Pages

Thursday, November 8, 2012

የአዲስ አበባ ከተማ እና ምርጫዋ


አዲስ አበባ 125ኛ ዓመቷን እያከበረች ነው፡፡ በከተማይቱ ልደት ሰሞን እናትና አባቷ (በመናገሻ ከተማነት የቆረቆሯት አጤ ምኒልክ እና ስሟን ያወጡለት እቴጌ ጣይቱ) ስማቸው ሲነሳ አልሰማሁም፡፡ ይልቁንም ላለፉት 21 ዓመታት በፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ መሪነታቸው በእጅ አዙር የዘወሯት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ እና በየመንገዱ ዳር በቆሙ ‹ቢልቦርዶች› ላይ ከከተማይቱ የመሠረተ ልማት አውታሮች ፎቶ ፊት ለፊት በጉልህ በተቀመጡ ምስሎቻቸው ታጅቦ ታይቷል፡፡

የክብረ በዓሉን ክንውን እንዲያዘጋጅ የኢሕአዴግ ሰዎች የሚመሯቸው ዋልታ እና ፋና ጥምር-ድቅል የሆነው ዋፋ የማስታወቂያ ድርጅት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ ምናልባትም የዚሁ የፓርቲ ጥገኝነት ጉዳይ ይሆናል መለስን በግምባር ቀደምነት የከተማይቱን ቆርቋሪ አስዘንግቶ ያስጠቀሳቸው፡፡

ለነገሩ ይህን ጽሑፍ ለማሰናዳት ያነሳሳኝ የክብረ በዓሉን ዐብይ-ሰብ (figure) ለመሰየም አይደለም፡፡ ስለከተማይቱ እያነሳሁ ይህንን ያፈጠጠ ስህተት ሳልነቅስ ማለፍ ስላልሆነልኝ ነው፡፡ የጽሑፌ ርዕሰ ጉዳይ ሚያዝያ ወር ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ከሀገር አቀፍ ምርጫ በሁለት ዓመት እንዲዘገይ የሆነው፣ በምርጫ 97 ከአንድ ወንበር በስተቀር ሁሉንም የከተማዋን ምክር ቤት መቀመጫዎች አሸንፎ የነበረው ቅንጅት ምክር ቤቱ ለመግባት ባለመፍቀዱ  ማሟያ ምርጫ እስኪካሄድ በተፈጠረው መዘግየት ሳቢያ ነው፡፡

ሀገሪቱ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በላይ ባላየችባቸው ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ አዲስ አበባ አምስት ከንቲባዎችን ለማየት ታድላለች፡፡ አንዴ ግዜያዊ የባለአደራ ከንቲባ ስታስተናግድ ቀደም ብሎ ደግሞ ‹‹ተበለሻሸች›› ተብሎ - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በሚፈቅደው መሠረት - ምክር ቤቷ ፈርሶ በድጋሚ እንዲገነባ ተደርጎ ነበር፡፡ በነዚህ ጊዜያት ከተሠሩ ሕንፃዎች እና መንገዶች በተጨማሪ በተለይ ሕዝቡን ያማከለ ሥራ የሠሩት አርከበ ናቸው፡፡ አርከበ የኮንዶሚኒዬም ቤቶችን እና አርከበ ሱቆች ተብሎ በማኅበረሰቡ የተሰየሙላቸውን ጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ ቤቶች ያስጀመሩ ከንቲባ ናቸው፡፡

በዐሥር ክፍለከተሞችና ከ100 በላይ በሆኑ ቀበሌዎች (አሁን ወረዳዎች) የተከፋፈለችው አዲስ አበባ ከ5 እስከ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎች እየዋሉ እንደሚያድሩባት ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው ከ3 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ለምርጫ ብቁ የሆኑት ደግሞ 2.2 ሚሊዮን የሚጠጉት ብቻ ናቸው፡፡