Pages

Wednesday, April 1, 2026

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስምንት ዓመታት በሥልጣን ማማ ላይ

(በበፍቃዱ ዘ. ኃይሉ)

ዐቢይ አሕመድ ተቃዋሚ መስለው፣ ተቃዋሚ ለብሰው ሥልጣን ከተቆናጠጡ እነኾ ዛሬ ድፍን ስምንት ዓመታቸው።

ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወዲህ በየሁለት ዓመቱ አስተዳደራቸውን የሚገመግም መጣጥፍ እየጻፍኩ ነው። ዘንድሮም ባሕሉን ለማስቀጠል ይህንን መጣጥፍ እነኾ ብያለሁ። በቅድሚያ የቀደምት ጽሑፎቼን ዐውድና ምላሽ በጨረፍታ ላስታውሳችሁ።


ዐቢይ አሕመድ በሥልጣን ጎዳና ሁለት ዓመት ሲሞላቸው በጻፍኩት ጽሑፍ  ሃይማኖታዊ ሰበካን ከአነቃቂ ንግግር ጋር በሚቀይጥ የንግግር ዘይቤያቸው አታላይ አንደበት አባታዊ (paternalistic) አገዛዝ ስርዓት እንደገነቡ ለመከራከር ሞክሬ ነበር፤ ክርክሬ መንግሥታቸው እኛን ዜጎቹን ልክ በራሳቸው መወሰን የማይችሉ ሕፃናት ይመለከተናል የሚል ነበር። ይህንን ጽሑፍ በጻፍኩበት ወቅት ዐቢይ አሕመድ በመሐል አገር ከፍተኛ ድጋፍ ስለነበራቸው፣ ምንም እንኳን ትችቴ የመረረ ሊባል የሚችል ዓይነት ባይሆንም እንዲህ ያለ ትችት ከመሐል አገር ሰው ጭራሹኑ አልተለመደም ነበርና ከአንዳንድ ወዳጆቼም ሳይቀር ብዙ ነቀፌታዎችን አስከትሎብኝ ነበር። 


አራት ዓመት ሲሞላቸው የጻፍኩት ግን በተቃራኒው የመረረ ትችት ሊባል የሚችል ነበር። “ከድጡ ወደ ማጡ” የሚል ርዕስ የሰጠኹት ሲሆን፣ መጀመሪያ በፍትሕ መጽሔት ላይ የሽፋን ገጽ ታሪክ (cover-story) ሆኖ ታትሟል። ከዚያም በብዙ ዩቱብ ገጾች ተባዝቷል። በወቅቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የገባችበት ነበር። የእርሳቸውን አራት ዓመታት ስገመግመው፣ ዐቢይ አሕመድ የብልፅግና ፓርቲ ብቸኛ ሰው መኾንን “ፓርቲው ራሳችው ናቸው” በሚል በመግለጽ - ወደ ፈላጭ ቆራጭነት ማደጋቸውን፣ ትግራይ ከኢትዮጵያ ወደ መሰናበት እያመራች መሆኗን፣ ኦሮሚያ አኬልዳማ ሊያስብላት የሚያስችል በታጣቂዎችና መንግሥት መሐል የተያዘ ሕዝብ መኖሩን፣ እና የሕግ የበላይነት መንኳሰስ እና የነውጠኝነትን መንሰራፋት (እንዲሁም  የእርሳቸውን አመራር “የነውጥ ቀዛፊነት” በሚል) ጠቅሼ - ለዚህ ሁሉ ዋናው ተጠያቂው እርሳቸው መሆናቸውን ደምድሜ ጻፍኩ። ይህን ጊዜ ብዙ ወዳጆቼ “ክክፉ ይጠብቅህ” ከማለት በቀር ከድምዳሜዬ እምብዛም የተለየ ድምዳሜ አልነበራቸውም። 


ስድስት ዓመት ሲሞላቸው “እየሰጡ መንሳት” የዐቢይ አሕመድ የአመራር ዘይቤ ነው የሚል ትንታኔ ጻፍኩ። በስድስት ዓመታት አስተውሎቴ፣ ዐቢይ አሕመድ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና እንቅስቃሴያቸው የታሰሩ ሰዎችን ሲፈቱ አይተናል፤ መልሰው ደግሞ የርሳቸውን ፖለቲካ የሚቃወሙ ሰዎችን በየሰበብ አስባቡ በመንግሥታቸው ሲያሳስሩ አይተናል። ብዙኃንን ያስፈነደቁ የሰላም ስምምነቶች ውስጥ ሲገቡ አይተናል (ኤርትራ፣ ትግራይ)፤ እነዚያ የሰላም ሥምምነቶች መልሰው ውኃ ሲበላቸው አይተናል። እነዚህ እና መሰል የአመራር ዘዬአቸው መገለጫ  - እየሰጡ መንሳት - ሊባል እንደሚገባ ትንታኔዬን አቅርቤያለሁ። ይሄም ጽሑፍ በመጠኑ አንባቢ አግኝቷል። ተባዝቷልም።  


ዐቢይ አሕመድ አሁንም ገና እየተገለጡ ነው።  ትንታኔያችንም ይቀጥላል።


Lost in Transition” ባሰኘሁት መጽሓፌ ውስጥም የዐቢይ አሕመድ አነሳስ (The Rise of Abiy Ahmed) በሚል ርዕስ የ18 ገጽ ትንታኔ አስቀምጫለሁ። በዚህ ትንታኔዬ ዐቢይ በምን ዓይነት ውስጣዊ እና ውጪያዊ ትግሎች ወደ ከፍተኛው የሥልጣን ማማ እንደተወጣጡ ለመተንተን ሞክሬያለሁ። ዐቢይ አሕመድ በብዕር ሥም ያሳተሙትን “እርካብና መንበር” አንብቤያለሁ። በሥማቸው ያሳተሟቸውን “የመደመር” ተከታታይ መጽሓፎችንም አንብቤያለሁ። ቶም ጋርድነር “The Abiy Project” በሚል ርዕስ የጻፈውን ባለ ትልቅ ጥራዝ መጽሓፍም አንብቤያለሁ። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እየሰበሰቡ የሚያደርጓቸውን ንግግሮችም እያሳደድኩ፣ ጊዜ በፈቀደልኝ ቁጥር ላደምጣቸው ሞክሬያለሁ። በነዚህ ሁሉ ንባቦቼ የተረዳሁት ዐቢይ አሕመድ የፈለጉትን ከማድረግ ምንም የማያስቆማቸው ሰው መሆናቸውን ነው ማለት እችላለሁ። ከዚህ በታች የምጽፈው እና ከዚህ ውጪም የምሰጣቸው አስተያየቶች በነዚህ ጥረቶቼ የወሰድኳቸው ግምገማዎቼ መሆናቸውን ቀድሜ ለማሳወቅ እወዳለሁ። 


ከ“ቲም ለማ” ወደ “መጋቢታውያን”


ለውጡን ስታስቡ ከ"ቲም ለማ" ውጪ ማሰብ ትችላላችሁ? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ይችላሉ። “የመደመር መንገድ” የሚለው መጽሐፋቸው ስለለውጡ አመጣጥ የሚተነትን ነው። ዐቢይ ለውጡን ለማምጣት የዐሥር ዓመት ሴራ እንደተሠራ ይናገራሉ። አምናቸዋለሁ። ከባድ ሚዛን “የሸዋ ፖለቲካ” ተጫዋች ናቸው። በአንድ እግራቸው ከገዢው ፓርቲ መንደር፣ በሌላ እግራቸው ከተቃዋሚዎች መንደር ቆመው ነው ጨዋታውን የተጫወቱት፤ ለዚህ ነው መግቢያዬ ላይ “ተቃዋሚ መስለው፣ ተቃዋሚ ለብሰው” የሚል ገለጻ የተጠቀምኩት። እንደ እርሳቸው አባባል እኛ “አሮማራ” የምንለው ሕወሓትን ለመገርሰስ የተፀነሰው ትብብር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ ራሺያ ሲጓዝ በዐቢይ እና ደመቀ የተጠነሰሰ ሴራ ነው። ስለዚህ ለለውጡ፣ የለማ መገርሳ ሚና እምብዛም እንዳልነበር እንደዋዛ ታልፏል። የመደመር መንገድ መጽሐፍ የለማን ስም አንድ ሁለቴ እንደዋዛ (anecdote) አንስቶ ነው የሚያልፈው። ይልቁንም መጽሓፉ ላይ ደመቀ መኮንን የተሻለ ተጠቅሰዋል። ዐቢይ፣ በዚህ መጽሐፍ ላይ “ቲም ለማ” የሚለውን የለውጥ ቡድን መጠሪያ ስም፥ “መጋቢታውያን” በሚል ሊተኩት ሞክረዋል። መጋቢት፣ እርሳቸው የተመረጡበት ወር ነው። በርግጥ ደመቀ መኮንን ከእጩነት ራሳቸውን ባልተጠበቀ መንገድ ባያገልሉ ኖሮ፣ ዐቢይ አሕመድ በሰፋ የድምፅ ብልጫ የማሸነፍ ዕድላቸው አጠያያቂ ይሆን ነበር፤ ስለዚህ የደመቀ መኮንንም መጠቀስ ትርጉም ይሰጣል። የለማ መገርሳ ግን እንደዋዛ ከታሪኩ መፋቅ በጣም አስገርሞኛል። ዐቢይ "ቲም ለማ" ከሚለው ይልቅ "መጋቢታውያን" የሚለውን መጠሪያ የወደዱት በለማ ስም መጠራቱ የእርሳችውን ሚና የሚያሳንስ ስለመሰላቸው ወይስ ከለማ መገርሳ ጋር መንገዳቸው ስለተለያየ?

ከ[ቀዳማዊ] ኢሕአዴግ ወደ ብልፅግና (ራብአዊ ኢሕአዴግ)


ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በፊት እና በኋላ አንድ አይደለም። ከምርጫ 97 በፊት ትርፍና ኪሳራው ሲወራረድ በዴሞክራሲያዊነት ረገድ ቀዳማዊ ኢሕአዴግ አዎንታዊ ደረጃዎችን አስመዝግቧል። ነፃ ሚዲያዎች እና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰፊው የሚንቀሳቀሱበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው የሚወጡበት ምኅዳር ፈጥሮ ነበር። ከምርጫ 97 በኋላ ያንን ምኅዳር መልሶ መቀልበስ ጀመረ፤ አሳሪ ሕጎች ወጡ፣ ዜጎች በፍርሐት ካቴና ታሰሩ። የተቃውሞ ፖለቲካ (opposition politics) ወደ እምቢተኝነት ፖለቲካ (resistance politics) ተቀየረ እና የ2010ሩ ለውጥ መጣ። ለውጡ የመጣው በተቃውሞ ግፊያ ቢሆንም፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ከተደረገው ውስጣዊ ትግል ውጪ እውን ሊሆን አይችልም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተመረጡት በኢትዮጵያ ሕዝብ አልነበረም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ አልታደለም። ይልቁንም፣ በኢሕአዴግ ውስጥ በነበረ የፓርቲ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው። ኢሕአዴግ እስከ 2011 አጋማሽ ድረስ ግንባር ሆኖ ዘልቋል። 


ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ “ጠርዝ ላይ” በሚል ባሳተሙት መጽሓፍ ሁለቱን ኢሕአዴጎች ሲያወዳድራቸው “ቀዳማዊ ኢሕአዴግ” እና “ዳግማዊ ኢሕአዴግ” በሚል ጠርተዋቸው ነበር። ነገር ግን የኢሕአዴግ አገዛዝም ቢሆን ቅድመ እና ድኅረ ምርጫ 97 መካከል ልዩነት ስለነበረው፣ የቅድመ ምርጫ 97ቱን “ቀዳማዊ” እንበለው፣ የድኅረ ምርጫ 97ቱን ደግሞ እስከ 2010 “ዳግማዊ” እንበለው እና ከ2010 እስከ ብልፅግና ያለውን “ሳልሳዊ” እንበለው። ቀዳማዊ ኢሕአዴግ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ያልነበረው፣ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ባሕሎችን ያለማመደ ግንባር ነበር። ዳግማዊ ኢሕአዴግ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊነቱ እየጎለበተ የመጣ (ምሳሌ የሕወሓት የበላይነት እየተሞገተ የነበረበት እና የሥልጣን ክፍፍል በግንባሩ አባላት መካከል እየተስተካከለ የነበረበት እና ለአዲሱ የኢሕአዴግ ትውልድም ሥልጣን ማጋራት የጀመረበት ጊዜ ነበር)፣ ነገር ግን አገራዊ አፋኝነት የተፋፋመበት (ለምሳሌ ቢሮክራሲው እና ፓርቲው የተጋቡበት) ነበር። ሳልሳዊ ኢሕአዴግ ደግሞ ከድኅረ 97 በኋላ የነበሩ ጥፋቶች እርምት የሚመስል እርምጃ የተወሰደበት ነበር። እስረኞች ተፈቱ፣ አፋኞቹ ሕጎች መከለስ ጀመሩ፣ ያኮረፉ የፖለቲካ አካሎች ለእርቅ ተጋበዙ፣ የተሰደዱ ተመለሱ፣ የተጣሉ ታረቁ፣ ፓርቲውና ቢሮክራሲው ተፋትተው ባለሙያዎች (ሜሪቶክራቶች) በገፍ ተቀጠሩ (የፓርቲ አባላት ያልሆኑ ባለሙያዎች ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው በገፍ የተቀጠሩበት ጊዜም ነበር)። ይህ ግን የቀጠለው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፤ ከዚያ ራብአዊ ኢሕአዴግ ተወለደ። ሳልሳዊ ኢሕአዴግ ብዙ አሳይቶናል፤ ተስፋም ሰጥቶን ነበር። ግን ዕድሜው አጭር ነው።


ራብአዊ ኢሕአዴግ (ብልፅግና ፓርቲ) ኢሕአዴግ እና አጋሮቹ ሲቀነስ ሕወሓት ማለት ነው። ዛሬ ብልፅግና ውስጥ የምናያቸው ቁልፍ ሰዎች፣ ከጥቂት በሳልሳዊ ኢሕአዴግ ጊዜ ከተቀላቀሉት እንግዶች በቀር ነባር ኢሕአዴጋውያን ናቸው። ስለዚህ ብልፅግና ሙሉ ለሙሉ ከኢሕአዴግ የተነጠለ አድርጎ ማሰብ ስህተት ይሆናል። ይልቁንም፣ ሌሎቹ የግንባሩ አባሎች የሕወሓት ታናሽ (junior) አጋር ተደርገው ይታዩ ነበር። ዛሬ የብልፅግና መሠረት ሆነው የምናያቸው እነዚህን ነው። ዐቢይ አሕመድም የኢሕአዴግ ሚኒስትር እስከመሆን የደረሱ ጉምቱ ናቸው። ነገር ግን ይህንን ታሪካቸውን ማረሳሳት ችለዋል። ዕድሜ የሕዝብን ቀልብ ለገዛው ሳልሳዊ ኢሕአዴግ!


ራብአዊ ኢሕአዴግ የቀዳማዊ ኢሕአዴግን ውስጠ ፓርቲ አፋኝነት እና የዳግማዊ ኢሕአዴግን አገራዊ አፋኝነት አጣምሮ ይዟል። በራብአዊ ኢሕአዴግ ውስጠ ትግል አድርጎ መሪ መለወጥ ቢያንስ በቅርቡ አይቻልም። በቀዳማዊ ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራትነት፣ በዳግማዊ ኢሕአዴግ ልማታዊ መንግሥትነት መንግሥታዊ ዲስኩር ነበር፤ እነዚህኞቹን ኢሕአዴጎች ምን፣ እንዴት፣ ለምን እንደሚወስኑ መገመት (predictability) ትችላላችሁ። በሳልሳዊ ኢሕአዴግ ሊበራሊዝም መሰል ነገር፣ በራብአዊ ኢሕአዴግ ደግሞ “ሰንበሌጣዊነት” ይስተዋላል፤ ብልፅግና ርዕዮተ ዓለም የለውም። ይህንን ፓርቲው በይፋ አውጆታል። ይህንን አንድ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር “ሰንበሌጣዊነት” ይለዋል፤ በነፈሰበት መንፈስ። አንዳንዴ “መደመር” የሚባል ዲስኩር ርዕዮተ ዓለምን ሊተካ ይሞክራል። ነገር ግን አንድም ምሁር በመደመር “ፍልስፍና” የብልፅግናን ፖለቲካ ለመተንተን አይሞክርን። ምክንያቱም ሐሳቡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ከመንፈሳዊ አነቃቂ ንግግርነት አያልፍም።


ግን ደግሞ በነፈሰበት መንፈስ ስንል ራብአዊ ኢሕአዴግ ድርቅ የሚልባቸው አቋሞች የሉም ማለት አይደለም። በሥልጣኑ እና በከተማ ውበት ጉዳይ ከማንም ጋር አይደራደርም - ፓርቲው፣ AKA መሪው፣ ዐቢይ አሕመድ። የሆነ ሆኖ ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ መሪ ቀይሯል። ብልፅግና በውስጣዊ ትግል መሪ መቀየር የሚችል ይመስላችኋል? እኔ ግን ይኼ የሚሆንበት ዕድል በቅርብ ርቀት አይታየኝም።


ከለውጥ ወደ ነውጥ 


የ2010ሩ ክስተት መጀመሪያ የመንግሥት ለውጥ ነበር። ነገር ግን ዘመኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚሉት 'የለውጥ' ከሚባል ይልቅ የ'ነውጥ’ ቢባል የተሻለ የሚያስኬድ ይመስለኛል።


ነውጡ የጀመረው ግለሰቦችን በድንጋይ በመውገር እና በአደባባይ ላይ ዘቅዝቆ በመስቀል በታጀበ የመንጋ ጥቃት (mob violence) ሲሆን፤ በመቀጠልም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለ ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት፣ ከዚያም የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትን እና የካቢኔ አባሎቻቸውን፣ እንዲሁም አባ ቶርቤ በተባለ ገድሎ አደር የኅቡዕ ድርጅት የሚገደሉ ባለሥልጣናት፣ ከዚያም ታዋቂውን የኦሮሚያ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመሳሰሉ ግለሰቦች ላይ ባነጣጠረ የፖለቲካ ግድያ ተስፋፍቶ፣ በስተመጨረሻም በትግራይ ወደተካሄደው ሙሉ ጦርነት አምርቷል። የትግራዩ ጦርነት በሰላም ሥምምነት የተጠናቀቀ ቢመስልም፣ ይህንኑ ተከትሎ በአማራ ክልል በታጠቁ ቡድኖች እና በመንግሥት መካከል ውጊያ ፈንድቷል። በኦሮሚያም በታጠቁ ቡድኖች እና በመንግሥት መካከል የሚደረገው ውጊያ ከትግራዩ ጦርነት በፊት ጀምሮ እስካሁንም ቀጥሏል። በመሆኑም የሽግግሩን ጊዜ የሚገልጸው "ነውጥ" የሚለው ቃል ነው ማለት ተገቢነት አለው።


ለዚህ “ዘመነ ዕብደት” ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለብቻቸው ተጠያቂ ማድረግ አግባብ አይደለም፤ ሁላችንም የየራሳችን ድርሻ አለን። ነገር ግን ዋነኛ ተጠያቂ እርሳቸው ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የደቦ ፍርዶች እና የደቦ ፍርዶችን የሚቀሰቅሱ ንግግሮቻቸው መሳ ለመሳ መሔዳቸውን አስተውያለሁ። በመጽሐፌ እንዳመለከትኩት፣ እርሳቸው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወጥተው ወጣቶች አካባቢያቸውን "ከፀጉረ ልውጦች" እንዲጠብቁ ባሳሰቡ ጥቂት ቀናት ውስጥ የጀመሩ የደቦ ፍርዶች ወደ ወል ግጭቶች አድገው ለወራት ዘልቀዋል። በወቅቱ የመንግሥታቸው ትርክት በአንድ በኩል ለሁሉ ነገር ሕወሓት ላይ ጣት የሚቀስር፣ ካልሆነ ደግሞ ታስሮ የቆየ ብዙኃን ነፃነት እና ዴሞክራሲን መሸከም እንዳቃተው የሚያመላክት ነበር፤ ይህም የሕግ የበላይነት ማስከበር የነበረበት መንግሥት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ የተከሰተውን ቀውስ ለማስቀየሻነት የዋለ ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ፣ ነውጡ እና ሁካታው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃይል ማከማቻነት ውሏል። ያሻቸውን እርምጃ ቢወስዱ፣ ማንም ምንም የማይታዘባቸው ወቅት ነበር።


ይህ በእንዲህ እንዳለ ነውጦቹ ስፋታቸው እያደጉ መጡ። የሚያስገርመው ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ነውጡን ጀመረውም አልጀመረውም፣ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ግን ሥልጣኑን ለማጠናከር ሁሉንም አጋጣሚዎች ተጠቅሞባቸዋል። መንግሥታቸው የ[መንጋ] ጥቃት መስፋፋትን የሕግ የበላይነትን ወደ ጎን ለማለት እንደ ማመካኛ ተጠቅሞበታል። በስምንት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውም ሦስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን አውጀዋል። መንግሥት ውይይት እና ድርድርን ከማድረግ ይልቅ ነውጥን እንዲመርጥ በማበረታታት፣ ነውጥን ሥልጣኑን ለማጠናከር እንዴት እንደተጠቀመበት ተጨማሪ ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት።


አንደኛ፣ መንግሥት በኦሮሚያ የተከሰተውን ነውጥ ዋነኛውን የኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲ የሆነውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እንዲከፋፈል ለማድረግ እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ለማዳከም ለሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደ ማመካኛ ተጠቅሞበታል። በርካታ የኦነግ አመራሮች ፍርድ ቤት በነፃ ካሰናበታቸው በኋላ ለበርካታ ወራት በእስር ላይ ቆይተዋል። ይህንን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችም ያረጋገጡት ነገር ነው። በምርጫ 2013 ኦነግ እና ኦፌኮ ከምርጫ “ተገፍተናል” ብለው ሲወጡ የሰጡት ምክንያት እነዚህን ክስተቶች ሽፋን በማድረግ የብልፅግና መንግሥት አባላት እና አመራሮቻችንን አስሯል፣ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻችንን ዘግቷል፣ መጫወቻ ሜዳችንን አጥብቧል በሚል ነበር።


በ2012 የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ነውጥ ምክንያት በማድረግ እንደ ጃዋር መሐመድ (ከኦፌኮ) እና እስክንድር ነጋ (የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ) ያሉ ታዋቂ የተቃውሞ መሪዎችን መንግሥታቸው አስሯል። እነዚህ ሁለቱ ግለሰቦች በቅደም ተከተል በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ትልቅ ተቃውሞን ሊመሩ ይችሉ ነበር። እነሱ በእስር ላይ እያሉ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን በአብላጫ ድምፅ አሸንፏል (በወቅቱ በኦሮሚያ ሁሉም ተቃዋሚዎች ተደምረው ያቀረቡት የእጩ ብዛት ከጠቅላላው የእጩዎች ብዛት 35% ብቻ ነበር፤ በኦሮሚያ ብልፅግና ብቻውን ነበር የተወዳደረው ቢባል ማጋነን አይደለም)። ከዚያም ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ እስር በኋላ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክሳቸውን በማቋረጡ ጃዋር እና እስክንድር እንዲሁም አብረዋቸው የተከሰሱ ግለሰቦች ከእስር ያለ ፍርድ ተፈትተዋል። ይህም መንግሥት አስቀድሞ ግቡን ስላሳካ ተጠርጣሪዎቹን እስር ቤት ማቆየት የማይፈልግበት ሰዓት ሲደርስ እንደለቀቃቸው ያስጠረጥራል። በዚህ መሐል የተዘነጋው 200 ያህል ሕይወት የቀጠፈውን ነውጥ ተጠያቂ አካል አለመኖሩ ነው። 


አሁን ላይ እስክንድር ነጋ በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል መሪዎች አንዱ ሲሆን፣ ጃዋር ደግሞ በዳግም ስደት ወደ በይነመረብ አክቲቪዝም ተመልሷል። በመሆኑም ሁለቱም በለውጡ ሰሞን ከቀሰቀሱት ሕዝባዊ መሠረታቸው በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲርቁ ተደርገዋል።


ሌላኛው ምሳሌ የትግራይ ጦርነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ ሕወሓትን እና አጋሮቹን ከመንግሥት ቢሮክራሲ እና ከደኅንነት መዋቅሩ አስወግደዋል፤ ይህ ማለት መንግሥታቸው ክፍት የሆኑትን ቦታዎች በታማኞቹ በመተካት በመንግሥት ሥርዓቱ ውስጥ ሊገጥመው የሚችለውን ተግዳሮት ቀንሷል ማለት ነው። በተጨማሪም መንግሥታቸው የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ሚዲያዎችን እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ዒላማ ባደረጋቸው አካላት ላይ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያካሒዳል። እንዲሁም የደኅንነት መዋቅሩን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል። አሁን፣ የትግራይ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወቶችን ከቀጠፈ በኋላ በሰላም ስምምነት (ለጊዜው) ተጠናቋል፤ እርግጥ ነው ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ ሌላ ጦርነት ሊጀመር ይችላል የሚል ስጋት በሰፊው እያንዣበበ ነው። የሆነ ሆኖ፣ ከጦርነቱ በፊት ሕወሓት የነበረው አቅም አሁን ሞቷል። ሕወሓት ለዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ይኼ ነው የሚባል ስጋት አይፈጥርም።


ነገር ግን የዐቢይ መንግሥት አሁንም ሕወሓቶችን ለመውጋት አጋር እንዲሆኑት የታገሳቸው ኃይሎች ይቀሩ ነበር። ዐቢይ አሕመድ ከመምጣታቸው በፊት የነበሩት ክልላዊ ልዩ ኃይሎች የሶማሊ ልዩ ኃይሎች ብቻ ነበሩ። ከዐቢይ አሕመድ መምጣት በኋላ ግን ልዩ ኃይሎች በየክልሉ ፈሉ። ልዩ ኃይሎቹ በርግጥም ለአገራዊ ሰላምም፣ ለመንግሥት ሥልጣንም አደጋ ነበሩ (የአማራ ክልል መሪዎችን መገደል፣ በሶማሊና ኦሮሚያ ክልሎች ድንበሮች የነበሩ ግጭቶች፣ አፋር እና ሶማሊ፣ ወዘተ ዋቢ አርጎ መጥቀስ ይቻላል)። ነገር ግን ለትግራይ ጦርነት አጋር እንዲሆኑ ሲባል ቸል ተብለው ነበር። በተጨማሪም እንደ “ፋኖ” ያሉ ታጣቂ ቡድኖችም በይፋ ወደ ጦርነቱ ተጋብዘው ነበር። ችግሩ የመጣው ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ነው። ታዲያ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ትኩረቱን ወደ እነዚህ በመቀየር፣ በድንገት መበተናቸውን አሳወቀ። ይህም በተለይ በአማራ ክልል ዛሬ ለተገባበት አሰቃቂ ውጊያ ምክንያት ሆነ። የትግራዩም ይሁን የአማራ ክልሎቹ ውጊያዎች፣ ቢያንስ እስካሁን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ይልቅ የክልሎቹን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁመና ነው ያናጉት። እያንዳንዱ ነውጥ እና ነውጥ አዘል ግጭት በእርሳቸው ሥልጣን ዙሪያ ያደረሰው ጉዳይ ምናልባት የገጽታ እንጂ የኃይል ሚዛን መዛባት አይደለም።


እነዚህን ኹነቶች ስንገመግም  'ለውጡ' ከሚለው ቃል እኩል ውይም በላይ 'ነውጡ' የሚለው ቃል ዘመናቸውን ይገልጸዋል። ለውጡ ነውጡ ነው።


ለትንታኔ አስቸጋሪው ዐቢይ


ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡበት ዘመን በማኅበራዊ ሚዲያ አተራማሽነት (disruption) ሲጦዝ፣ እንዲሁም የምዕራባውያንን ኃያልነት በምሥራቃውያን ኃያልነት (ቻይና) ተግዳሮት ሲገጥመው ነው። በመሆኑም ዘመኑ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ዐቀፍ ወጀቦችም የታጀበ ነው። በዚያ ላይ በ2012 የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ የዓለምን ኢኮኖሚ አናውጦታል። ዐቢይ የተወዳጇቸው የዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ መሪዎች ጨምሮ የመካከለኛው ምሥራቅ ሰዎችም አካባቢያዊ ተፅዕኗቸውን ያሳደጉበት ዘመን ላይ ነን። ኢትዮጵያም ደሴት አይደለችም፤ ዓለማችን መርከብ ከሆነች እና ወጀብ ከመታት አብራ ትናጣለች። ከዓለም ዐቀፍ ትርምሶች ታተርፋለችም፣ ታጎድላለች።

 

ይህ በእንዲህ እያለ፣ እስራኤል እና አሜሪካ ኢራን ላይ ጦርነት ሲያውጁ፣ የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተንታኞች (Ethiopia experts) ‘ዐቢይ ይህንን አጋጣሚ ከለላ አድርገው ኤርትራ ላይ ጦርነት ያውጃሉ’ በማለት ተነበዩ። ይህንን የተነበዩት በብዙ ምክንያቶች ነው። አንደኛ፣ ዐቢይ በነውጥ ቀዛፊ ስለሆኑና፣ ከነውጥ ውስጥ ጥቅማቸውን ፈልቅቀው እንደሚያወጡ እርሳቸውም የማይደብቁት ጉዳይ በመሆኑ  ነው። በቅርቡ እንኳን በዓለም ዙሪያ ስላንዣበበው የግጭት አደጋ ሲጠየቁ እኛ የሚጠበቅብን ከግጭቶቹ ውስጥ ዕድል (opportunity) ፈልቅቀን ማውጣት ነው ብለው ነበር። ሁለተኛ፣ ዐቢይ የትግራይ ጦርነት በሥምምነት ሲቋጭ ከተኳረፏቸው የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል፤ ይኸውም የባሕር በር ጥያቄን ግንባር ቀደም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አጀንዳ አድርጎታል። ምንም እንኳን የባሕር በር የምናመጣው “በሰላም ነው” እያሉ ቢዝቱም ማንም አላመናቸውም። ጉዳዩን በሰላም ለማድረግ ብዙ ዲፕሎማሲ የሚጠይቅ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን እርሳቸው ኃይልን እንደ ሁነኛ የችግር መፍቻ መንገድ ይመለከቱታል ተብሎ ስለሚታመን ነው - ተንታኞቹ እንዲህ ማሰባቸው። ሦስተኛ፣ የትግራይ ጦርነት የጀመረው ልክ የአሜሪካ ምርጫ የተካሔደበት ቀን ስለሆነ፣ የዓለም ትኩረት አቅጣጫ ሌላ ሰፈር ሲሆን፣ ዐቢይ አሕመድ የሆነ ነገር ያደርጋሉ ብለው ገምተው ነው። ነገር ግን ትንቢታቸው አልሠራም። 


የኢራን ጦርነት ከጀመረ ከሁለት ሦስት ቀናት በኋላ ተንታኞቹ “ትንቢታቸው ለምን እንዳልሠራ” በመተንተን ፈንታ፣ ዐቢይ አሕመድ ለምን ጦርነቱን እንዳልጀመሩ ለመተንተን ሞክረዋል። ዐቢይ አሕመድ እንኳን በአስተርጓሚ እገዛ እና በእንግሊዝኛ ዜና መነፅር የሚመለከቷቸውን ሰዎች ቀርቶ እኛ በየቀኑ የሚሠሩትን እያየን፣ የሚናገሩትን እያደመጥንም ቢሆን ለትንታኔ ያስቸግሩናል። እዚህ ጋር ተንታኞቹ የሠሩት አንዱ ስህተት ዐቢይ አሕመድ ራሳቸው እንደተናገሩት ከግጭቶች ጥቅም ፈልቅቀው ያወጣሉ፤ ለፖለቲካ ዓላማቸው የትኛውንም አካል ወደ ነውጥ ይገፋሉ። ነገር ግን ግጭቶችን ራሳቸው እንደሚጀምሩ አንድም ማስረጃ የለንም። የምዕራብ ተንታኞች ከገመቱት በተቃራኒው የትግራይን ጦርነት ሁለቱም ወገኖች በትርዒት እና ፉከራ ሲቀሰቅሱት ቆይተው፥ የመጀመሪያውን ጥይት የተኮሱት ራሳቸው ሕወሓቶች ናቸው። ከዚያ አስቀድሞ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) እና መንግሥት መካከል ውጊያ የተጀመረው በራሱ ትጥቅ አልፈታም ብለው ባመፁ የኦነሠ አባላት ነው (ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረውን ስምምነት ዝርዝር ባይታወቅም፣ በአንድ አገር ውስጥ ቅቡልነት ያለው ታጣቂ ኃይል መንግሥት ብቻ መሆኑን መከራከር አንችልም)። በፋኖ እና በመንግሥት መካከልም የተጀመረው ጦርነትም መነሻው ልዩ ኃይል መፍረስ የለበትም ብለው ባመፁ የፋኖ ታጣቂዎች ነው። ጦርነቱን ዐቢይ ናቸው ያወጁት ተብሎ ብዙ ክርክር ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን እርግጡ ነገር ከሁሉም ግጭቶ እርሳቸው ሥልጣናቸውን ከትላንት የተሻለ ዛሬ ለማደላደያነት እንደተጠቀሙባቸው ብቻ ነው። 


አንድ የእንግሊዝ ዲፕሎማት ዐቢይ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን የተሰማቸውን ለተመራማሪዎች እንደተናገሩት፣ “Abiy was a disruptor… He was changing everything all the time… Ethiopians couldn’t keep up; we could not keep up.” (“ዐቢይ ማርሽ ቀያሪ ናቸው። … ሁሌም ሁሉንም ነገር እየቀያየሩት ነበር።… ኢትዮጵያውያንም በሳቸው ፍጥነት ምን እያደረጉ እንደሆነ ማወቅ አልቻሉም፣ እኛም አልቻልንም።” ዓይነት ነገር) ብለው ነበር። በዚህም “የነውጥ ቀዛፊው” ዐቢይ አሕመድ እስከ የሰላም ኖቤል ተሸላሚነት ደርሰዋል።  


ዐቢይ አሕመድ ነገሮችን በማይታመን ፍጥነት ማድረግ ይወዳሉ። ወደ ሥልጣን የወጡ ሰሞን በየቀኑ ሰበር ዜና ይሰጡን ነበር፤ አንዱን አውርተን ስንጨርስ ሌላኛው ይቀጥላል። በዚህ መሐል እርሳቸው ሥራቸውን ይሠራሉ፤ አንድም ሰው ከሰበር ዜና ጠለቅ ብሎ የድርጊቶቻቸውን እና የውሳኔዎቻቸውን ዘላቂ ጦስ መተንተን አልቻለም፤ ቢችልም አድማጭ የለውም። ብዙዎቻችን መለስ ብለን ስናስታውሰው፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት እየታመስን የተንገረገብነው ብዙ ጊዜ ነው። አሁን ማን ይሙት፣ በ2014 ከጦር ሜዳ ሆነው እንዲያ ሲያብጠለጥሏቸው የነበሩት ጌታቸው ረዳ የመንግሥታቸው ሹመኛ እና ተከላካይ ይሆናሉ ብሎ ማን አሰበ? በርካታ የሕወሓት ሹመኞች የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ሊሆኑ ሲሻሙ እርሳቸው ግን ለምን ጌታቸውን መረጡ? ጌታቸው ላይ የሕወሓት አንጋፋ አባላት ሲያምፁ እርሳቸው ለምን ቀጥተኛ ጣልቃ ሳይገቡ ቀሩ? ምን አስበው ነበር? አሁንስ ምን እያሰቡ ነው?


የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ጀምረዋል። ለነዚህ የልማት ሥራዎች በርካታ መኖሪያ ቤቶች መፍረስ እና ነዋሪዎች እንዲነሱ ተደርጓል። ይህን ሲያደርጉ የሚያደርጉበት ፍጥነት እና ስፋት ሁሉም ሰው ከአቅሙ በላይ (overwhelming) ይሆንበት ነበር። የተፈናቃዮቹ ዕጣ ፈንታ ሳይወራ፣ አዲስ የሚመረቁት ሰፈሮች ይመጣሉ፤ በዚሀ መሐል ሌላ ሰፈር ይፈርሳል። በአንድ በኩል ብዛቱ፣ በሌላ በኩል ፍርሐቱ፣ በዚያ ላይ ፓርቲያቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሠማራቸው ካድሬዎች የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ! ሁሉም ይህንን በሚያህል ስፋት እና ጥልቀት የሚሠራ ሥራ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እና ጦስ ሳይተነን እንዲያልፍ እያደረጉ ነው። 


ዐቢይ አሕመድ ጠላቶቻቸውን ሲችሉ የእርሳቸው ተከላካይ ጠበቃ፣ አልያም አቅመ ቢስ ያደረጉበት መንገድ የማይታመን ነው። ኢሳትና ኦኤምኤን የተባሉ ቴሌቪዥኖች በአንድ ወቅት አገር አንቀጥቅጥ እንዳልነበሩ፣ ዛሬ ተከፋፍለው እና ተመናምነው የከሸፉበት ጥበብ አልተተነተነም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አጋር ፓርቲነት የተቀየሩበት መንገድ ከተራ በሹመት ማባበል በላይ መመርመር አለበት። ማኅበራዊ ሚዲያን ከተቃዋሚዎች መድረክነት ወደ ገዢው ፓርቲ ካድሬዎች መፈንጫነት የቀየሩበት መንገድም አልተስተዋለም። ምክንያቱም ይህን ሁሉ ለመመርመር ጊዜ አልሰጡንም። እንደ አስማተኛ ማስቀየሻ ሰበር ዜናዎች አሏቸው፤ ይኼን ብልጭልጭ አይተን ዞር ስንል ያኛው ሔዷል። 


“ሐሳብ አመንጪው” ጠቅላይ ሚኒስቴር


ባለሥልጣኖቻችን አዳዲስ የመንግሥት ሥራዎችን ሲያስተዋውቁ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት” ብለው ይጀምራሉ። እኔና አንድ ጓደኛዬ፣ የኢቢሲ የቴሌግራም ዜና ዘገባዎች ላይ ባደረግነው ቀላል ሐሰሳ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሐሳብ አመንጪነት” የሚለው 14 ዜናዎች  ውስጥ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ “አነሳሽነት” የሚለው ደግሞ 10 ዜናዎች ውስጥ ከነሐሴ 2012 ጀምሮ መጠቀሱን አስተውለናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐሳብ አመንጪነት የተጠቀሱት በብዛት ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ ቢሆንም፣ ከአረንጓዴ አሻራ፣ ከኢቢሲ እድሳት፣ ከክብረ በዓሎች ዝግጅት፣ ከተቋማት መመሥረት፣ እና ከስታዲየም ግንባታዎች ዕቅድ ጋር በተያያዘ ተወድሰዋል። 


እርግጥ ነው ብዙ ከከተማ ማስዋብ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዙት ሥራዎች በእርሳቸው ፍላጎት ባይሆን አይሠሩም፣ ቢሠሩም አሁን በሚሠሩበት ፍጥነትና ስፋት አይከናወኑም ነበር። የሹማምንቱና የዘገባዎቹ አጠቃቀም ግን ዕውቅና ከመስጠትም በላይ ሰበብ እየፈለጉ የማወደስ ዓይነት ይመስላል፤ እንደሚመስለኝ የሹመት መንገዱ ታማኝነትን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማረጋገጥ ነው። ሹማምንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሳይጠቅሱ መናገር 'ክሬዲቱን’ እንደመውሰድ እንዳይቆጠርባቸው ሰግተው፣ አልያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም ሥራዎች እና አፈፃፀሞች ላይ ካልተጠቀሱ ቅር ይላቸዋል በሚል ፍራቻ (ወይም ቅር እንደሚላቸው ከዚህ ቀደም ስላስተዋሉ) ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ አገሩ ውስጥ ሰው የሌለ ይመስል ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ለአንድ ሰው መስጠት አሳሳቢ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውነትም ዜናዎቹ እና ሹማምንቱ እንደሚሉት የሁሉም ነገሮች ሐሳብ አመንጪ ከሆኑም አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም ተደጋግሞ እንደተባለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራችንን በራሳቸው አምሳል መልሰው እየሠሯት ነው። እውነታቸውን ካልሆነና እየሸነገሏቸውም ከሆነ ያው ለራሳቸውም ቢሆን አደገኛ ነው።


ለንፅፅር እንዲረዳን፣ ትራምፕ የካቢኔ አባሎቻቸውን ሰብስበው ምስጋና ሲቀበሉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች አሉ። ይህ ለምን ሆነ ብዬ የተሰጡ ትንታኔዎችን ወዲያ ወዲህ እያልኩ ሳፈላልግ በርካታ መልሶች ተመለከትኩ። አንዳንዶቹ ታማኝነታቸውን ለማረጋገጥ ነው፣ ሌሎቹ ትራምፕ መወደስ እንደሚወዱ ስለሚያውቁ ሊያባብሏቸው ነው፣ ከፊሎቹ ትችት የበዛባቸውን የፕሬዚዳንቱን ሞራል ለመጠበቅ ነው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በተቀናቃኞቻቸው የተበላሸውን ገጽታቸውን ለመገንባት ነው የሚል ትንታኔ ሰጥተውበታል። የኛም ሹማምንት እነዚህን የ'ክሬዲት' ስጦታዎች የሚያዥጎደጉዱት ከነዚህ ምክንያቶች በተለየ ምክንያት ይሆናል ብዬ አልገምትም። ሆኖም፣ በአንድ ነገር መስማማት እንችላለን፤ እንዲህ ያለ የቁልምጫ እጅ መንሻ የሚጠብቀው አምባገነናዊ ማንነት ያለው የመንግሥት ሹመኛ ብቻ መሆኑን ነው። 


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በራሳቸው “ሐሳብ አመንጪነት” ኢትዮጵያን በራሳቸው ፍላጎት ልክ መልሰው ለመሥራት ቆርጠዋል ይባላል (የቶም ጋርድነር መጽሐፍም በዚሁ ዙሪያ ነው የሚያጠነጥነው)። ጦርነት እና ግጭት ቢፈነዳ፣ ትችት እና ማስፈራሪያ ቢዘንብ ማንንም የሚሰሙ አይመስሉም። የሚፈልጉትን ያደርጋሉ። “ታላቁ ትርክት” በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የጋራ ትርክት ለመፍጠር ትርክቱንም ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። አገራዊ ምክክሩን በመጠቀም እስከ ሕገ መንግሥት ክለሳ ለመድረስ ይሞክራሉም ተብሏል። መሐል አዲስ አበባን የዛሬ ስምንት ዓመት ያያት ሰው ዛሬ ገብቶ አይወጣባትም። የምኒልክ ቤተ መንግሥትን በከፊል ቀይረው ዩኒቲ ፓርክ ያሰኙት ሰሞን ለውጡ ከቢሮዬ ጀምሮ አገር ያዳርሳል ብለው ነበር። እንዳሉትም፣ በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ያሉት ሰፈሮች ሁሉ ተቀይረዋል። አዲስ ቤተ መንግሥትም ከተማዋ አናት ላይ እየተሠራ ነው። በየከተማዎቹ አዲስ አበባ የሚሠራው ዓይነት የመንገድ ዳርቻዎችን የማስጌጥ ሥራ እንዲባዛ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፣ እየተሠራም ነው (“የኮሪደር ልማት” የተሰኘው የከተሞች ዕድሳት ቢያንስ በ54 ከተሞች እንደተከናወነ ሰምቻለሁ፤ ወደ ገጠርም እየዘለቀ እንደሆነ የሚያሳዩ ጅምሮች በደቡብ ኢትዮጵያ አሉ)። በግለሰብ ባለቤትነት የሚተዳደሩ ሕንፃዎች ቀለም ላይ ሳይቀር፣ የግድግዳው እና መስታወቱ ዓይነት ላይ ጭምር መንግሥታቸው የራሱ ምርጫ አለው። 


የኮሪደር ልማቱ ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ደግሞ በግጭቶቹም፣ በኮቪድም፣ በዓለም ቀውስም፣ በፊስካል ፖሊሲ ለውጥም ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየፈተናት ነው። እርሳቸው ሥልጣን ላይ ሲወጡ ሃያ ምናምን ብር የነበረው አንድ ዶላር፣ ዛሬ በባንክ መቶ ሃምሳ ምናምን ገብቷል። የደሞዝተኛ ዜጎች ገቢ በአንድ ዓመት ውስጥ በግማሽ እንደቀነሰ ቁጠሩት። ስለዚህ የኮሪደር ልማቱ አስፈላጊ ቢሆን እንኳን “ኢትዮጵያ እነዚያን ሁሉ ነዋሪዎች የማፈናቀል፣ መልሶ የማቋቋም አቅም አላት ወይ? አዲሶቹ ግንባታዎች እና በተለይ ረብጣ ሀብት የሚፈስባቸው ባለመብራት የውሃ ፏፏቴዎች የሚጨምሩ መዝናኛ ሥፍራዎችን የመሥራት አቅም አላት ወይ? ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር ከከተሞች ርቀው የተሠሩት ቅንጡ ሪዞርቶች የሚያርፉባቸው ቱሪስቶች ይኖራሉ ወይ? የወጡባቸውን ወጪዎች ይመልሳሉ ወይ? ዘላቂ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ ወይ?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚያስቀይም አይሆንም።  ሆኖም፣ ቀድም ብዬ እንዳልኩት ዐቢይ አሕመድን ከመንገዳቸው ማንም፣ ምንም አያስቆማቸውም።


የጫካ ፕሮጀክት የሚባለውን ቤተ መንግሥት የሚጨምር “ሳተላይት ከተማ” በአዲስ አበባ  አንድ አናት ላይ ሲገነቡ፣ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚወስድ ተናግረዋል። የልማት ተነሺዎች ተበደልን ብለው ፍርድ ቤት መሔድ የሚችሉበት መንገድ ቀጭን ነው። ሕልማቸውን የሚያከናውኑት ከሕዝባቸው ጋር ተማክረው አይደለም። ለልጆቹ የሚበጀውን እንደሚያውቅ አባት የሕዝባቸውን ጫጫታ መስማት አይፈልጉም። ከዚህ በፊት ፓርላማው ገንዘብ ላልሰጠኝ የጫካ ፕሮጀክት ምንም ሊጠይቀኝ አይችልም እስከማለት ደርሰው ነበር። ጄኔራል ኦዲተሯ ባንድ ወቅት የነዚህ "ሜጋ" (ግዙፍ) ፕሮጀክቶች በጀት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ስላማያልፍ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የለንም ሲሉ ሰምቻለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚፈልጉትን የሚያሳኩት በእንዲህ ያለ ከሕግ የበላይነት ጭምር ነው።


ባለፉት ስምንት ዓመታት ያየነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዞ፣ የማይታመን ጥድፊያን ከማይታመን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ነውጥ ጋር አጣምሮ የያዘ ነው። ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን በራሳቸው ምስል እና ምናብ ልክ ለመቅረጽ ሲተጉ፣ የዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እና የሕግ የበላይነት ግን የዚሁ “ፈጣን ጉዞ” ሰለባ ሆነዋል። ዐቢይ ወደ ሥልጣን የወጡት በሰላማዊ ሒደት ቢሆንም፣ እንደ ቀደምት መሪዎች ሁሉ መሰንበቻቸው በነውጥ ሆኗል።  የነገዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም የሚወሰነው የተዋቡ የከተማ ኮሪደሮችና ወንዞች በዚህ በኩል፣ ጦርነትና የኑሮ ውድነት በወዲያ በኩል በሚያፈሩት ፍሬና በሚያስከትሉት ጦስ መካከል ነው። ስምንት ዓመታት አንድ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሁለት ጊዜ ተመርጦ አገልግሎቱን የሚያጠናቅቅበት ዘመን ነው። የእርሳቸው ሥልጣን ግን ገና እየጀመረ ይመስላል። ጥሩፋታቸውን ይኼ ነው ብሎ መተንበይ ይቸግራል። ነገር ግን በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ በሕግ የበላይነት፣ በዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር መልካም ሥም ጥለው ያልፋሉ ብሎ ለመገመት ምልክቱ የለም። የነውጦቹ መቋጫም ምን እንደሚሆን መገመት ነብይነት ይጠይቃል። ዐቢይ አሕመድ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “he has won the battles but not the war” (“ጦር ሜዳው ላይ ቀንቷቸዋል፤ ጦርነቱን ግን አላሸነፉም” እንደማለት።) 


መጪውን አብረን የምናየው ይሆናል፣ ነገር ግን ትልቁ ጥያቄ “ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዕቅድ ምንድን ነው?” የሚለው ሳይሆን፣ “ኢትዮጵያውያን ይህንን ሁሉ ነውጥ፣ የኢኮኖሚ ጫና እና ያልተገደበ ሥልጣን እስከመቼ ተሸክመው መዝለቅ ይችላሉ?” የሚለው ነው።

8 comments:

  1. መጪውን አብረን የምናየው ይሆናል፣ ነገር ግን ትልቁ ጥያቄ “ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዕቅድ ምንድን ነው?” የሚለው ሳይሆን፣ “ኢትዮጵያውያን ይህንን ሁሉ ነውጥ፣ የኢኮኖሚ ጫና እና ያልተገደበ ሥልጣን እስከመቼ ተሸክመው መዝለቅ ይችላሉ?” የሚለው ነው።
    This is the point !!!

    ReplyDelete
  2. ኢ መደበኛ ሃይል ብለው የመጀመሪያውን ቃታ የሳቡት እሳቸው አይደሉም ወይ? ሌላው ፅሁፍ ማለፊያ ነው። ፅሁፉ ያነጋግራል፣ ከራስ ህሊና ጋር ሙግት ያስገጥማል።

    ReplyDelete
  3. በየዓመቱ መጋቢትን ጠብቀህ መጻፍህ ለአንባቢያን በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው ምን አልባትም የብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እንደ በቀልተኛዎቹ ህወሓቶች ወደ ቃሊቲ እስር ቤት እንደጨመሩህ አላደረጉብህም (የተሻለ ነጻነት ሰላለ) ሆኖም ግን የየአውደ ዓመታቱ ጽሁፎችህ Smeared biography እየሆኑ እስከመቼ ይቀጥላሉ? የሚለው ጥያቄ እንደ ተደራሲ ያሳስበኛል ። በበቂ ሁኔታ ያልተተነተኑ በማህበራዊ ሚዲያ በየዕለቱ ተቃርኖ ያላቸው ሰዎች ከሚያነሱት የተለየ ካልሆነ scrolled ሆኖ ማለፉ አያጠራጥርም

    ReplyDelete
  4. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በሕገ መንግሥቱ የተመሰረተው በልዩነት አንድነት መርህ ላይ ነው። የፌዴራል አደረጃጀቱ ሁለት ታሪካዊ ግዴታዎችን ለማስታረቅ ሞክሯል፤ እነሱም የኢትዮጵያን መንግሥት መጠበቅ እና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተለያዩ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች እና የፖለቲካ መብቶች እውቅና መስጠት ናቸው። በንድፈ ሐሳብ ደረጃ፣ ይህ ሞዴል መንግሥትን ከሥልጣን መሣሪያ ወደ ድርድር አብሮ የመኖር ማዕቀፍ ለመቀየር ዘመናዊ ሙከራን ይወክላል። ሆኖም በተግባር ግን፣ ገዥው ፓርቲ ፌዴራሊዝምን በይፋ ሲያረጋግጥ፣ ከእውነተኛ ብሔረሰባዊ ዲሞክራሲ ይልቅ ከጃኮቢኒዝም ጋር የሚቀራረብ ርዕዮተ ዓለምን በድብቅ እንዳሳደገ የሚገልጽ ክርክር እየጨመረ መጥቷል።

    ጃኮቢኒዝም፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ ማዕከላዊነት፣ ወጥነት እና በመንግሥት የሚመራ ብሔራዊ ውህደትን የማያወላውል አስተምህሮ ያመለክታል። ልዩነት በፖለቲካዊ ሁኔታ የተደራጀ እና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መልኩ የሚያረጋግጥ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ልዩነትን በጥርጣሬ ያስተናግዳል። በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ጃኮቢኒዝም ሁልጊዜ በግልጽ መግለጫዎች ውስጥ አይታይም። ብዙውን ጊዜ በተዘዋዋሪ ይወጣል፡ በመሃል ላይ ባለው የሥልጣን ክምችት፣ በራስ ገዝ የክልል ተቋማት መዳከም፣ በማንነት ላይ በተመሰረቱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ የሚሰነዘረው የሞራል ጥርጣሬ እና ሕገ መንግሥታዊ ብዝሃነትን ለብሔራዊ አንድነት ስጋት አድርጎ እንደገና ለመግለጽ በተደጋጋሚ በሚደረገው ጥረት። ስለዚህ፣ ብሔራዊ ትስስር ተብሎ የሚታወጀው ነገር ብዙውን ጊዜ በተግባር የፌዴራል ልዩነትን መቆጣጠር ይሆናል።

    ይህ ቅራኔ በኢትዮጵያ የአሁኑ የፖለቲካ ውጥረት እምብርት ላይ ይገኛል። ሕገ መንግሥቱ ራስን መግዛት እና የጋራ አገዛዝን እንደ የፌዴሬሽኑ እኩል ምሰሶዎች አድርጎ ይቆጥረዋል። አንድነትን እንደ ልዩነት ማስወገድ ሳይሆን በሕግ፣ በስምምነት እና በጋራ እውቅና በኩል የልዩነት የፖለቲካ አስተዳደር አድርጎ ይቆጥረዋል። ይሁን እንጂ የጃኮቢን ግፊት ይህንን አመክንዮ ይለውጠዋል። መንግሥት መጀመሪያ አንድ የፖለቲካ ፍላጎት መፍጠር እና ከዚያም ብቻ በጥንቃቄ በተቆጣጠሩ ገደቦች ውስጥ ልዩነትን መታገስ እንዳለበት ያስባል። በእንደዚህ ዓይነት አካሄድ፣ ፌዴራሊዝም በቅጽ ይጠበቃል ነገር ግን በይዘት ተሸፍኗል። የክልል መንግሥታት በአስተዳደራዊ መልኩ የሚታዩ ሆነው ይቆያሉ፣ ነገር ግን በፖለቲካዊ ተገዢ ናቸው። ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በጽሑፍ ሳይበላሹ ይቀራሉ፣ ነገር ግን በማዕከላዊ ፓርቲ ዲሲፕሊን እና በፖለቲካ ምህንድስና በተግባር የተገደቡ ናቸው።

    በዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ውስጥ የተደበቀ የጃኮቢኒዝም አደጋ ጥልቅ ነው። ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናዎች ቅዱስ ከመሆናቸው ይልቅ ቅድመ ሁኔታ ያላቸው መሆናቸውን ስለሚያሳይ በተዋዋይ ቡድኖች መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል። ዴሞክራሲያዊ ውድድርን ያዳክማል፣ ምክንያቱም የፖለቲካ ህጋዊነት ከሕዝብ ስምምነት ጋር የተቆራኘው ለማዕከላዊ ፕሮጀክቱ ታማኝነት ሳይሆን ከሕዝብ ስምምነት ጋር ያነሰ ነው። እንዲሁም አለመረጋጋትን ያባብሳል፣ ምክንያቱም ነፃነታቸው እየተሸረሸረ ነው ብለው የሚያምኑ ማህበረሰቦች የፌዴራል መንግስትን እንደ የጋራ ቤት ሳይሆን እንደ ድብቅ ውህደት መድረክ አድርገው ይተረጉሙታል። በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች፣ ለእኩልነት፣ ለቋንቋ መብቶች፣ ለግዛት ታማኝነት እና ለክልል ራስን በራስ የማስተዳደር ህጋዊ ጥሪዎች እንኳን በቀላሉ እንደ ፓሮቺያሊዝም ወይም አክራሪነት ይወገዳሉ።

    አሳዛኙ ነገር ኢትዮጵያ ከመጠን በላይ ልዩነት አይሰቃይም፤ ማዕከላዊ ስልጣን ባላቸው ሰዎች የማያቋርጥ የልዩነት ፍርሃት ይደርስባታል። የፌዴራል ሀሳቡ ይህንን ታሪካዊ ፍርሃት ልዩነትን ወደ ህገ መንግስታዊ ጥንካሬ በመቀየር ለመፍታት የታሰበ ነበር። ስለዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ወደ ጃኮቢን ልማዶች የሚደረግ ማንኛውም ድብቅ መመለስ የፖሊሲ መዛባት ብቻ አይደለም። ከፌዴሬሽኑ መስራች ቃል ኪዳን የፍልስፍና ማፈግፈግ ነው።

    ኢትዮጵያ እንደ ዴሞክራሲያዊ ብሔረሰብ አቀፍ መንግስት እንድትጸና ከፈለገች፣ ከማዕከላዊ ወጥነት ፈተናዎች ይልቅ ለሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳኗ ታማኝነትን መምረጥ አለባት። አንድነት እንደ ርዕዮተ ዓለም ተመሳሳይነት በሚተረጎምበት በልዩነት ውስጥ አንድነት ሊኖር አይችልም። ልዩነት ሲዘጋ ሳይሆን ልዩነት ሲታወቅ፣ ሲከበር እና በተቋማዊ መንገድ ሲጠበቅ ፌዴሬሽኑ የተረጋጋ ሆኖ ይቆያል። በዚህ መልኩ፣ የኢትዮጵያ እውነተኛ መከላከያ የሚገኘው በጃኮቢን ውህደት ላይ ሳይሆን በሕገ መንግሥታዊ ፌዴራሊዝም በሐቀኝነት ተግባራዊ በሆነ መልኩ ነው።

    ReplyDelete
  5. ለኢጎው ሲል ይህን ሁሉ መከራ አገሪቱ ላይ ያውደ አውሬ መጨረሻው ምን ይሆን?

    ReplyDelete
  6. ጠ/ሚሩ የራሳቸው የሆነ ህገ መንግስት የማርቀቅ ወይም ባለው ላይ ማሻሻያ የማድረግ እቅድ አላቸው።
    በተለይ ክልላዊ መንግስታትን አቅም አልባ ለማድረግ የፌደራል ስርዓቱን ያፈርሳሉ አልያም አዲስ የአስተዳደር መዋቅር ይቀርፃሉ። የሚገጥማቸው ተግዳሮት ግን ቀላል አይሆንም።
    ከፖለቲካው ቁርሾና የአማፂያን ትጥቅ ትግል መበራከት በመነሳት መጪው አምስት አመት ለፓርቲያቸውም ሆነ ለርሳቸው የፈተና ግዜ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

    ReplyDelete
  7. ጠ/ሚሩ የራሳቸው የሆነ ህገ መንግስት የማርቀቅ ወይም ባለው ላይ ማሻሻያ የማድረግ እቅድ አላቸው።
    በተለይ ክልላዊ መንግስታትን አቅም አልባ ለማድረግ የፌደራል ስርዓቱን ያፈርሳሉ አልያም አዲስ የአስተዳደር መዋቅር ይዘረጋሉ። የሚገጥማቸው ተግዳሮት ግን ቀላል አይሆንም።
    ከፖለቲካው ቁርሾና የአማፂያን ትጥቅ ትግል መበራከት በመነሳት መጪው አምስት አመት ለፓርቲያቸውም ሆነ ለርሳቸው የፈተና ግዜ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።

    ReplyDelete
  8. ለትንታኔ አስቸጋሪው ዐቢይ በሚለው ርዕስ ስር እንደ አንድ ተዓምረኛ አድርገህ ሰውየውን ያስቀመጥክበትን መንገድ አልስማማም። በእርግጥ የተነተንካቸው ሁኔታዎች የተከናወኑ ቢሆንም፥ አብይ ስኬታማ ሊሆን የቻለው አንተ እንዳልከው ሊጠኑ የሚገባቸው ተዓምረኛ ሁነው ሳይሆን፥ ከድርጊታቸው ሊያስቆማቸው የሚገቡት አካላት ማለትም ተቃዋሚ ሃይሎች እና የአገሪቱ ዜጎች ድክመት እና የጠላቴ ጠላት ወዳጄ በሚል ብሂል ድጋፍ ሰለሰጡት እንዲሁም በሰውየው ሊታሰብ ከሚገባው ባላይ ጨካኝነት ነው።
    ሌላውን ምክንያት በጹሁፍህ ላይ ገልጸኸዋል ሰውየው ራሱን ከህግ በላይ አድርጎ የሚያይ እና የፈለኩትን ሁሉ አሳካለሁ የሚል ከሆነ እና የሚታወቀንም የማይታወቀውን የአገሪቱን ሀብት መከለከያን ጨምሮ በእጁ ካደረገ በስሩ ያሉትም የመንግስት ስልጣን የያዙት ሃላፊነታቸውን ትተው ለሱ ካሸረገዱ እንዴት ነው የጠቀስካቸውን ነገሮች ሁሉ የማያሳካው? ለመጠቃለል ያህል ሰውየው አንተ ያልከውን ያህል ሊጠና የሚገባው ተዓምረኛ ሳይሆን ነገሮችን አንድ ተራ ደላላ የሚጠቀማቸውን ቴክኒኮች ተጠቅሞ የሚያደረግ ሲሁን የእኛ የዜጎች ደደብነት እና መከፋፈል ሃይ ባይ ሰይኖረው የፈለገውን እንዲያደርግ አስችሎታል። ሌላ የተለየ ተዓምር የለውም።

    ReplyDelete