Pages

Friday, May 18, 2012

ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይስ የለም? (እርስዎ ምን ይላሉ?)


ዴሞክራሲ ትልቅ ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ሆኖም ልክ እንደአብዛኛዎቹ የዓለማችን እውነታዎች ፍፁም ሊሟላ አይችልም፡፡ ነገር ግን ምሁራን ዴሞክራሲን መለኪያ ቅንጣቶችን ያስቀምጡለታል፡፡ በነዚህ ቅንጣቶች እየለኩም ነው ሃገራትን ዴሞክራሲያዊ፣ ከፊል ዴሞክራሲያዊ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ… እያሉ ሲፈርጁ የምንመለከተው፡፡ እኛስ፣ ኢትዮጵያውያን ራሳችን ዴሞክራሲያችንን መመዘን ብንችል ብላችሁ ተመኝታችሁ አታውቁም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የማሰቢያ ቋቶች (think tanks) አሁን አሁን ብቅ ብቅ ማለት ቢጀምሩም ብዙዎቹ ደፍረው ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን እያነሱ ጥናት አያደርጉም፡፡  በየዓመቱም እየገመገሙ ‹‹አድገናል፣ ወድቀናል›› አይሉንም፡፡ አገራችን ‹‹በማደግ ላይ ያለች›› በመሆኗ እና ምናልባትም እጅግ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ መንግስታት ስታገኝ እንዲህ ዓይነት ተቋማት ወደፊት እየተበራከቱ እንደሚመጡ ተስፋ ማድረግ ብንችልም እስከዚያው ግን እኛ የበኩላችንን ጥረት ብናደርግስ?

ብዙ ጊዜ የሚሞግተኝ ጥያቄ አለ፡፡ (በተለይ ይህንን ጦማር ለማንበብ የታደልነው) ብዙዎቻችን ከተሜዎች ወይም ከተማ ቀመስ ነን፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የገጠር ነዋሪዎች ናቸው፤ በይነመረብ (Internet) ለነርሱ ቅንጦት ነው፡፡ ለብርሃን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል እንኳን ለማግኘት አልታደሉምና ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ ስለኢትዮጵያ ስናወራ ከራሳችን ስሜት እና ልምድ ተነስተን እንደመሆኑ የብዙሐኑን ስሜት እና እውነት ማንፀባረቃችንን እርግጠኛ መሆን ይቸግረኛል፡፡ እርግጥ ነው፤ ገጠሬው ኢትዮጵያዊ የሚባልለትን ያህል እንዳልበለፀገ እግር ጥሎን ስንሄድ፣ ዘመድ አዝማዶቻችን ሲመጡ እና በሌሎችም አቋራጮች እንገነዘባለን፡፡

ችግሩ
ገጠሬው ኢትዮጵያዊ ለበይነመረብ ብቻ ሳይሆን ለቀለም ትምህርት እና መረጃም ሩቅ ነው፡፡ (ይህ ጥቂት የማይባሉ ከተሜዎችን ያልለቀቀ ነገር ቢሆንም፤) ገጠሬው ግን እስካሁን ‹‹ንጉሥ አይከሰስ›› በሚለው እምነቱ እንደፀና ነው፡፡ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ እና ፍላጎቱ ዘልቆ ገብቶታል ለማለት የሚያስደፍር እውነት አይታየኝም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ እውነት በየትኛውም ዓለም የፀና ነው፡፡ ዕጣ ፈንታ ከውልደታቸው እስከ ዕድገታቸው ነገሮችን የማወቅ ዕድል ያመቻችላቸው ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ተፈጥሮ ያመቻቸላቸውን የመልካም አጋጣሚ ብድር መመለስ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ተጠቃሚ ዜጎች፣ ጥቅም ለጎደለባቸው መታገል አለባቸው ነው ነገሬ፡፡ ስለዚህ ገጠሬው ያፈራውን እህል ብቻውን እንደማይበላው ሁሉ ከተሜውም ስለዴሞክራሲ ገብቶኛል የሚል ከሆነ የዴሞክራሲን አጀንዳ ጠረጴዛ ላይ ሲያስቀምጥ ለከተሜው ብቻ ሳይሆን ለገጠሬውም ጭምር ነው ማለት ነው፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ገጠሬው ስለዴሞክራሲ የሚኖረው ግንዛቤ ከከተሜው ያነሰ ነው የሚል መስማሚያ ላይ መድረስ አወዛጋቢ አይመስለኝም፡፡ እስኪ ደግሞ ኢትዮጵያዊው ከተሜ በአሁኑ ስርዓት ስለሚተገበረው ዴሞክራሲ ምን ይላል የሚል ጉጉት አደረብኝ፡፡ ነገር ግን ከተሜውን ሁሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የነበረኝ አማራጭ ለበይነመረብ ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን (ናሙና ከተሜዎች መሆናቸው አያጠራጥርም፤ ነገር ግን ከተሜ ሁሉ በይነመረብ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ቢሆንም በይነመረብ ተጠቃሚዎች ለዓለማዊ መረጃዎች ቅርብ እንደመሆናቸው ስለዴሞክራሲም የሚኖራቸው ግንዛቤ የተሻለ እንደሚሆን በማመን) የመስመር ላይ ቅኝት (online survey) አዘጋጅቼ ውጤቱን ለመተንተን እና በጦማሬ ላይ ለማተም ፈለግኩ፡፡ እነሆ ጥያቄዎቹንም አዘጋጅቼ እዚህ አቀረብኩላችሁ፡፡

መጠይቁን ሳዘጋጅ የተጠቀምኩት በርካታ ምሁራን ዴሞክራሲ ይለካባቸዋል ብለው በሚያስቀምጧቸው ቅንጣቶች ነው፡፡ እነዚህም ፍትሐዊ ምርጫ፣ ነፃ ሲቪክ ማሕበረሰብ፣ በነፃ ሐሳብን የመግለፅ መብት፣ የሕግ የበላይነት፣ የብዙሐን መሪነት፣ የግለሰብ ነፃነት እና ሌሎችንም ያካትታሉ፡፡  

ጥያቄዎቹን ከማቅረቤ በርካቶች መሙላት መጀመራቸውን ሪፖርቱ ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ አንዳንድ አስተያየቶች እየደረሱኝም ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ‹አማካይ› የላቸውም (ጥቁር እና ነጭ ብቻ ናቸው)፣ የተፈለገውን ያህል ብዛት ያለው ሰው ምላሽ መስጠት ሊፈራ ይችላል፣ የዚህ ቃለ መጠይቅ ድምዳሜ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚገነዘቡ የ'አሁኑ'ስርዓት ተጠቃሚ ነን ባዮች ሊፈጥሩት የሚችሉትን ድምዳሜ የማስቀየር ተፅዕኖ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ስጋቶቹ እና እንደድክመት የተነሱት እና ሊነሱ የሚችሉት ሐሳቦች ተገቢም ትክክልም ናቸው፡፡ ሆኖም የዚህ አነስተኛ ቅኝት ዋና ዓላማ ከድምዳሜውም በላይ ነው፡፡ ስለዴሞክራሲያችን መወያየት መቻል፡፡ ስለዚህ ከላይ ጥያቄዎቹን በመሙላት በበይነመረብ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ስለዴሞክራሲያችን ያለውን አመለካከት ጠቅላላ ምስል ለመገመት ይረዳን ዘንድ መጠይቁን በመሙላት የቻልነውን ያክል እንሞክር፡፡

No comments:

Post a Comment