ስም ያለው
ነገር ሁሉ ‹‹ያለ›› ነገር ነው እያለ ከልጆቹ’ጋ ሲሟገት የነበረ አንድ ጦማሪ ወዳጄ፥ ስማቸው
ከመቃብር በላይ የዋለላቸው ሰዎችም ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች እስካሉ ድረስ ‹‹የሉም›› ማለት አይቻልም - ምክንያቱም ‹‹አሉ››
ብሏል፡፡ መከራከሪያው ለዚህ ጽሁፍ መንደርደሪያ ግብአትነት ብቁ ስለሆነ ያለምንም ክርክር ተቀብዬዋለሁ፡፡ የጨዋታዬ ርዕሰ ጉዳይ
ግን ‹‹ያለ›› እና ‹‹የሌለ›› ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም አንዳንድ ሕያዋን ሰዎች ከተናገሯቸው ሕያው ንግግሮች መካከል እያጣቀሱ
የዛሬውን የአገራችንን ፖለቲካ መሄየስ ነው፡፡ በምናባዊ ሳይንስ ሊቁ አልበርት አይንስታይን ብንጀምርስ?
1. አልበርት አይንስታይን
“The world will not be destroyed by those
who do evil, but by those who watch them without doing anything.” (ዓለማችን የምትጠፋው
ክፉ በሚያደርጉ ሰዎች ሳይሆን ክፉ ሲያደርጉ እያዩ ዝም በሚሏቸው ሰዎች ነው፡፡)
በኢትዮጵያ
የፖለቲካ እውነታ በየጓዳው ከመንሾካሾክ እና ከመብሸቅ ባሻገር ይሄ መንግስት (ይሄ ገዢ) ያለእኛ ተገዢነት እና ፈቃደኝነት ሊጨቁነን
እንደማይችል ገብቶን የተነጠቅነውን ነፃነት ለማስመለስ የምንሞክር እጅግ ጥቂቶች ነን፡፡ በተለይም ‹‹ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ብዙሐኑን
ስላላማከለ አንድ ቀን አገሪቱ ወደማትወጣው ችግር ውስጥ ትገባለች፣ ወዘተ. ወዘተ...›› እያሉ የጋን ውስጥ ትንታኔያቸውን የሚሰጡት
ነገር ግን ለጋዜጣ እንኳን ማብራሪያ ለመስጠት ‹‹ስሜ ከተጠቀሰ አይሆንም›› የሚሉ ምሁራን ከአጥፊው ገዢው ፓርቲ ይልቅ - ለጥፋቱ
ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡
2. ማሕተመ ጋንዲ
“You assist an evil system most effectively
by obeying its orders and decrees. An evil system never deserves such
allegiance. Allegiance to it means partaking of the evil. A good person will
resist an evil system with his or her whole soul.” (መጥፎ ስርዓትን በጣም ጥሩ አድርገህ የምታጠናክረው
ትዕዛዛቱን እና አገዛዙን እሺ ብለህ ስትቀበል ነው፡፡ መጥፎ ስርዓት እንዲህ ዓይነት ታዛዥነት አይገባውም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ስርዓት
መታዘዝ ማለት ለጥፋቱ ተባባሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ማንኛውም መልካም ሰው የተበላሸ ስርዓትን በሙሉ እስትንፋሱ ይቃወማል፡፡)
በዘመነ ኢሕአዴግ
አምባገነን በአምባገነን እግር ተተክቷል፣ ዘረኝነት ከመቼውም በበለጠ ነግሷል፣ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትና በምርጫ መንግስት
የመቀየር እድል ብቅ ብሎ ወደ ሰንኮፉ ተመልሶ ገብቷል… ሁሉንም ክፉ ድርጊቶች እናውቃለን፣ እንታዘባለን፡፡ ሆኖም ምንም ማድረግ
እንደማይችል ሰው እጅና እግራችንን አጣጥፈን ተቀምጠናል፡፡ የሰላማዊ ትግል ምሳሌ የሆነው ማሕተመ ጋንዲ ግን ለእንዲህ ዓይነቱ ብልሹ
ስርዓት ከመታዘዝ የበለጠ ውርደት እንደሌለ ይነግረናል፡፡ ሰዎች በማያምኑበት ሥርዓት ተገዢ በሆኑ ቁጥር የስርዓቱን ስር መስደድ
እያጎለበቱ እንደሆነ ነው የላይኛው አባባሉ የሚያስረዳው፡፡ ስለዚህ በጋንዲ ዓይን ትዝብት ውስጥ ገብተናል፤ ለማንፈልገው አገዛዝ
‹‹እምቢታ›› የሌለን የክፉ ስርዓት ሰለባ ሆነናል፡፡
3. ዴዝሞንድ ቱቱ
“If you are neutral in situations of
injustice, you have chosen the side of the oppressor. If an elephant has its
foot in the tail of a mouse and you say that you are neutral, the mouse will
not appreciate your neutrality.” (ኢ-ፍትሐዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ከማንም ለመወገን ካልፈለግክ፣ ያኔ የጨቋኙን
ተግባር መደገፍ መርጠሃል ማለት ነው፡፡ ዝሆን የአይጧን ጭራ ረግጦ እያየህ፣ ገለልተኛ ነኝ ብትል ያንተ ገለልተኝነት ለአይጧ አይዋጥላትም፡፡)
በአገራችን
ምን እየተከሰተ ነው? የኃይል ሚዛኑ ወዴት አጋድሏል? ብረቱን የታጠቀው ማነው? የፍርድ ቤቶች ዳኛ ማነው? የዚህን መልስ እውነታ
በልቡ እያጉላላ ‹‹የለም፤ ዛሬ የተረገጥኩት እኔ ስላልሆንኩ አይመለከተኝምና ለማንም የማልወግን ገለልተኛ መሆን አለብኝ›› ብሎ
ዝም ማለት ሁሉን ኃይል ተቆጣጥሮ ሌላውን ኃይል ለሚረግጠው አካል መወገን ማለት ነው፡፡ ገለልተኝነት ወይም ዝምተኝነት በሚዛናዊ
ተቀናቃኞች መሃል እንጂ በጨቋኝ ተጨቋኞች መሃከል ለጨቋኙ መወገን ማለት ነው - ይህንንም ዴዝሞንድ ቱቱ ቁልጭ አርገው ከላይ ተናግረውታል፡፡
የዓለማችን
ታላላቅ ሰዎች ስለወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን አሉ፤ እርስዎስ ምን ይላሉ?
ዋናው ችግርማ ምንም አያገባኝም ማለቱ ሳይሆን ፍርሃቱና ለጥቅም ተገዢነቱ ነው:: ይሄ ደግሞ የሚያሳየው ስለ ኢትዮጵያዊያን አልገዛም ባይነትና ቆራጥነት የተወራልንን በሙሉ ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚከተው ነው::
ReplyDelete