(በፍቃዱ ኃይሉ)
"እውነቱን ለመናገር፣ ከፌሚኒዝም ታሪክ ጋር የምጋራቸውም ሆነ የማልስማማባቸው ነጥቦች አሉኝ፤ [ነገር ግን] የሌለኝን ማዕረግ ወስጄ ራሴን [ፌሚኒስት በሚል ሥም] ለማቆላመጥ አልፈልግም።" (የጀርመን የመጀመሪያዋ ሴት ቻንስለር አንጌላ መርኬል፣ እኤአ በ2017 በበርሊን Women20 Summit ላይ “ፌሚኒስት ነዎት ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ።)
"ያኔ ስናገረው ትንሽ እየፈራሁ ነበር። አሁን ግን በደንብ አስቤበታለሁ፤ በዚህ መልኩ ሲታይ ሁላችንም ፌሚኒስቶች መሆን አለብን ማለት እችላለሁ።" (አንጌላ መርኬል እኤአ በ2021 "ሁላችንም ፌሚኒስት መሆን አለብን" በሚለው ንግግሯ/መጽሐፏ የምትታወቀው ናይጄሪያዊት ቺማማንዳ አዲቼ የተሳተፈችበት መድረክ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ።)
ፌሚኒዝም በኢትዮጵያ ውስጥ መጠነ-ሰፊ ማኅበራዊ ተፅዕኖ ማሳደር የመጀመሩን ያክል፣ የተቀናጀ የሚመስል ፅኑ ተቃውሞ እና ፍረጃም እየገጠመው ነው።
ነገር ግን በፌሚኒዝም ላይ የሚሰነዘሩ ነቀፌታዎች አዲስም፣ አገር በቀልም አይደሉም። ንቅናቄው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ በየደረሰበት ማኅበረሰብ እና በየዘመኑ እየተፈተነ፣ እየወደቀና እየተነሳ እዚህ የደረሰ ኅያው ሞገድ ነው። እንዲያውም የሚገርመው፣ ፌሚኒዝምን በመተቸትና ድክመቱን በማጋለጥ ረገድ ከራሳቸው ከፌሚኒስቶቹ የከረረ ሂስ ያቀረበ ሌላ አካል የለም። የንቅናቄው ትልቁ ጥንካሬም ራሱን ከትችት በላይ አድርጎ ባለማኖሩ፣ ሁሌም ራሱን በመፈተሽ መታደስና ማደግ መቻሉ ነው።
ትርጉም፣ ሞገዶች እና የንድፈ-ሐሳብ ልዩነቶች
ፊሚኒስቶች ሁሉ አንድ ዓይነት የችግር አረዳድ፣ የመፍትሔ መንገድ እና የውጤት ዒላማ የላቸውም። ለዚህም ነው አንዳንድ ፌሚኒስቶች “ሊበራል ፊሚኒስት”፣ “ማርክሲስት ፌሚኒስት”፣ “ኢንተርሴክሽናል ፌሚኒስት”፣ “ክርስቲያን/ሙስሊም ፌሚኒስት” ሲሉ የምንሰማቸው። አንዳንዶቹ በአባውራ የሚመራው ቤተሰብ “የጭቆና መሸሸጊያ ነውና ይፍረስ” (abolitionists) ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ “የለም፣ ይታደስ” (reformists) ይላሉ።
ፌሚኒዝም አንድ እና ወጥ የሆነ፣ ሁሉን አስማሚ ትርጉም የለውም ቢባል የተጋነነ አይደለም። ገና ከጥንቱ ከጠዋቱ፣ ሬቤካ ዌስት የተባለች እንግሊዛዊት ፌሚኒስት ጸሐፊ እኤአ በ1913 “እኔ ራሴ ፌሚኒዝም በትክክል ምን እንደሆነ ለማወቅ አልቻልኩም” ስትል ጽፋ ነበር፤ ሆኖም፣ “እኔ የማውቀው ከጫማ መጥረጊያ ምንጣፍ እና ከሴተኛ አዳሪ የሚለዩኝን ነገሮች ስናገር ሰዎች 'ፌሚኒስት እያሉ እንደሚጠሩኝ ብቻ ነው” ብላለች። ይህ ማለት ግን ፌሚኒስቶች በሙሉ የሚስማሙባቸው ነገሮች የሉም ማለት አይደለም። ሁሉም ፌሚኒስቶች ዓለማችን ‘ፓትሪያሪካል’ (በተባዕታዊ ላዕላይነት) የሚመራ ሥርዓተ ማኅበር እንደምትመራ፣ በእየርከኑ ያሉ ወንዶች እና ሴቶች መካከል የመብቶች እና የዕድሎች መበላለጥ እንዳለ ከሞላ ጎደል ይስማማሉ።
በሬቤካ ዌስት ዘመን ፌሚኒዝም ባመዛኙ የሕጋዊ እኩልነት (የመምረጥ/የመመረጥ መብት፣ የንብረት ባለቤትነት መብት፣ የጋብቻ እኩልነት መብት፣ ወዘተ.) ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበር። ይህንን ኋላ የመጡ ምሁራን “የመጀመሪያው የፌሚኒዝም ሞገድ” ይሉታል። ከዚያ ለአርባ ዓመት ያክል ተቀዛቅዞ የቆየው የፌሚኒዝም ንቅናቄ በ1960ዎቹ በድጋሚ አንሰራርቷል። ይህንኛው ደግሞ “ሁለተኛው የፊሚኒዝም ሞገድ” ተብሎ ተሰይሟል። በዚህ ጊዜ ሴቶች ለማኅበራዊ እኩልነት እና ውሳኔ ሰጭነት (የሥራ ቦታ እኩልነት፣ ለሥነ ተዋልዶ መብቶች፣ እና የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ለማስቆም ለመሳሰሉት) ታግለዋል።
ሁለተኛውን የፌሚኒዝም ሞገድ “የግላችን ጉዳይ ፖለቲካዊ ነው” (the personal is political) የሚለውን መፈክር ያህል የሚገልጸው የለም። የዚህ ሐሳብ ፈጣሪ ካሮል ሀሪሽ የተባለች፣ አሜሪካዊት ፌሚኒስት ናት። የአባባሉ ስንፀ ሐሳብ እነዚህ በሁለተኛው የፌሚኒዝም ሞገድ ወቅት የተነሱ ጥያቄዎች በሴቷ የግል ጥረት ይመለሳሉ የሚለውን አባባል ለመመከት ነው። በወቅቱ የነበሩት ፌሚኒስቶች ‘የየግላችን ችግር ተደርገው የሚገለጹት ከቤት እስከ አደባባይ የምንፈተንባቸው ጉዳዮች ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ እርምት የሚፈልጉ ናቸው’ ሲሉ የተቃወሙበት ፍልስፍና ነበር።
ቤል ሁክስ በሚለው የብዕር ሥሟ በስፋት የምትታወቀው አሜሪካዊቷ ፌሚኒስት ደራሲ ቤል ሁክስ “Feminist Theory: From Margin to Center (1984)” በሚለው መጽሐፏ ላይ የፌሚኒስት ንድፈ ሐሳቦችን አመጣጥ ስትናገር፣ በዋነኝነት እና በቀዳሚነት የተሻለ ዕድል ከገጠማቸው፣ የኮሌጅ ምሩቅ፣ ነጭ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሴቶች አማካኝነት ነው ትላለች። እነዚህ ሴቶች ደግሞ ግፉዓን (marginalized) ሴቶች እና ወንዶች የሚኖሩትን ሕይወት ለመረዳት ይቸገራሉ ብላ ተከራክራለች።
ሁክስ፣ “ሴቶችን ከወንዶች ጋር ማኅበራዊ እኩልነት ማጎናፀፍ” የሚለውን የፌሚኒዝም ብያኔ ስትተች፣ ወንዶች ራሳቸው በዚህ የነጮች የበላይነት ያለበት፣ የከበርቴዎች (capitalist) ሥርዓት፣ ተባዕታዊ የመደብ መዋቅር ውስጥ እኩል ስላልሆኑ፣ “ከየትኞቹ ወንዶች ጋር እኩል ለመሆን ነው የምንታገለው?” የሚል ጥያቄ ታነሳለች። ዝቅተኛ የኢኮኖሚ መደብ ላይ ላሉ፣ ነጭ ላልሆኑ ሴቶች፣ ብዝበዛ ላይ ካሉ አቅመ ቢስ ወንዶች ጋር እኩል መሆን “የአርነት ግብ” ሊሆን አይችልም ባይ ነች። ስለሆነም፣ ፌሚኒዝምን “ፆተኝነትን፣ ፆታዊ ብዝበዛን፣ እና ፆታዊ ጭቆናን የማስቆም ንቅናቄ” (a movement to end sexism, sexual exploitation, and sexual oppression) ስትል ተርጉማዋለች።
ከቤል ሁክስ ቀደም ብላ፣ እኤአ በ1949 ሲሞን ደ ቦቯ (Simone de Beauvoir) የተባለችው ፈረንሳዊት የኅላዌነት ፈላስፋ (existentialist philosopher) እና ፖለቲካዊ ጸሐፊ “ፌሚኒዝም” የተባለውን መጠሪያ “The Second Sex” በሚለው መጽሐፏ ተቃውማዋለች። ቦቯ የሴቶች ትግል ሴትነታቸው ተረጋግጦ፣ “ሌላ ዓይነት” (other object) ሰው (ከወንዶች አንፃር የሚገመገሙ) ሆነው ለመኖር ሳይሆን፣ “ሙሉ ማዕረግ እንዳላቸው ሁለንተናዊ ሰው” (subject) መሆናቸው እንዲረጋገጥ መሆኑን በሙግቷ አስረድታለች።
ፌሚንዝም ቃሉ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ሁሉንም በሚያስማማ መልኩ አልተተረጎመም። ሆኖም “ፌሚኒዝም” የሚለው ቃል መጀመሪያ የተፈጠረው ቻርለስ ፎርዬ (Charles Fourier) በተባለ የፈረንሳይ ፈላስፋ እኤአ በ1837 እንደሆነ ይነገራል (ይህ attribution በአንዳንዶች ዘንድ ያከራክራል)። የቃሉ ምንጭ “Femina” (ፌሚና) የሚለው የላቲን ቃል፣ “ισμός” ወይም “ismós” (ኢዝሞስ) ከሚለው የግሪክ ቃል ጋር በጣምራ የተገመደ ነው። "ፌሚና" የሚለው ቃል ሴት (woman) የሚል ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን፣. "ኢዝሞስ" የሚለው ቃል ደግሞ በአማርኛ "... ነት" እንደምንለው ድኅረ-ቅጥያ (suffix) ማንኛውም ሥያሜ ላይ ሲቀጠል ቃሉ እምነትን፣ ልምድን፣ አመለካከትን የሚያሳይ ይሆናል። በዚህም ፌሚኒዝም (“ሴትነት” ብለን ልንተረጉመው የምንችለው ቃል) መጀመሪያ ሲፈጠር "ሴት መሆን" ብቻ የሚል ትርጉም ነበረው። የቦቯ ትችትም “የሴቶች ትግል ሴት ስለመሆን አይደለም” የሚል ይዘት የነበረው ለዚያ ነው።
የቃሉ ፈጣሪ ቻርለስ ፎሪዬ የኅብረተሰባዊ ምድረገነት (utopian socialist) አቀንቃኝ ነበር። ፎሪዬ ትዳር ለሴቶች የጭቆና ተቋም ነው ብሎ ያምን ነበር። በዚህም ሴቶች ነጻ ካልወጡ ማኅበራዊ ዕድገት አይኖርም የሚል ፅኑ እምነት ነበረው። በዘመኑ "ማኅበራዊ ዕድገትና የታሪክ ዘመናት ለውጦች የሚከሰቱት ሴቶች ወደ አርነት በሚያደርጉት ግስጋሴ ልክ ሲሆን፣ የማኅበረሰብ ውድቀት ደግሞ የሚከተለው የሴቶች አርነት በተንኳሰሰ ቁጥር ነው" ብሎ ተሟግቷል።
ፎርዬ እንዳለውም፣ በሴቶች የአርነት (የነፃነት) ተጋድሎ እልፍ አእላፍ ማኅበራዊ ዕድገቶች ተመዝግበዋል። እሱ ካለፈ በኋላ ሴቶች በፖለቲካው ዓለም መምረጥ መመረጥ ችለዋል፣ በኢኮኖሚው ዓለም ንብረት ማፍራት እና ማውረስ ችለዋል፣ በማኅበራዊው ዓለም በራሳቸው ፈቃድ እና ምርጫ መንቀሳቀስ ችለዋል። ብዙ ለውጦች መጥተዋል፤ ብዙ ለውጦች ይቀራሉ።
የኋላ ኋላ ራሷን ፌሚኒስት ብላ ብትጠራም፣ የፎርዬን ሥያሜ እና ከዛ በኋላ የተሰጠውን ብያኔ የተቃወመችው ሲሞን ደ ቦቯ “one is not born, but rather becomes, a woman” (“አንዲት ሴት፣ ሴት ሆና አትወለድም፤ ሴት ትሆናለች እንጂ”) በሚለው አባባሏ፣ በሥርዓተ ፆታ ጥናት ውስጥ ፆታ (sex) እና ሥርዓተ ፆታ (gender) የሚባሉ ሁለት ሐሳቦችን ለይቶ ለሚያየው የማኅበራዊ ሳይንስ አረዳድ መሠረት ጥላለች።
ፆታ (sex) በተፈጥሮ የሚገኘው፣ ሥነ ሕይወታዊ (biological) እና እና አካላዊ (physiological) ልዩነትን ሲገልጽ፣ ሥርዓተ ፆታ (gender) ግን ማኅበራዊ ሥሪት ነው። በእንግሊዝኛ Female እና Woman የሚሉትን ቃላት ለዚህ ጽሑፍ ብለን 'ሴት’ (female) እና 'እንስት’ (woman) ብለን ብንተረጉመው፣ ተፈጥሮ ‘ሴት’ እና 'ወንድ’ (male) አድርጋ ብትሠራንም፣ ማኅበራዊ ኑሮ ደግሞ እንስትነትን (womanhood) እና ተባእትነትን (manhood) ፈጥሯል። በቦቯ መነፅር ሴትን ልጅ ወደ ማጀት፣ ወንድን ወደ አደባባይ የሚልከው ኅብረተሰብ ሠራሹ ባሕል (ሥርዓተ ፆታ) እንጂ ተፈጥሯዊ እውነታ አይደለም።
ስለሆነም ሲሞን ደ ቦቯ ‘እንስታዊነት’ (ፌሚኒዝም) ሴትን በሥርዓተ ፆታ ድንጋጌ ሥር ገብራ እንድትኖር የሚያስገድድ ብያኔ ነው በማለት፣ “የሴት ልጅ ትግል ሙሉ ሰው የመሆን ትግል ነው” ብላ ተቃውማዋለች።
የፌሚኒዝም አገር በቀል መሠረት (የእኛዎቹ ሞገዶች)
ፌሚኒዝም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለምና ንቅናቄ ነው። እንደማንኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ከእምነት፣ ባሕል እና “አገራዊ” እሴቶች ጋር ውጥረት ውስጥ ሊገባ ይችላል። ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቶች ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ (ይስፋፋሉ)፣ ይሞታሉ። ፌሚኒዝም እንደ ማንኛውም ሰብዓዊ መብቶች ላይ ተመሥርቶ ያደገ ፅንሰ ሐሳብ የዳበረው በምዕራባውያን ዘንድ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በምዕራብ አገሮች ውይይቶችን ለማድረግ አስቻይ የአካዳሚ እና የፖለቲካ ነፃነት በመኖሩ እንጂ፣ የሴቶች እኩልነት እና ነፃነት ተሟጋቾች አፍሪካ እና እስያ የመሳሰሉ አኅጉሮች ውስጥ ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም።
ይህንን ለማስረዳት ብዙ ርቀን ሳንሄድ፣ የዛሬ 350 ዓመት ገደማ (በ1660) የተጻፈውን “ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ” እንመልከት። ዘርዓ ያዕቆብ በቤተ ክርስቲያን አድጎ በፍልስፍናዊ ሐሳቦቹ ብዙ መገለል እና መገፋት የደረሰበት፣ ከትግራይ ተሰዶ ጎንደር እንፍራንዝ የከተመ ምሁር ነበር። በጉዳዩ በደረሰበት ጫና ሳቢያ ከአንድ ደቂቅ በቀር ሌሎች ተከታዮችን ማስተማርና ማፍራት ያልቻለ፣ በዘመናዊ ትምህርት የኢትዮጵያ ፍልስፍና ታሪክ ሲጠቀስ የማይገደፍ ዐሳቢ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት ምዕራፍ 3፣ ቁጥር 16 ላይ “በፀነስሽ ግዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፡፡ ፈቃድሽም ወደባልሽ ይሆናል፡፡ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” በሚል በሙሴ የተጻፈውን መልዕክት በጥርጣሬ መርምሮታል። ዘርዓ ያዕቆብ "ይህ የሙሴ ሕግ ሴትን ከፈጠረ አምላክ የመጣ ሊሆን አይችልም" ሲል ይሟገታል። ታዲያ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ይህ አገር በቀል ክርክር “የፌሚኒዝም ቅድመ አያት” ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል?
ፌሚኒዝም በሴቶች ትግል ውስጥ ዕድሜው አጭር ነው። ፌሚኒዝም የሚለው ሥም አገራችን ውስጥ ሳይታወቅ ጀምሮ፣ የፌሚኒዝም ተግባር ላይ የተሰማሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አንዷ እና የማትዘነጋው የቃቄ ውርድወት ነች። ውርድወት “ለእኩል የትዳር መብቶች” የታገለች ሴት ናት። የቃቄ ልጅ ውርድወት የዛሬ መቶ ሃምሳ ዓመት ገደማ (በ1880ዎቹ) የተዳረችለት ሰው ሌሎች ሚስቶች እንዳሉት በማወቋ ያለ እርግማን (አንቂት) ፍቺ ለመፈፀም የታገለች ሴት ነች። ውርድወት፣ በዘመኑ የጉራጌ ባሕል ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስቶችን ያለሚስቶቻቸው ይሁንታ ማግባት የሚችሉ ሲሆን፣ ሴቶች ይህንን “እምቢ” በማለት ፍቺ ቢፈፅሙ ለእርግማን ይዳረጉ ነበር፤ ይህን በመቃወም፣ የመንደሯን ሴቶች በማስተባበር ከማመፅዋም ባሻገር፣ በሴቶች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንዶች ብቻ ይቀርቡበት በነበረው በየጆካ (ሸንጎ) ስርዓት ላይ ቀርባ፣ ተከራክራ የረታች እና መብቷን ያስከበረች ሴት ነች። ታዲያ ውርድወት እንደ ፌሚኒስት ታግላ፣ እንደፌሚኒስት ተወቅሳ ኖረች አትሉም?
ከመጀመሪያዎቹ ሴት የፓርላማ ተመራጮች አንዷ የነበሩት ስንዱ ገብሩ ለምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት፣ ወንዶች “ለመሆኑ የአገራችን ሴቶች መቼ ታግላችሁ ነው የመመረጥ መብት ያገኛችሁት?” ብለው ጠይቀው ነበር። ስንዱ የሰጡት መልስ አንዲት ፌሚኒስት የምትሰጠው መልስ ነው፤ “እናንተ ወንዶችስ መቼ ታግላችሁ ነው የመመረጥ መብት ያገኛችሁት?” የኢትዮጵያን የምርጫ ታሪክ ለሚያውቅ፣ የፓርላማ ምርጫ የተጀመረው፣ ይሄ ነው የተባለ የፖለቲካ ንቅናቄ እና የብዙኃን ጥያቄ ኖሮ ሳይሆን፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይሁንታ እና ዘመናዊ የመንግሥት ተቋማትን ከእንግሊዝ ለማስመጣት (import) በተደረገ ሙከራ ነው። ሆኖም፣ የተባዕታዊው ስርዓት ትምክህተኝነት (patriarichal entitlement) ወንዶች በችሮታ ያገኙትን፣ ሴቶች በትግል እንዲያገኙት ይመኛል።
የአሁኑ ሕገ መንግሥት ሲቀረፅ ጀምሮ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እስኪፀድቅ ድረስ ብዙ የሴቶች ማኅበራት ተፈጥረዋል። ታግለዋል። ትግሎቻቸው ከውጭ የትግል ስልቶች ተምረዋል፤ ነገር ግን የታገሩት አገር በቀል ችግር ነው። ርቀን ሳንሄድ በአንድ ሰው ዕድሜ ውስጥ ጠለፋ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ንብረት ማፍራት እና ማውረስ ላይ ያሉ ገደቦች ሕጋዊ ክልከላ ያልተደረገባቸው ሰፊ ልማዶች ነበሩ። የእናቶቻችን ትግል መና አልቀረም፤ ሴቶች ላይ የሚደርሱ እነዚህ መዋቅራዊ (ሕጋዊ) ጫናዎች አሁን ሕገ ወጥ ተደርገዋል። በዚህም ችግሮቹ ከአንድ ትውልድ በፊት ከነበሩበት አስከፊ ደረጃ ቀንሰዋል፤ ግን አሁንም አሉ።
የዘመናችን ኢትዮጵያዊ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ባብዛኛው ራሳቸውን “ፌሚኒስት” ብለው ይጠራሉ። እነርሱ ያንን መጠሪያ ለራሳቸው ባይሰጡም እንኳን የሴቶች መብቶችን ጎላ ባለ ድምፅ ካቀነቀኑ አድማጮች “ፌሚኒስት” ብለው ይጠሯቸዋል።
የዘመኑ ፌሚኒስቶች ንቅናቄ ከእናቶቻችን እና አያቶቻችን ትግል የተለየ ወይም በነርሱ ትከሻ ላይ የቆመ ትግል ያነገበ ነው። ትግላቸው በሕግ የተከለከሉ ነገር ግን በልማድ የቀጠሉ እንደ ጠለፋ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ሙሉ እንዲወገዱ፣ የሕግ ከለላ ያላገኙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ወንጀሎች እንዲያገኙ፣ የሕግ አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እና ማነቆዎች እንዲቀረፉ ማድረግ እና ማኅበራዊ እሴቶቻችን ውስጥ የተሰገሰጉ (የተሸሸጉ) ተግባራንትን መንግለው ለመጣል የሚደረጉ ትግሎች ናቸው።
ይህ ትግል ሕጋዊ መዋቅሮችን ከማስተካከል ወደ ባሕል እና እሴት ማረም ተሸጋግሯል (ምዕራባውያን ሦስተኛው የፌሚኒዝም ሞገድ የሚሉት ላይ በራሳችን መንገድ ደርሰናል)። ባሕል እና እሴቶች ደግሞ የቱንም ያህል አስከፊ ገጽታ ቢኖራቸውም፣ ጥብቅና የሚቆምላቸው አይጠፋም። የሴት ልጅ ግርዛት ወንጀል ሲደረግ ሴት ልጆቻቸውን በድብቅ ወደ ግርዘት የወሰዱት እናቶች ናቸው፤ ይህ የሆነው ከጥላቻ ሳይሆን ካለማወቅ ነው። ተባዕታዊው ሥርዓት ሴቶችን ራሳቸውን መበደላቸው ለራሳቸው ጥቅም እንደሆነ ሲያሳምናቸው ኖሯል። የአሁኑ ትግል ይህንን ጭንቅላታችን ውስጥ ቤት የሠራውን የድንቁርና ሐሳብ በምክንያታዊ ሙግት ሸርሽሮ መቀየር ነው።
#ትሰማ፤ ከንድፈ ሐሳብ ወደ ተግባር
የፌሚኒዝምን የሚያህል በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወዶ ዘማች ያለው አንድም ፖለቲካዊ ንቅናቄ የለም። ለዚህም ነው በዚህ ንቅናቄ ቀዳሚ ተሸናፊ የሆነው ፓትርያርኪ (ተባዕታዊው ስርዓት) ምልጃ እና ፍረጃ የጀመረው። ሆኖም፣ ፌሚኒዝም እየገሰገሰ ነው። አሁን በፌሚኒዝም ሥር የሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ራሳቸው ንዑስ ንቅናቄ ወደ መሆን ተሸጋግረዋል።
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት፣ የኢትዮጵያ ፌሚኒስቶች አንዱ እና ትልቁ ጥንካሬያቸው፣ ንቅናቄዎቻቸው በአገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚቀሰቀስ መሆናቸው ነው። ከሌሎች አገሮች እና ልምዶች ይማራሉ፤ ነገር ግን የዘመቻዎቻቸው መነሻ እና መዳረሻ ግን አገር በቀል ችግሮች ናቸው። ትሰማ የተሰኘውና በቅርብ ቀን ከፍተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ድምፅ መሆን የቻለው ዘመቻም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የትሰማ ጥያቄ “ሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደረግ ጥቃት” ብሔራዊ አደጋ (national emergency) ተብሎ ይታወጅ የሚል ነው፤ ጥያቄው ራሱን የቻለ ፆታዊ ጥቃትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚከታተል፣ የሚከላከል፣ እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የመንግሥት ተቋም ይቋቋም የሚል ነው።
የትሰማ ጥያቄ ከሰማይ የወረደ አይደለም። ፌሚኒስቶች ላለፉት በርካታ ዓመታት ሕዝብን ሲወተውቱት የነበረው ጉዳይ አብጦ ሲፈነዳ የተወለደ ጥያቄ ነው። የሴቶች ለጥቃት ተጋላጭነት፣ ከባይተዋር መንገደኛ ወይም ክፋት ከተጠናወታቸው የውጭ ሰዎች የሚመጣ አለመሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አደገኛም፣ አሳሳቢም ያደርገዋል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ባሳተመው የ2016 ዴሞግራፊ እና ጤና ጥናት መሠረት ከ10 ሴቶች ሦስቱ (29.8%) በትዳር ወይም በፍቅር አጋራቸው አካላዊ፣ ፆታዊ ወይም ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ሆኖም ይኸው ጥናት የመፍትሔውንም ፍንጭ ጨምሮ ያሳያል። የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሴቶች ለጥቃት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃና ከዚያ በላይ የተማሩ ሴቶች ተጋላጭነት ወደ 9% ዝቅ ይላል። በተመሳሳይ፣ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ የሌላቸው ሴቶች የጥቃት ሰለባ የመሆን ዕድላቸው 28.2% ሲሆን፣ የራሳቸው ገቢ ያላቸው ሴቶች ተጋላጭነት ግን ወደ 20% ያሽቆለቁላል።
ፌሚኒስቶች ሴት ልጅ፣ "ትሰማ፣ ትማር፣ ትቀጠር" እያሉ የሚወተውቱት ለዚህ ነው።
አፍሮባሮሜትር (Afrobarometer) እ.ኤ.አ. በ2024 ይፋ ባደረገው ጥናት ደግሞ ሌላ አስደንጋጭ ማኅበራዊ ተቃርኖ ይነግረናል። 70% የሚሆኑ ዜጎች በፍቅር አጋር የሚፈፀም አካላዊ ጥቃትን በፅኑ የሚያወግዙ ቢሆንም፣ ወደ ሁለት ሦስተኛ የሚጠጉት (63%) ግን "የቤት ውስጥ ጥቃት በቤተሰብ ውስጥ እንጂ በሕግ አካላት መፈታት የለበትም" ብለው ያምናሉ። ጥቃትን አለማሳወቅ የመነጨው በፖሊስ አለመተማመን ሳይሆን (86% ፖሊስ ላይ እምነት አላቸው)፣ ከማኅበራዊ መገለል፣ ከነውር እና ከበቀል ፍራቻ (50%) ነው። ቤተሰብ የጭቆና መሸሸጊያ የሚሆነው፣ ባሕልም ለወንጀል ከለላ የሚሰጠው እንዲህ እንዲህ እያለ ነው።
ምስክርነት፦ ፌሚኒዝም የዋለልኝ ውለታ
በማኅበራዊ ሳይንስ ውስጥ ሥርዓታዊ ጭቆናዎችን ለመመርመር የሚያስችሉ የጠያቂነት አስተምህሮቶችን (Critical Theories) ይማራሉ፤ እነዚህ አስተምህሮቶች ዕውቀት ከፖለቲካዊና ታሪካዊ ዐውድ ነጻ እንዳልሆነ፣ ማኅበራዊ የማዕረግ ተዋረዶች እንዴት "ተፈጥሯዊ" ተደርገው እንደሚዋቀሩ ያጋልጣሉ።
ለእኔ ግን ይህን የጠያቂነት ባሕል በኮርስ ከመውሰዴ በፊት ያስተማረኝ፣ በፖለቲካዊ አመለካከቴ ውስጥ ከተከላካይነትና ከገባሪነት (defensiveness and submission) ይልቅ የጠያቂነትና የተሟጋችነት ባሕሪን ያለበሰኝ ፌሚኒዝም እና በዙሪያዬ የነበሩ ብርቱ ፌሚኒስቶች ናቸው።
በዘር፣ በብሔር፣ በሃይማኖት እና በኢኮኖሚ መደብ የተገነቡ መድልዎዎችንና ኢ-ፍትሐዊ ተዋረዶችን በቅጡ እንድረዳ ዓይኔን የከፈተልኝ የፌሚኒዝም መነፅር ነው። ቋንቋችን፣ ተረቶቻችን፣ የቤተሰብ መዋቅራችንና ፖለቲካችን ለአንዱ እየመገቡ ሌላውን እንዴት እንደሚያደቅቁ፣ ጨቋኙን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ራሱን የጭቆና መዋቅሩን ለመረዳት ፌሚኒዝም ወደር የሌለው መሣሪያ ነው።
ፌሚኒዝምን መረዳት፣ ጭቆናን፣ የጭቆና መሣሪያን፣ የኃይል እና የማዕረግ ተዋረዶችን፣ እውነተኛ ይሁንታን እና በኃይል የተጫነ ይሁንታን ለይቶ ለመረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው።
ፌሚኒዝም እንከን አልባ ፍልስፍና አይደለም፤ ፌሚኒስቶችም ፍፁማን አይደሉም። ርዕዮት ዓለሙ ከሥርዓተ ማኅበራት ውስብስብነት እና ተለዋዋጭነት አንፃር የትንታኔ እና ምላሽ ውሱንነት ሊኖርበት ይችላል፤ ፌሚኒስቶችም ከሰው ባሕሪ የሚመነጩ በርካታ ችግሮች አሉባቸው። ነገር ግን ራስን ከምቾት ቀጠና አውጥቶ፣ የራስንም ሆነ የአካባቢን እና የኅብረተሰባችንን የዕለት ተዕለት ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶች እየፈተሹ ለመኖር ከፌሚኒዝም የተሻለ የሕሊና መፈተሻ ማግኘት ከባድ ነው።
ፌሚኒዝም በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል። ለምን? ፌሚኒዝም ነውጥ እና ጭቆናን (violence and repression) ይቃወማል፤ ማኅበራዊ የማዕረግ ተዋረዶችን (social hierarchies) ከፍትሕ አንፃር ይፈትሻል፤ የኢኮኖሚ መደብ፣ የዘር፣ የፆታ፣ እና ሌሎችም ክፍፍሎች በንቅናቄዎች ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ (intersectionality በማጤን) የትግሉን ዓይነት ይቀይሳል፤ እንዲሁም ሕግ እና መዋቅር ብቻ ሳይሆን ባሕል እና እምነት ውስጥ የተሰገሰጉ የጭቆና መሠረቶችን ያጋልጣል። ፖለቲከኞቻችን እነዚህን የፌሚኒስት ስልቶች ቢሞክሯቸው ኖሮ ምናልባት ለመላው የፖለቲካ ሥርዓታችን ፍቱን መድኃኒት ያገኙ ይሆናል።
ለዚህም ነው ያለምንም ማመንታት “ሁላችንም ፌሚኒስት መሆን አለብን” የምንለው።

No comments:
Post a Comment