Pages

Saturday, May 12, 2012

የጋንዲ፣ ኪንግ እና ማንዴላ መንፈስ


ማሕተመ ጋንዲን፣ ማርቲን ሉተር ኪንግን እና ኔልሰን ማንዴላን ስታስታውሱ መጀመሪያ ወደአዕምሯችሁ የሚመጣው ነፃነት ነው፤ በትግል የተገኘ ነፃነት፡፡ ሦስቱም ስለነፃነት የኖሩ፣ ዘመን የሞገታቸው ነገር ግን የታገሉለትን ነፃነት እየኖረ ያለው እነርሱን ተከትሎ የመጣው ትውልድ በልቡ ሃውልት ያቆመላቸው የ20ኛው ክፍለዘመን ድንቅ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሦስቱም የተወሰደባቸውን ነፃነት ለማስመለስ ብረት ማነገብ ያላስፈለጋቸው፣ ሰላማዊ የነፃነት እና የእኩልነት ታጋዮች ነበሩ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያኖችስ ከነእዚህ የዓለም ሃብቶች አንፃር ራሳችንን አይተነው እናውቅ ይሆን?

ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር እና ኔልሰን ማንዴላ የማሕተመ ጋንዲ የመንፈስ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በማሕተመ ጋንዲ የትግል መርሕ የተቀረጹ ናቸው፡፡ የማሕተመ ጋንዲ መርሕ ‹ሰላማዊ ተቃውሞ› ነው፡፡

ማሕተመ ጋንዲ በእንግሊዞች የበላይነት የምትመራውን ሃገራቸውን - ሕንድ ነፃ ለማውጣት ይጠቀሙበት የነበረው ዘዴ - ብረት አልባ ጦርነት ነበር፡፡ ሰላማዊ እምቢተኝነት እና አለመተባበር የተባሉ መሳሪያዎች፡፡ ማሕተመ ጋንዲ በሕንድ ለሕንዳውያን እኩልነት መታገል ከመጀመራቸው በፊት በደቡብ አፍሪካ ያሉ ሕንዳውያን የሚደርስባቸውን ጭቆና በመታገል ነው የጀመሩት፡፡ ጋንዲ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው አንደኛ መደብ ዜጋ ለሚባሉት (ነጮች) ብቻ በተፈቀደ ባቡር ውስጥ በገዛ ፈቃዳቸው (በእምቢተኝት) በመሳፈራቸው በጥበቃ ኃይሎች ተወርውረው ከባቡሩ እንዲወጡ ተደርገው ነበር፡፡ ጋንዲን ይሄ ‹‹አርፈው እንዲቀመጡ›› አላደረጋቸውም፤ እንዲያውም በእምቢተኝነታቸው በመቀጠላቸው በማግስቱ በአንደኛ መደብ የባቡር ክፍል ውስጥ መሳፈር እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡


ጋንዲ ወደሕንድ ተመልሰው ሳላማዊ ትግል ሲጀምሩም መንገዱ ቀና ሆኖላቸው ነበር ለማለት የሚያስችል ነገር ከናካቴው አልነበረም፡፡ የሚመሩት ሰላማዊ ተቃውሞ - አድማ፣ አለመታዘዝ፣ የእንግሊዝ ኩባንያዎችን አለመጠቀምና የመሳሰሉት ሒደቶች ወደአመጽ እየተለወጠ ለብዙ ዜጎች ሕልፈት እና እስራት መንስኤ ሆኗል፡፡ እርሳቸው እና 65,000 ሌሎች ሕንዳውያንም የታሰሩበት አድማ ተከስቶ ያውቃል፡፡ ማሕተመ ጋንዲ ከሰባት ዓመታት በላይ በፈጀው በዚህ የሰላማዊ ትግል (እምቢተኝነት እና አለመተባበር) አቋማቸው ገፍተውበት፣ ለእንግሊዞቹ ሰበብ የሚሆን የተጋነነ አመጽ ዕድል ሳይፈጥሩ ሕንድን ለነፃነት አብቅተዋል፡፡

ማሕተመ ጋንዲ ለዚህ ሥራቸው አምስት ጊዜ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው ሳይሸለሙ ቀርተዋል፡፡ የኋላ ኋላ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ማሕተመ ጋንዲን ሳይሸልም መቅረቱ ስህተት እንደነበር ለማመን በቅቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1948 - ማሕተመ ጋንዲ ለመጨረሻ ጊዜ ለኖቤል ታጭተው የነበሩ ቢሆንም ሽልማቱን ሳይቀበሉ በመገደላቸው - ኮሚቴው ‹‹በሕይወት ያለ ተስማሚ ሰው ባለመኖሩ›› በሚል ምክንያት ያንን ዓመት ማንንም ሳይሸልም ቀርቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1989 ዳላይ ላይማ ኖቤል ሽልማት ሲቀበሉ ኮሚቴው ‹‹ሽልማቱ ለማሕተመ ጋንዲ መታሰቢያነት ይዋል›› ማለቱ ያኔም ይገባቸው እንደነበር የሚያስመሰክር ነው፡፡

ማርቲን ሉተር ኪንግ በማሕተመ ጋንዲ የሰላማዊ ትግል ስልት የሚያምን፣ በዴሞክራሲ የማትታማውን አሜሪካ ለጥቁሮች እኩልነት ሕጋዊ እውቅና እንድትሰጥ የታገለ ታላቅ ሰው ነው፡፡ የኪንግ ትግል የተቀጣጠለው በተለይ ሮዛ ፓርክስ፣ የሕዝብ አውቶቡስ ውስጥ ለነጮች ወንበሯን አልለቅም ብላ እምቢ ማለቷን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ መሪነቱ ነው፡፡ ያኔ ቤቱ በቦምብ ከመመታቱም ባሻገር ለእስር ተዳርጎ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የኪንግ አገር አሜሪካ፣ በወቅቱም ቢሆን በሕግ የምትመራ ቢሆንም የእኩልነት ትግሉ እንደማንኛውም የነፃነት ትግል መከራ የበዛበት ነበር፡፡ ለዚህ ትክክኛ ምሳሌው ‹‹bloody Sunday›› እየተባለ የሚታወሰው እና ብዙዎች በጥይት የተደበደቡበት የተቃውሞ ስብሰባ ነው፡፡ ቢሆንም ሰላማዊ እምቢተኝነት እና አለመተባበርን ገፍቶ መቀጠል የሚችል መንግስት ባለመኖሩ ትግሉ ለፍሬ በቅቷል፡፡

ማርቲን ሉተር ኪንግ ከመንፈስ አባቱ ጋንዲ የተሻለ እውቅና በዘመኑ አግኝቷል - የኖቤል ሽልማት በማግኘት፡፡ ነገር ግን ልክ እንደማሕተመ ጋንዲ ሁሉ የጠላቶቹ ሰለባ ሆኖ በግድያ ሕይወቱ አልፏል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ፤ ከማሕተመ ጋንዲ እና ከማርቲን ሉተር ኪንግ የሚለዩት ምናልባትም በጠላቶቻቸው ባለመገዳላቸው ነው፡፡ ሁሉም የነፃነት ታጋይ መጨረሻው መገደል ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ከመድረሳቸውን በፊት ፈር መያዣ የሚሆነን የእርሳቸው ታሪክ ነው፡፡ ነገሮች ለነፃነት ታጋዮች ከድሮው እየቀለሉ መምጣቱንም ያሳየናል፡፡

የኔልሰን ማንዴላ ፓርቲ ሰራዊት ለማቋቋም የተገደደበት ጊዜ ቢኖርም ፓርቲያቸው በአብዛኛው ሲንቀሳቀስ የነበረው በስራማቆም አድማ፣ እና የተቃውሞ ሰልፎች ነበር፡፡ የተቃውሞ ሰልፎቹ እና አድማዎቹ ሁሉንም ጥቁሮች ያለመከፋፈል የሚያሳትፍ የነበረ በመሆኑ ለነጮቹ ገዢዎች የሚቋቋሙት አልነበረም፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ለዚህ የነፃነት ትግላቸው፣ ከሕይወታቸው 27 ዓመታትን ለእስር ገብረዋል፡፡ በእስር ባሉበት ወቅት ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ካቆሙ በነፃ እንደሚለቀቁ በወቅቱ ፕሬዘዳንት ቢነገራቸውም፣ ‹‹ፓርቲዬ፣ ወይም ሕዝቤ ነፃ ሳይወጣ የኔ ነፃ መውጣት ፋይዳ የለውም›› ብለው እምቢ ብለዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ፕሬዘዳንት ሲሆኑ 27 ዓመት ያሰሯቸውን ሰዎች በመበቀል፣ ወይም ለቂማቸው ትዝታ ሃውልት በማቆም ለመመጻደቅ አልሞከሩም፤ ይልቁንም ያለፈውን በመተው ስለወደፊቱ በእርቅ እና በእኩልነት መኖር ሰብከው - እውነተኛ የነፃነት ሰው መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡

በዚህም ኔልሰን ማንዴላ፣ በስተመጨረሻ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ሦስቱም የነፃነት ምሳሌዎች ተገልለዋል፣ ተገፍተዋል፣ ታስረዋል፣ ተደልለዋል፡፡ እነርሱ ግን ነፃነታቸውን ለፍርሃት እና ለግል ጥቅም ባለመለወጣቸው ክብራቸው ልቋል፣ ሽልማት እና ሙገሳ ተቀብለዋል፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ግን የታገሉለትን እና በዋጋ የማይሰፈረውን ነፃነት ለራሳቸው እና ለሕዝቦቻቸው ማምጣታቸው ነው፡፡

ሦስቱም ስለእኩልነት እና ነፃነት፣ ስለሚዛናዊ የሃብት ክፍፍል፣ ስለፀረ ዘረኝነት፣ ስለሃይማኖቶች እኩልነት በያሉበት፣ በተለያየ ቋንቋ ነገር ግን በአንድ መንፈስ ዘምረዋል፡፡ ለነርሱ ሕዝቦች እነዚያ ክፉ ጊዜያት ከሞላ ጎደል አልፈዋል፡፡ ለእኛስ?

ኢትዮጵያውያን ለውጭ ወራሪዎች እምቢተኞች ብንሆንም ለአገራችን ጨቋኞች ግን እምቢተኛ የሆንበት፣ ለገዢዎቻችን የጭቆና ቀንበር መጠናከር አንተባበርም ያልንበት፣ ለስልጣን ሽኩቻ ካልሆነ በቀር ለሕዝቦች እኩልነት እና ነፃነት ሕይወታችንን አደጋ ውስጥ የጣልነበት ታሪክ የለንም፡፡

ኢትዮጵያ አብዛኛውን ዘመኗን የጨረሰችው በእርስ በእርስ ጦርነት ነው፡፡ ለድሃ አገር ጦርነት ኪሳራ ነው፡፡ በጦርነት የሚተካ መሪም አምባገነንን በአምባገነን መተካት እንደሆነ ሕያው ምሳሌ አለን፡፡ ያለውን አምባገነንንም መጪውንም ለነፃነት ስለነፃነት የሚኖሩ ለማድረግ የሕዝቡ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፡፡ እምቢተኝነት ደግሞ አሪፉ መሳሪያ ነው፡፡ ሦስቱም ምሳሌዎቻችን የሚያምኑት ‹‹ነፃነት ከጨቋኞች የሚቸር ስጦታ ሳይሆን፣ በጨቋኞች አልጨቆንም እምቢ ባይነት የሚገኝ የትግል ፍሬ እንደሆነ ነው፡፡››

እምቢ ዘረኝነት! እምቢ ድህነት! እምቢ በስልጣን መባለግ! እምቢ አምባገነንነት! እምቢ ጭቆና! እምቢ…. እምቢ… እምቢ….

እምቢተኝነት ለዘላለም ይኑር!

2 comments:

  1. It is a very inspirational issue you raised.we have a lot work to do.Everyone one of us should internalize this strategy before rushing to any action.Finaly i disagree with you about we Ethiopian haven't had a histroy of peacful struggle.what about the 1966 E.C revolution.Eventhough it wasn't successful,it was our firt experience.

    ReplyDelete
  2. May be our past prime minister meles.

    ReplyDelete