Pages

Monday, June 11, 2012

የአንድ ኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ታሪክ


የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እጣ ክፍሎቼ እንዳልሆኑ እየተረጋገጠ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን እርሜን ‹ኢሚግሬሽን› ብሄድ ለሦስት ሰዓታት በግዞት እንደቆየሁ አጫውቻችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ የጓደኛዬን ጉዳይ ላስፈጽም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰነድ ማረጋገጫ ቢሮ ተገኘሁ፡፡ እዚህ እንደከዚህ ቀደሙ አካላዊ ጥቃት ባይደርስብኝም - መንግስታችንን በኪራይ ሰብሳቢነት እንድታዘበው የሚያደርገኝ ነገር ተከስቷል፡፡

ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ የሰነድ ማረጋገጫ ሥራ የሚባለው ሰነዱን ባለቢሮዎቹ ተኮር ብለው ካዩት በኋላ ማሕተም ይመቱበታል - አለቀ፡፡ ይህ ሥራ የ30 ሰከንድ ሥራ ቢሆንም ብዙ ያስከፍላል - በጊዜም፣ በገንዘብም፡፡

እኔ የሄድኩት አንድ የትምህርት ማስረጃ ሰነድ ላይ የእውነተኛነት ማረጋገጫ ማሕተም ለማስመታት ነው፡፡ ይህንን ሰነድ ሌላ ቦታም ቀደም ብሎ ማረጋገጫ ማሕተም ማስመታት በቅድመ ሁኔታነት ተከናውኗል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሰነዶች ማረጋገጫ ቢሮ ደግሞ ከግቢ ውጪ ጥቂት፣ ጊቢ ውስጥ ደግሞ በአግዳሚ ወንበር እና ከዚያ የተረፈው ግድግዳ ተደግፎ ቆሞ የተሰለፈ ብዙ ሰው አለ፡፡ ያንን መጠበቅ - በተለይ እንደኔ ላለውና በስጋ ሳይሆን ባጥንት ብቻ ለቆመ ሰው - ወገብን ይፈታተናል፡፡

በግምት ለሁለት ሰዓታት ያህል በሰልፍ ጠብቄያለሁ፡፡ ተሰልፌ ግን ስሰጋ የነበረው ስለወገቤ፣ ስለጥበቃው ወይም ከምሳ ሰዓት በፊት ወረፋው ባይደርሰኝስ ስለሚለው አልነበረም፡፡ እነዚህኞቹ እዳቸው ገብስ ነው፡፡ እኔን የጨነቀኝ ይህን ሁሉ ሰዓት ጠብቄ ያላሟላኸው አንድ ነገር አለ ተብዬ ሰልፉን እንደገና እንድጀምር ብደረግስ?

ኪራይ ሰብሳቢነት - አንድ
ይሄን የሚያህል ሰልፍ ያለበት ቢሮ ምን፣ ምን እንደሚያስፈልግ መረጃ የሚጠየቅበት በቂ መንገድ የለም፡፡ የጊቢ ውስጥ መረጃ ሰጪ ሴት ብትኖርም የውጪውን ሰልፍ ከጨረሱ በኋላ እንደገና ወደኋላ መመለስ የሚባል ጣጣ አለ፡፡ ይህንኑ ፍራቻ አሰስ ገሰሱን ሁሉ ኮፒ ከማድረግ አንስቶ የተቻለኝን ሁሉ (መጨረሻ ላይ ግን አስፈላጊ እንዳልነበር የተረዳሁትን) ጥንቃቄ አደረግኩ፡፡ ምን አለ ይሄ ቢሮ ሁሉንም መረጃዎች የሚያቀርብበት ኤሌክትሮኒክ የመረጃ ምንጭ (ምናልባት ስልክ፣ ምናልባት ድረገጽ) ቢኖረውና ከጭንቀት ቢገላግለን፡፡ ይህንን ለማድረግ ገንዘብ የሚያጥረው ከመሰላችሁ - ኪራይ ሰብሳቢነት ሁለትን አንብቡ፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት - ሁለት
ለዚህ ለጠቀስኩላች የ30 ሰከንድ አገልግሎት ጽ/ቤቱ 150 ብር ጠይቆኛል፡፡ ወቸ ጉድ! ቢቻል ይሄ ለታክስ ከፋይነቴ በነፃ የሚሰጠኝ አገልግሎት መሆን ነበረበት፡፡ አሊያም ዋጋው ባይበዛ! ለየትኛው ሥራ? የሆነ ነገር የሚሰጡኝ ነገር ቢኖር? - እሺ! የሆነ የሰነዱን እውነተኛነት የሚያረጋግጡበት ውጣ ውረድ ቢኖር? - እሺ! የሆነ ነገር ቢኖር ክፍያው አሳማኝ ይሆን ነበር፡፡ ያሳዝናል፤ ከኔ የበለጠ ብር - እንደየሰነዳቸው ዓይነት - የሚከፍሉ ሰዎችም አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ከኪራይ ሰብሳቢነት ውጪ ስም አላገኘሁለትም፡፡ በየ30 ሰከንዱ በ7 መስኮቶች የሚሰበሰበው ገንዘብ ምን ይደረግ ይሆን?

ኪራይ ሰብሳቢነት - ሦስት
ከፊት ለፊቴ ተሰልፋ የነበረች አንዲት ሴት ስልክ ስታወራ የነበረች ልጅ ‹‹ወደአዲስ አበባ ሄጄ እኮ ነው የዘጋኋችሁ…›› ስትል ሰማኋት፡፡ መጀመሪያ አሃ! ለካስ ከክፍለሃገርም የሚመጡ አሉ ብዬ ተጽናናሁ፣ ቀጥሎ እንዴ! ለካ እኔም ራሴ ክፍለሃገር ላለው ጓደኛዬ ተወክዬ ነው አልኩ እና አሰብኩ፣ ሰልሼ ስለአሰራሩ ማሰብ ቀጠልኩ፡፡

ቆይ ይሄ ፌዴራሊዝም የሚባለው ነገር እኒህ እኒህ ሥራዎችን እንኳን በየክልሉ፣ በየወረዳው ማከፋፈል ካልቻለ - ግዴታ ለትንሹም ለትልቁም ከየክፍለሃገሩ እየተመሙ ወደአዲስ አበባ መምጣት አለባቸው ማለት ነው? አንዲት ማሕተም ለማስመታት ከሥራ የቀናት ፈቃድ መውሰድ፣ የሆቴል እና የትራንስፖርት ወጪ ማድረግ - ፈጽሞ ፍትሐዊ አሰራር አይደለም፡፡ እዚህ ብቻ አይደለም፣ ‹ኢሚግሬሽንም›፣ ሌሎቹም መሰል ቢሮዎች ውስጥ ይህ ነገር መታረም አለበት፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ሥራ ቢሆንም እንኳን ግዴታ አንድ ቦታ ተማክሎ መሰራት አለበት የሚል ሕግ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለዚህ ይሄ የመንግስታዊ ኪራይ ሰብሳቢነት ውጤት ነው ብዬ ደመደምኩ፡፡

4 comments:

  1. የመንግስት ሰሞነኛ ቋንቋዎች ይገርማሉ፡፡ አንዱ ሳይገባኝ ሌላ ይወለዳል፡፡ …ጥገኛ ዝቅጠት ሳይገባኝ ኪራይ ሰብሳቢነት መጣ፡፡ ወይ የእንግሊዝኛ ተርሙን ባውቀው ዊኪፒዲያ ላይ አየው ነበር፡፡…ጽናቱን ይስጥህ፡፡

    ReplyDelete
  2. Naod, if you are serious about the word I think it's rent-seeking for ኪራይ ሰብሳቢ. የገዢያችን የወቅቱ ምርጥ ቃል። ለምሳሌ የመንግስት መስሪያ ቤት ለኢንተርቪው ሄደህ ኪራይ ሰብሳቢ ማለት ምንድነው ልትባል ትችላለህ። ከምሬ ነው። ቤት አከራይቶ ገንዘብ ማግኘት ያለች የፅዳት ስራ አላገኘችም።

    ReplyDelete
  3. Thank you. I checked it on wikipedia and it talks about economic benift by manipulating social and government system....It also notes that most people confuse rent-seeking with profit-seeking. I think our gov't official, as usual, are confused about terms.

    ReplyDelete