ከዕለታት አንድ
ቀን ከምሣ መልስ ቡና የምጠጣበት ካፌ ተሰይሜያለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአዲስ አበባ መስተዳደር ፕሮግራም ይተላለፋል፡፡ ፕሮግራም
አቅራቢያዋ በእኛ ቲቪ ያልተለመደ ዓይነት ፕሮግራም እያቀረበች ነው፡፡ አንዷ መምህርት ትናገራለች ‹‹ልጆቹ ራሳቸውን ይስታሉ››
አለች፡፡ ልጆቹ ያለቻቸው እሷ የምታስተምርበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎችን ነው፡፡
‹‹እናነሳቸውና
ካፌ ወስደን ውሃ አጠጥተን፣ ዳቦ አብልተን ስንለቃቸው ደህና ይሆናሉ፤›› አለች መምህርቷ፡፡ ‹‹በኋላ ላይ ሲደጋገምብን ጠይቀናቸው-
ለካስ የሚወድቁት ምግብ ከበሉ ሁለት ሦስት ቀን እየሆናቸው ነው፡፡››
ያንን ፕሮግራም
ተመልክተው ከእንባቸው ጋር ያልታገሉ ሰዎች አልነበሩም፡፡ ሕፃናቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቸቸው የተነጠሉ ሲሆኑ፣ ያልተነጠሉትም
ቢሆኑ ቤተሰቦቻቸው በየቀኑ የመመገብ አቅም የሌላቸው ነበሩ፡፡ የኋላ ኋላ በደረሰኝ መረጃ ያንን ፕሮግራም ያቀረበችው ጋዜጠኛ ‹‹በመርዶ
ነጋሪነት›› ከአለቆቿ ተግሳፅ ደርሶባታል፡፡
- - -
ኢቴቪ ጫወታ አማረልኝ
ብሎ ያቀረባቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ ኮሌጅ ዘልቀው ዲግሪ እንደጨበጡ ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን በኮብል ስቶን ጠረባ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
ኢቴቪ ይሄንን ‹‹ሥራ ፈጠራ›› ብሎታል፡፡ በሥራ ፈጠራና በሥራ አለመናቅ በኩል መስመር አለ፡፡ እነዚህ የተማሩ ኃይሎች፣ የፈለገ
ሥራ ባይንቁ እንኳን የተማረ ኃይል እጥረት አለባት የምትባለው አገር ውስጥ ምናልባትም ከዚያ ውጪ ሌላ የሥራ አማራጭ የሌላቸውን
ሥራ እየተሻሙ ነው፣ በልተው ለማደር፡፡
- - -
ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው
የውይይት መድረክ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን መወያያ ንግግር አቅርበው ነበር፡፡ ከታዳሚዎቹ አንዱ ‹‹ማስተርስ አለኝ፤›› አለ፡፡
‹‹ነገር ግን ሥራ አጥቼ በስንት መከራ አሁን አንድ ሺህ ከምናምን ደሞዝ እየበላሁ ነው፡፡ ነገር ግን የክፍለሃገር ልጅ በመሆኔና
የቤት ኪራዩን ስለማልችለው ዛሬ አንዱ፣ ነገ አንዱ ጓደኛዬ ቤት እያደርኩ ነው፡፡ ለዚህ ኑሮ ያበቃኝን ኢሕአዴግ እግዚአብሔር ይስጠው››
አለ፡፡ ሪፖርተርም ይህ አይግረማችሁ ሲለን እንዲያውም ‹‹ዲግሪ
ያላቸው ዜጎች የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል›› የሚል ዜና አስነብቦናል፡፡
- - -
አንድ መምህር ጓደኛዬን
አገኘሁት፡፡ በተለይም እዚህ ከተማ ውስጥ ቤተሰብ ስለሌላቸው መምህራን ባልደረቦቹ ሕይወት ይነግረኝ ገባ፡፡ መምህራኑ ርካሽ ከሚባለው
ከት/ቤቱ ካፍቴሪያ ይመገባሉ፡፡ ነገር ግን ተቆራርጣ የምትደርሳቸው ደሞዛቸው በዕዳ ‹‹ኔጌቲቨ›› ትገባለች፡፡ አንዳንዴ ምህረት
ይደረግላቸዋል፣ ባብዛኛው ግን ለሚቀጥለው ወር ይሸጋገርባቸዋል፡፡
ጓደኛዬ ሲነግረኝ
‹‹አንዱ፣ የደሞዝ ቀን ዕዳውን ሲያወራርድ 35 ሳንቲም ቀረው፡፡ እሷኑ ሲጃራ ገዝቶ አጨሰባት፡፡›› ይህንን የነገርኩት ሌላ ሰው
‹‹ሲጃራ በ35 ሳንቲም ማግኘቱም ጥሩ ነው፡፡›› አለኝ፡፡
- - -
ዝግንን የሚል ነገር ነው፡፡ ምን ይሻለን ይሆን
ReplyDeleteከመዘግነን አልፎ የሚያስደነግጥ ነገር ነው! ብሎም የሚያሳፍር እና ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ግን መፍትሄ የሌለው ችግር የለም፡ የተማረው የሰው ሃይል ቁጥር በዝቶ ካለው ፍላጎት ጋር ካልተመጣጠነ ትልቁ ችግር ይሄ ነው፡፡ እውነት ነው ብዙ በዲግሪ እና በማስተርስ የተመረቁ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምሁራን በየጊዜው ይመረቃሉ ነገር ግን እነዚህ ምሁራን የሚቀበል መስሪያ ቤት እና ድርጅቶች በቂ አይደሉም፡፡ በቂ እንዲሆኑ አልተፈለገም ይሁን ለምን አልኖሩንም የሚለው ቀጣይ ዋና ችግር ነው! እንደው ከጀመርኩት አይቀር የግድ አንድ ሰው ተመረቀና ስራ ፈልጎ መቀጠር አለበት በሚለው ነጥብም ብዙ አልስማማም፡፡ እንዲያውም የስራ ፈጣሪ ነው መሆን ያለበት በሚለው የበለጠ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ የትምህርት ፖሊሲያችን ስራ ፈጣሪነትን የሚያበረታታ እና የሚያሳድግ አይደለም እዚህ ጋር መስተካከያዎች ቢደረጉበት የተማረው ምሁር በትንሽ ነገር ተነስቶ ሀገር እስከመለወጥ ይደርሳል፣ ለሌላውም ይተርፋል፡፡
ReplyDeleteሌላው ነጥብ ደግሞ አዳዲስ የሚመሰረቱ ማንኛውንም አነስተኛ እና ጥቃቅን ድርጅቶችን በደምብ እራሳቸውን ችለው እስኪቋቋሙ ድረስ ማበረታታት እና መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ባለው ስርአት እስከ 6 ወር አንድ አመት ድረስ ታክስ አይከፈልም ነበር አሁን ስርዓቱ ተቀይሯል፡ አይደለም ድርጅቱ እስኪቋቋም ቀርቶ ያለውንም ማፈናፈን ያልቻለ አሰራር ነው የተመሰረተው ነገር ግን ማስተካከያ ቢደረግበት የተሻለ ውጤት ያመጣል፣ አልፎ ተርፎም ቅድም ከላይ የተነሱትን የምሁራን ጉዳይ በቂ መልስ ይሰጣል፡፡ እርግጠኛ ያልሆንኩት ግን የሰማሁት፡ የቻይና መንግስስት አዲስ ለሚመሰረቱ ትናንሽ ድርጅቶች በተቻለው መጠን ያግዛል፡፡ አንድ ቻይናዊ ድርጅት መክፈት ቢፈልግ የሚያስፈልገውን ካፒታል እና አትራፊ ነው አይደለም የሚለው ታይቶ መንግስት ጣልቃ ገብቶ በጋራ ባለቤትነት ወይም በፐርሰንት ተካፍሎ ያስተዳድራል፡፡ በዚህ ባለቤቱም ተጠቀመ፣ መንግስት ተጠቀመ፣ ሃገር ተጠቀመ ማለት ነው! አሁን ግን በትክክል መንግስት ከቅሚያ ያልተናነሰ ስራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡
ምነው ከነቻይናና ህንድ እንደዚህ እንደዚህ አይነት ሃሳቦችን ከመውሰድ ነጻነትን ማፈኛ መሳሪያ መግዛት በለጠባቸው???