Pages

Wednesday, August 1, 2018

የትግራይ ፖለቲካ እንደምን ወደዳር አገር ፖለቲካ ተገፋ?

የኢትዮጵያ ሥርወ መንግሥት መነሻ ማዕከሉ (core state የሚሉት) ሰሜን ላይ ነበር - አክሱም። ቀስ በቀስ ወደ ደቡብ እያፈገፈገ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ሸዋ ላይ ከትሞ እስከ ዛሬ ዘልቋል። 'የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ' በአሁኑ ቅርፅዋ የተሠራችው በ19ኛው ክፍለዘመን ማገባደጃ ነው። ከዛሬዪቱ ኢትዮጵያ በፊት የነበረችው 'ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ' ነች። ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የዓለማችን ጥንታዊ አገራት ሁሉ፣ ድንበር አልነበራትም - የተፅዕኖ አድማስ እንጂ።  የተፅዕኖ አድማሷ ደግሞ እንደ ጊዜው እና እንደ ነጋሹ አቅም ሲሰፋና ሲጠብ ነው የከረመው።

ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ የአማርኛ ተናጋሪዎች እና የትግርኛ ተናጋሪዎች በዋነኝነት የሚዘውሯት ነበረች። በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ ያለችው ኢትዮጵያ በሁለቱ ፉክክር እና ማመቻመች (compromise) ነበር የቆመችው። ዳግማዊ ምኒልክ ደቡቡን እና ምሥራቁን የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ አካል ባደረጉበት ወቅት ግን በቁጥር ከትግርኛ ተናጋሪዎቹ እና ከአማርኛ ተናጋሪዎቹ የሚበልጡ ኦሮሞዎች የአገረ መንግሥቱ አካል በመሆናቸው፥ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በፊት ከነበራቸው ተቀናቃኝነት የበለጠ ኃይል አግኝተዋል። ይህ ክስተት ኢትዮጵያን ሦስተኛ የሥልጣን ተፎካካሪ እንድታገኝ አድርጓታል። (ይህ ማለት ግን ከዚያ በፊት ኦሮሞዎች የአገረ መንግሥቱ አካል አልነበሩም ማለት አይደለም፤ ሸዋ ቀድሞውንም ቅይጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን 'ታላቁ የኦሮሞ ፍልሰት' የኦሮምኛ ተናጋሪዎች ሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ተቀላቅለዋል። ይህም የወሎና የጁ ኦሮሞ ፖለቲከኞችን አፍርቷል። በዘመን ወደኋላ በነጎድን ቁጥር ታሪኩ ይለዋወጣል፤ ስለዚህ ርቀን ባንሔድ ጥሩ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ዛሬን በሚጫኑ የቅርብ ጊዜ ታሪካዊ መቀናቀኖች ላይ ማተኮር ብቻ ነው። እንዲያውም ትግራይን ከተፎካካሪ ሕዝቦች የነጠሉ የታሪክ ኩነቶችን መለየት ነው።)

የኤርትራ (ባሕር ምላሸ) የጣልያን ቅኝ ግዛት መሆን የትግራዋዩን ቁጥር በግማሽ ቢቀንሰውም ትግራይ የመንግሥት መነሻ ማዕከል በመነበሯ ምክንያት የመሐል አገር የሥልጣን ፉክክሩ ውስጥ ተፅዕኖዋ ሳይቀንስ ከርሟል። በዳግማይ ምኒልክ ሰዐት ትልቁ ኃይል እና ሥልጣን ሸዋ ላይ ተከማችቶ የነበረ ቢሆንም፣ ትግራይ እና ደቡቡም በየአካባቢ ንጉሡ የተወሰነ ነጻነት ነበረው። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ቀኃሥ) ግዜ ግን የአካባቢ ነገሥታት ሁሉ ከስመው ማዕከላዊነት ሰፈነ። ቀኃሥ የሥልጣን መስህቡን ሁሉ አዲስ አበባ ላይ - በመዳፋቸው ሥር አኖሩት።

ደርግም የቀጠለበት ይህንኑ የቀኃሥ እጅግ የተማከለ መንግሥታዊ ስርዓት ነው። ኢሕአዴግ ሲመጣ ምንም እንኳን በፌዴራል ስርዓት የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን በሕግ (de jure) ለክልሎች ቢያከፋፍልም በተግባር (de facto) ትልቁ ሥልጣን ግን በማዕከላዊ መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር ነበር። የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በእጅ አዙር የሥልጣኑን ቁጥጥር ለኢሕአዴግ ፈላጭ ቆራጮቹ ትሕነግኦች (TPLFs) ስላጎናፀፈ መቐለን ከአራት ኪሎ ያላነሰ ባለ ሥልጣን አድርጓት ነበር።