ሰዎችን ለማድነቅ የምንጠቀምበት ቃል
‹ወንድ› ወይም ‹ወንዳታ› በሆነበት ማኅበረሰባዊ አስተሳሰብ የምትደነቅ ሴት ማብቀል ይከብዳል፡፡ የምትደነቅ ሴት ብትበቅል እንኳ
የማኅበረሰቡ ውጤት ነው ማለት አይቻልም ባይ ነኝ፤ የግል ጥረቷ ውጤት ነው የምትሆነው!
ቋንቋ፣ አባባሎች እንዲሁም ተረትና ምሳሌዎች
ማኅበረሰቡ አባላቱን የሚያሳድግበትን (nurture የሚያደርግበትን) መንገድ ያሳብቃሉ፡፡ ያልዘራነውን አናጭድም፤ ስለዚህ አጋጣሚውን
ተጠቅመን ከቃላት አጠቃቀማችን ጀምሮ ራሳችንን መገምገም መጀመር ሊኖርብን ነው፡፡
- ሴት ሲበዛ ጎመን ጠነዛ
- ሴትና ዶሮ ዱር ከሄዱ ቤታቸውን ይክዳሉ
- ሴት ከወንድ፣ እህል ከሆድ
- ሴት ለቤት፣ ወፍጮ ለዱቄት
- ሴትና መሬት የማይችሉት የለም
- ሴት ማገዶ ሲቸግራት ምሰሶ ትነቅላለች
- ሴት በማጀት፣ ወንድ በችሎት
- ሴት በጳጳስ፣ ኳደሬ በንጉስ
- ሴት ብታውቅ፣ በወንድ ያልቅ
- ሴት ሲያፏጩላት፣ ያረሱላት ይመስላታል
- ሴት አማት የመረዘው፣ ኮሶ ያነዘዘው
- ሴት አግብተው ሴት ቢወልዱ፣ የት አለ ንግዱ
- ሴት ከጠላች፣ በቅሎ ከበላች አመል አወጣች
- ሴት ካልወለደች ቋንጣ አትጠብስም
- ሴት ያመነ ጉም የዘገነ
- ሴት ያመጣው ጠብ አይበርድም
- ሴት ይወዷል ማጀት ያንጎዳጉዷል
- ሴትና ቄስ ቀስ
- ሴትና በቅሎ እንደገሪዋ ነው
- ሴትና አህያ ዱላ ይወዳል
- ሴትና ድመት ወደ ሞቀበት
- ሴትና ድስት ወደ ማጀት
- ሴትና ዶሮ ሳያብድ አይውልም
- ሴትና ፈረስ እንደኩሬ ውሀ እያደር ማነስ
- ሴትና ፈረስ የሰጡትን ይቀምስ
- ነፍስ በፈጣሪዋ፣ ሴት ባሳዳሪዋ
- ወጭትና ሴት ሲከናነቡ ይሻላል
- ወንድ ልጅ ለፈረስ ሴት ልጅ ለበርኖስ
- የመንገድ ዳር እሸት ባል የሌላት ሴት
- ዝናብ ካልጣለ ሁሉ ቤት፣ እንግዳ ካልመጣ ሁሉ ሴት
ተረትና ምሳሌ፤ የእምነት-እውነት
ተረትና ምሳሌዎች እንደባሕላዊ እሴት ወይም
ብልሐት (wisdom) የተለመደ ነው፡፡ በሙግት ለመርታት ብዙ ተረት መቻል በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ተረትና ምሳሌዎች፣ ልክ
እንደሌሎቹ ሁሉ የተገነቡት በተጠራቀመ የማኅበረሰብ የእምነት-እውነታ
ላይ ነው፡፡ አሁን፣ አሁን ከከተማ እየተመናመኑ ቢሆንም በብዙኃኑ ገጠሬ እና ጥቂት በማይባሉ ከተሜዎችም ውስጥ ስር የሰደደ እምነት
የተጣለባቸው አፍራሽ ተረቶች ናቸው፡፡ ደግነቱ፣ ተረት በተጠራቀመ ዕውቀት ተረትም፣ በተረት ይተካል፡፡
ለተረትና ምሳሌዎቻችን ትንሽ ጥብቅና ለመቆም
ያክል፣ እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆኑም በሴቶች ዙሪያ ገንቢ የሆኑ ተረትና ምሳሌዎችም አሉን፡፡ እንደምሳሌ ‹‹ሴትና ጭስ መውጫ አያጣም››
የሚለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንኑ ይዘው ይመስለኛል ብዙዎች ‹‹ሴት አይደለሽ እንዴ መላ አምጪ እንጂ!›› የሚሉት፡፡ ተረትና
ምሳሌዎች በጊዜ ብዛት በሰዎች ልቦና ውስጥ የእምነት-እውነት
የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡
No comments:
Post a Comment