ኢሕአዴግ ከ21
ዓመታት በኋላ በዴሞክራሲ ጎዳና ወደኋለ መመለሱን ለማረጋገጥ ጥናት አያስፈልገውም፡፡ ታሪክን ባጭሩ ‹‹መገረብ›› በቂ ነው፡፡ ሆኖም
ከሰሞኑ የተሰራች ትንሽዬ ቅኝትም የምንገርበውን የታሪኩን ወቅታዊ ደረጃ ውጤት ታረዳናለች፡፡
ኢሕአዴግ በትጥቅ
ትግል አምባገነኑን ደርግ ከገረሠሠ በኋላ የሽግግር መንግስት አቋቋመ፡፡ የሽግግር መንግስቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ በነፃ ሐሳብ የመግለፅ
መብትን እና ወዘተ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚደነግገውን ሕገ መንግስት ቀረፀ፡፡
በታሪካችን
ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫም (ከነእንከኑ) ተካሄደ፣ ተደገመ፡፡ በርካታ የግል ጋዜጦች ተከፈቱ፣ ብዙ ሰዎችም
ትንፋሽ ታፍኖ ከሚኖርበት የደርግ የኑሮ ዘዬ በከፊል በመላቀቅ ለመብታቸው ጥብቅና መቆም እና ሐሳባቸውን መግለፅ ጀመሩ፡፡ በዚህ
መሃል ሦስተኛው ብሔራዊ ምርጫ (97) መጣ፡፡ ያ ወቅት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ጫፍ (maximum peak) ላይ የደረሰበት
ወቅት ነበር፡፡
ምርጫ 97
መጨረሻው ብጥብጥ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ እያቆጠቆጠ የነበረው ሕዝባዊ ነፃነት እና ዴሞክራሲ ወደአፎቱ ተመለሰ፡፡ ኢሕአዴግም በኢትዮጵያ
ታሪክ በምርጫ ስልጣን በመልቀቅ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ዕድሉን በገዛ ፈቃዱ ገደለው፡፡ በርካታ አዋጆች የዴሞክራሲያችንን አቅም፣
የሕዝቡን ነፃነት እና እምነት አሽመደመዱት፡፡
ዛሬ መንግስት
ዴሞክራሲን እያሳደገ እንደሆነ ቢናገርም፡፡ እስካሁን ድረስ በሕገመንግስቱ የተቀመጡት መብቶች ባይፋቁም ተግባራዊነታቸው ግን ወደ
1983 ተመልሶ ‹በ› ጉብጠት (n-curve) ሰርቷል፡፡
ዴሞክራሲያዊ
ስርዓትን እና መንግስታዊ ቅቡልነትን በአዋጆች ቁጥር፣ በገዢ ፓርቲ አባሎች እና ደጋፊ ነን ባዮች ብዛት እና በምርጫ ውጤት
(99.6%) ለመገምገም መሞከር ወደተሳሳተ መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡
ባሳለፍነው
ሳምንት በይነመረብ (Internet) ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በመጠየቅ ስለዴሞክራሲያችን ወቅታዊ፣ ሕዝባዊ የቅቡልነት ደረጃ (legitimacy
level) ለመቃኘት አቅጄ ተነሳሁ፡፡ ቅኝቱን ለማካሄድ ያቀረብኩትን መጠይቅ የሚሞሉ ሰዎች ቁጥር መጠይቁን ለማስተዋወቅ የጻፍኩትን
ጦማር ካነበቡት ሰዎች ቁጥር እጅግ ያነሰ ነበር፡፡ ይህ አንዱ የዴሞክራሲያችን መክሸፍ (የፍርሃታችን መገለጫ) መሆኑን የተረዳሁት
ግን ጥቂት በግል የማውቃቸው ሰዎች ያልሞሉበትን ምክንያት ከነገሩኝ በኋላ ነው፡፡ የመንግስት የደህንነት ሰዎች የመለሱትን መልስ
በሆነ መንገድ ያውቁብናል የሚል ስጋት አላቸው፡፡
የሆነ ሆኖ
በሞሉት ሰዎች መልስ ላይ ተመስርቼ የደረስኩበት መደምደሚያ የሚከተለውን ይመስላል፤ (ሙሉ
ቅጂውን እዚህ ማግኘት ይቻላል፡፡)
በመጠይቁ ውስጥ የተካተቱት መሰረታዊ ጥያቄዎች በሙሉ ከ86 በመቶ በላይ አሉታዊ ምላሾች አሉዋቸው፡፡ አብዛኞቹ የቅኝቱ ተሳታፊዎች ዴሞክራሲ አለ ብለው አያምኑም፣ በመንግስት ምርጫ ይተካል ብለው አያምኑም፣ ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት በርግጥም ተረጋግጧል ብለው አያምኑም፣ የሕግ የበላይነት አለ ብለው አያምኑም፣ ዜጎች ሰብአዊ መብታቸው ያለ ዘር እና ፖለቲካዊ አድሎ ይጠበቅላቸዋል ብለው አያምኑም፣ ብዙሐኑ የሚመራበት አናሳው መብቱ የሚከበርበት ስርዓት አለ ብለው አያምኑም፡፡ሲቪል ማሕበረሰቡ ፖለቲካዊ ተስፋ የማያደርግበት ምክንያት፣ በብዙዎች እምነት የደህንነት ፍራቻ ነው፡፡ መንግስት በምርጫ ይተካል ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ጥቂቶች እንኳን እንደምክንያት የሚያስቀምጡት የተቃዋሚዎችን ድክመት እና የፖለቲካ ምህዳሩን መጥበብ እንጂ የገዢውን ፓርቲ ተፈላጊነት ወይም ጥንካሬ አይደለም፡፡በጥቅሉ ጥያቄዎቹ በሙሉ የሚያተኩሩት ስለዴሞክራሲያዊ መርሖቹ በሃገራችን አተገባበር ላይ የመላሾቹን እምነት ማግኘት ላይ ነው፡፡ በውጤቱም መደምደም የሚቻለው አብዛኛዎቹ መላሾች በኢሕዴግ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ ምንም ዓይነት እምነት እንደሌላቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በርግጥም ተተግብሯል እንዲባል ሕዝባዊ ቅቡልነት ያስፈልገዋል፤ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግን ይህ ዓይነቱ ሕዝባዊ ቅቡልነት የሌለው መሆኑን ከዚህ አጭር ቅኝት አጠቃሎ መረዳት ይቻላል፡፡
ኢሕአዴግ ከ21
ዓመታት በኋላ ለስልጣኑ ያለው ቀናኢነት የተጋነነ ደረጃ ላይ ደርሶ የገረሠሠውን አምባገነን ለመተካት እንደበቃ ምስክር መጥራት የማያሻን
ይህንን ስናይ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment