Pages

Saturday, February 8, 2014

የሌለውን ልማት መካድ



ሰሞኑን በአዲስ ዘመን እና ኢዜአ ‹‹ጥናት›› ስም ገበያ ላይ ከወጡ አዲስ አባባሎች ውስጥ ‹‹ልማቱን መካድ›› የሚል ይገኝበታል፡፡ አባባሉ እንዲህ እንደዛሬው ጥናታዊ ዕውቅና አላገኘም ነበር እንጂ እንዲሁ በገደምዳሜው ግን ስሙ ይታወቅ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ እና ቲፎዞዎቹ ‹‹ተቃዋሚዎች ልማቱን ይክዳሉ›› ይላሉ፤ ልማቱ የኢሕአዴግ ትልቁ መንጠልጠያ ነው፡፡

ራሱን ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ መንግሥት ‹ሥልጣኑን ጠቅልዬ መያዝ የሚኖርብኝ እና ዴሞክራሲ ለመንፈግ የተገደድኩት ልማቱን ለማፋጠን ብዬ ነው› ይላል፡፡ አባባሉ ‹እኔ ሥልጣኑ ላይ ካልቆየሁ ልማት አይኖርም› የሚል ይመስላል፤ ሌሎች ልማት ማምጣት ስለማይችሉ ይሁን እነሱ ሥልጣን ላይ ከሌሉ አገሪቷ ላይ ሌላ ኃይል እንዳይመጣ ጦርነት ስለሚከፍቱ እኔንጃ - ልማቱ የሚጨናገፈው በምን እንደሆነ ተናግረው ግን አያውቁም፡፡ መቼም ልማት ማለት ግንባታ ሆኗል እና የግንባታ መሣሪያዎቹን እና መሥሪያ ቦታዎቹን ይዘው ከሥልጣን አይወርዱም ብለን እናስባለን፡፡
የበኩር ስህተት

የኢሕአዴግ እና የቲፎዞዎቹ የበኩር ስህተት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እና ልማትን እንደ አንድ ዓይነት ነገሮች መመልከታቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለዐሥር ዓመታት ያክል በተከታታይ አስመዝግቢያቸዋለሁ ለሚለውና ከሞላ ጎደል የዓለም ባንክ እና የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚያረጋግጡለት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በኢትዮጵያ መንግሥት አነባበብ ሁለት አሐዝ ይደርሳል፡፡ እርግጥ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው (GDP) አነስተኛ የሆኑ አገራት ሁለት አሐዝ የሚደርስ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስመዘግቡበት ዕድል ሰፊ ነው፤ በተረጋጋ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሒደት ውስጥ እስከሆኑ ድረስ፡፡ ችግሩ ይህንን የኢኮኖሚ ዕድገት ልማት ብለው የተረጎሙት ዕለት ነው የተጀመረው፡፡

ኢኮኖሚስቶች ኢኮኖሚያዊ ልማት ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሰፊው እንደሚለይ፤ ዕድገት የልማት አንድ የአካል ክፋይ እንጂ አቻ ስያሜ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ባለሙያዎቹ ልማትን በጥቅሉ ሲተረጉሙት ‹የሕዝቦች የኑሮ ደረጃ መሻሽል፣ ለራሳቸው ያላቸው ግምት/አመለካከት መጨመር፣ ከጭቆና እና ጥገኝነት ነጻ መውጣት እንዲሁም ለኑሮ የሚበጁ የተለያዩ አማራጮች› ማግኘትን› ይመለከታል ይላሉ፤ ልማት በዜጎች ላይ በሚታዩ ለውጦች ላይ ያተኩራል፡፡ በዕድገት ምዘና ግን ድምር የአገሪቱ ገቢ ከዓመት፣ ዓመት መጨመሩ ላይ ብቻ የሚያተኩር በመሆኑ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ባይኖርም፣ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ባይሻሻልም፣ ዜጎች ኢኮኖሚያዊም ይሁን ፖለቲካዊ ነጻነት ባይኖራቸውም በጥቂት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና በጥቂት የሀብታሞች የበለጠ መበልፀግ ላይ ብቻ የተመሠረተ የቁጥር መሻሻል ከታየ ዕድገት ሊባል ይችላል፡፡ (ንፅፅሩን የአንድን ሰው ተራ የዕድሜ እና የክብደት መጨመርን፤ ከሌሎች የሥነ-አዕምሮ፣ ምግባር፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ደረጃ ዕድገት ጋር እንደማነፃፀር  ነው - የመጀመሪያው ኢኮኖሚ፤ ሁለተኛው ልማት መሆኑ ነው፡፡)

ይህ የትርጉም ልዩነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንጂ ልማት አለመሆኑን ይናገራል፤ ስለዚህ ልማቱ ከመካዱ በፊት በቦታው መኖር ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ (ከዚህ ርዕስ ጋር የተገናኘ ሙግት እዚህ ዞን ዘጠኝ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ላይም ማግኘት ይችላሉ፡፡)

የኢትዮጵያ ተርታ

ኢትዮጵያ የምዕራባውያን ዋነኛ ዕርዳታ ተቀባይ አገር ውስጥ ናት፡፡ እንግሊዝ እርዳታ ከምትለግሳቸው አገራት ከፍተኛ መጠን ያለውን የምትቀበለው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ካናዳ ከሐይቲ እና አፍጋኒስታን ቀጥሎ በሦስተኝነት ደረጃ እጇን የምትዘረጋው ለኢትዮጵያ ነው፡፡ እርዳታ አያኮራም፤ ሆኖም እንደኛ አገር ላለው ቁስለኛ ኢኮኖሚ አንድ የአገር መሪ እርዳታ ማስገኘት መቻሉን እንደ ድል መቁጠር የተለመደ ነው፡፡ የእኛም መንግሥት በዚህ ኩራት ይሰማዋል፡፡

አሳፋሪው ነገር ግን የሚመጣው ብዙዎቹ ለጋሽ ሃገራት የሚለግሱን ከነማን ተርታ አሰልፈው እንደሆነ የተመለከትን ዕለት ነው፡፡ ልገሳዎቹ ባብዛኛው በጦርነት ከተጎዱ አገራት ተርታ ነው፡፡ እኛ የእርስ በርስ ጦርነታችንን ካቆምን ሀያ ዓመታት ቢያልፉንም ዛሬም በጦርነት ከተጎዱና በተፈጥሩ አደጋ ከተናጡ አገሮች ተርታ እርዳታ የሚመደብልን አገር ነን፡፡ ይህ በልማት ምን ያህል ወደኋላ እንደቀረን አመላካች መራር እውነት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አገራችን ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገሮች ተርታ ተሰለፈች ተብሎ ዝርዝሩ ሲታይ በኢኮኖሚያቸው ድቅቅ ካሉ አገራት ተርታ መሰለፏን ማየት የሚያስደስት ነገር አይደለም፤ የሚደሰኮርበትም አይሆንም፡፡ አንድ መቶ ብርን በሁለት እጥፍ ማሳደግ፣ አንድ መቶ ቢሊዮን ብርን በእጥፍ ከማሳደግ ይቀላል፡፡ የዕድገታችን ፐርሰንታይል ከፍ ብሎ መታየትም በዚህ ይገለፃል እንጂ የመንግሥታችንን በልማት መመንደግ የሚያረጋግጥ እውነታ አይደለም፡፡

ጠቅላላ ገቢያችን ከሕዝብ ብዛታችን አንፃር

ኢትዮጵያ በጠቅላላ የገቢ ዕድገቷ በዓለም 14ኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ፍጥነት እያደገ ያለው ጠቅላላ ገቢ ለሕዝብ ቁጥራችን ሲካፈል ዛሬም ውራ እንደሆንን ይነግረናል፡፡ በጠቅላላ ገቢ ለሕዝብ ቁጥር ምጣኔ ኢትዮጵያ በአይ.ኤም.ኤፍ. ደረጃ ላይ169ኛ ከ187 አገራት እና የዓለም ባንክም 169ኛ ከ180 አገራት አንፃር ተቀምጣለች፡፡ ያውም ይህ  ምጣኔ በሀብታሞች እና በድሆች መካከል ያለውን የገቢ ክፍተት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ ጠቅላላ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ተሻሽሎ እንደሆነ እና እንዳልሆነ የሚገመግመው የተባበሩት መንግሥታት ሰብኣዊ ልማት ኢንዴክስ ላይ ኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ዝቅ ብላ 173ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ ከልማት ራቅ ብለን እንደምንገኝ ብዙ እማኝ መጥራት አይጠበቅብንም፡፡

በዚያ ላይ ደግሞ በቅርቡ የኢኮኖሚስቱ ኢንተሊጀንስ ዩኒት እ.ኤ.አ. በ2014 ፈጣን ዕድገት ያስመዘግባሉ ብሎ ከገመታቸው ዐሥር አገራት ውስጥ ኤርትራ ሳትቀር 8 በመቶ እንደምታድግ (በ9ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ) ኢትዮጵያ ግን ዝርዝሩ ውስጥ መግባት አልቻለችም፡፡ ይህ ማለት የተጀመረው ዕድገትም፣ ልማት ደጃፍ ላይ ሳይደርስ ሊሸረሸር እንደሚችል እና መንግሥት የባለሙያዎቹን ምክር በመስማትና ሕዝባዊ ተሳታፊነትን በማሳደግ ለዘላቂ ልማት የሚያደርስ የኢኮኖሚ ግንባታ መስመር ማስመር እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን እየቆጠሩ ‹‹ልማት መካድ›› የሚል ባጅ መለጠፍ ‹‹ልማታዊ›› አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment