Pages

Sunday, April 29, 2012

ከአከሌን አሰሩት እስከ አከሌን አገዱት!


ሰሞኑን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የተሰኘ እና መቀመጫውን ሰሜን አሜሪካ ያደረገ ቡድን ባጋለጠው መረጃ መሰረት INSA (Infromation Network Security Agency) በመባል የሚታወቀው መንግስታዊ ድርጅት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የ‹‹ተጠርጣሪ›› ግለሰቦችን ንግግር በመጥለፍ ሲያዳምጥ እና ሲቀዳ ይውላል ይለናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ምን እንደተከሰተ ባይታወቅም ይኸው INSA ከዚህ በፊት ከነበረው ትጋት በበለጠ በአንድ ሳምንት ብቻ ከመቶ በላይ ድረአምባዎችን እና ጦማሮችን አግዷል፡፡

የጦማር እገዳው ዘመቻ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጦማሪዎች ሲዘጋባቸው፣ አዲስ ሲከፍቱ፤ ሲዘጋባቸው፣ አዲስ ሲከፍቱ ሰንብተዋል፡፡ በፖለቲካዊ ሽሙጦቹ መንግስትን የሚያንጰረጵረው አቤ ቶክቻው (ይህንን ጽሁፍ እስከጻፍኩበት ጊዜ ድረስ ብቻ) ሰባት ጦማሮችን በመክፈት ክብረወሰን ለመስበር በቅቷል፡፡


INSA በድረአምባው ላይ በእንግሊዝኛ ያሰፈረው ተልዕኮው ‹በምርምር ላይ ተመስርተው በሚዘጋጁ መተግበሪያዎች የመንግስትንና የሕዝብን የመረጃ ስርዐቶች በብቃት ከአደጋ መጠበቅ የሚያስችል አቅም መገንባት፤› እንደሆነ ይናገራል፡፡ በራዕዩ፣ ዓላማዎቹ እና አገልግሎቶቹ ዝርዝር ውስጥ መረጃዎችን እና ድረአምባዎችን ማገድ የሚል ነገር ፈልጌ አላገኘሁም፡፡ እኔም በበኩሌ ከላይ ባስነበብኳችሁ ተልዕኮው መሠረት INSA በቫይረስ፣ በሃከሮች ወይም በሌሎች የደህንነት ስጋቶች የሚሰነዘርብኝን ጥቃት ይከላከልልኛል ብዬ ሳስብ፣ በተቃራኒው ጦማሬን በማገድ አስደንግጦኛል፡፡ እንደሕግ አክባሪ ዜግነቴ የምገፈግፈው ታክስ እኔኑ ለማፈን መልሶ መዋሉ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡

OpenNet Initiative (ONI) የተሰኘ ድምበር የለሽ ተቋም በየሃገራቱ የሚታገዱ ድረአምባዎችን ሁኔታ እና ምክንያቶች በየዓመቱ የመተንተን ስራ ይሰራል፡፡ OpenNet በማገድ ተግባራቸው ሃገራትን Pervasive Substantial Selective Suspected No evidence እያለ ከጭፍን አጋጆች እስከ ነፃ የሚባሉትን ይመድባል፡፡ በዚህ ምድቡ፣ ያውም የዚህ ሳምንቱ ጉድ ከመሰማቱ በፊት ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያን Substantial የተባለው ምድብ ውስጥ አስቀምጧታል፡፡

ኢትዮጵያ የነበረችበት ምድብ (የነበረችበት የምለው በዚህ ሰሞን አካሄዷ Pervasive የተሰኘውን እና ተቃራኒ ሐሳብ ለማንሳት የሚዳዳቸውን ሁሉ ከማገድ የማይመለሱት ምድብ ውስጥ ትቀላቀላለች የሚል እምነት ስላለኝ ነው፤) እናም በነበረችበት ምድብ ውስጥ በተወሰነ የፖለቲካ ርዕስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ድረአምባዎች ወይም ጦማሮችም እንደሚታገዱ OpenNet ይናገራል፡፡

ሕገ መንግስቱን እናስታውሳቸው!
መንግስት ካወጣው በኋላ የዘነጋውን ሕገመንግስት እንከን አልባ እንደሆ ይዘምርለታል፡፡ እኛ ግን አማራጭ የለንምና ከነእንከኑም ቢሆን እየተገዛንለት እንገኛለን፡፡

የሕገመንግስቱ አንቀጽ 29/2 ‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል› ይላል፡፡

ይኸው ሕገ መንግስት ‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣› እና ሕዝብ ‹ጥቅሙን የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድል› እንዳለው ያስቀምጣል፡፡

እነዚህ መብቶች ከወረቀት ወደመሬት ወርደው ማየት የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘወትር ምኞት ነው፡፡ ምክንያቱም እውነታው፡-
  • የመንግስትን ሥራ የሚናገሩ (ወይም ከውዳሴ በቀር ሌላ ጉዳይ /ለምሳሌ ድክመቱን እና ስህተቱን/ ስለመንግስት የሚያወሩ ወይም ከገዢው ፓርቲ ውጪ ሕዝቡ አማራጭ እንዳለው የሚጠቁሙ) ግለሰቦች እና የዜና ምንጮች ይታሰራሉ፣ ይታገዳሉ፡፡
  • አሁን ደግሞ፣ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲሱ የሕትመት ሥራ ውል ላይ ማተሚያ ቤቱ አሳታሚዎቹ ለሚያወጡት ጽሁፍ ይዘት በሕግ ተጠያቂ አይሆንም ካለ በኋላ፤ ለሕትመት የሚቀርብለት ጽሁፍ ሕግን እንደሚጥስ በቂ ማስረጃ ካለው አላትምም የማለት መብት አለው እያለ ነው፡፡ ማለት ‹‹የተከለከለውን›› ቅድመ ምርመራ አድርጎ ሲያበቃ ማለት ነው! (አንቀጽ 9 እና 10)

ዴሞክራሲ በሒደት እንደሚያድግ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት አበክረው እየነገሩን ነው፡፡ በርግጥ እኔም በአባባሉ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲ በሒደት አያሽቆለቁልም፡፡ መረጃ የማግኘትን እና የመስጠትን ነጻነትን ከመቀማት የበለጠ የዴሞክራሲ ማሽቆልቆል ሊመጣ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሟጠጠ ወርዶ አሁን ስሙ ራሱ በቴሌቪዥን ከተነሳ ከርሟል፡፡

ነገር ግን አሁንም እንዲህ እላለሁ፤ በዴሞክራሲ ተስፋ ያልቆረጣችሁ፣ ነጻነታችሁን አሳልፋችሁ ላለመስጠት የቆረጣችሁ ጦማሪ ወዳጆቼ ሆይ - ከ‹አንድ ብርቱ› ነውና ተረቱ - ኑ መንግስትን እንክሰሰው!!!

1 comment:

  1. Yes my taxpayer money is filling these chinese hackers pocket.shame on our rulers who ones said they were fighting to remove mercyless dictator.and for that couse thousend and thousends lives had been sacrificed.After all that you preach us to choose bread than democracy.HELLO we didn't still find thd bread on the table three times a day after 20 years.

    ReplyDelete