ ኢሕአዴግ በድኅረ ምርጫ 97 ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የሲቪክ ምኅዳሩን ማጥበብ ዋነኛዎቹ ነበሩ። መብት ተኮር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የገቢ ምንጫቸው እንዲጠብ፣ እንዲሁም የተቆጣጣሪው ሥልጣን እንዲበዛ በማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መንግሥትን የመታዘብ እና አምባገነናዊ ባሕል ሲያዳብር እንዲመለስ የመወትወት (advocacy) አቅም እንዳይኖራቸው ተደረጉ። ይህም፣ ብዙኃን ተቋማት መር ለውጥ እንዳይጠብቁ ስላደረገ አገር ዐቀፍ ተቃውሞዎች ተበራክተው ነበር፤ አንዳንዶቹ ተቃውሞዎች ነውጥ አዘል ንቅናቄዎችን ወልደዋል። አሁንም የሕጎቹ እና የአሠራሮቹ መከለስ የነውጥ አልባ መንገዶችን ሁሉ በመዝጋት፣ ነውጠኝነት እንዲስፋፋ እና በኢትዮጵያ የተንሰራፉት ግጭቶች እልባት እንዳያገኙ ያደርጋል።

ስለሆነም፣ መንግሥት እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት፣ ወደ ሕጋዊ አፈና የሚያሸጋግረንን ረቂቅ ሕግ ውድቅ እንዲያደርጉት ሕዝባዊ ግፊት ማድረግ ይገባል። ይልቁንም፣ የሲቪክ ምኅዳሩ እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ተጨማሪ ሕጋዊ ጥበቃ እና ከለላ እንዲኖራቸው የሚያስችል ሕግ በማርቀቅ ሕገ መንግሥታዊውን የመደራጀት መብት ማክበር እና ማስከበር ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን እና ለሰላምና መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ነው። 

No comments:

Post a Comment

The Return to Rule by Law: The Case of Draft CSO Law in Ethiopia

(Befekadu Hailu) [The original version of this piece is written in Amharic; please read the Amharic version for accuracy.] The Ministry...