Pages

Friday, April 6, 2012

እስኪ እንጠያየቅ፤ አገራችን የት ነው? (መጠባበቂያ ካስፈለገ)


ከመቶ ዓመት በፊት፣ በሃገራችን ሸንጎዎች የሚካሔዱት በተጻፈ ሕግ ሳይሆን በዳኞቹ የብልሐት ፍርድ ነበር፡፡ በምኒልክ ዘመን በዳኝነት ጥበባቸው ስማቸው ደጋግሞ የሚነሱት ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ካልተሳሳትኩ - ከዳኝነት ባንዱ የሚከተለው የገጠማቸውም እርሳቸው ናቸው፤ አንድ ሕፃን ልጅ ‹የኔ ነው፣ የኔ ነው› በሚል የተካሰሱ ሁለት ሴቶች ፍርዳቸውን ሽተው ቀረቡ፡፡

ኃብተጊዮርጊስ በጣም ተጨንቀው፣ አውጥተው፣ አውርደው ውሳኔያቸውን አሳለፉ፡፡ “እንግዲህ ሁለታችሁም እናት ነኝ ብላችኋል፡፡ ሁለታችሁም እናት መሆናችሁን ምስክር አቅርባችሁ አረጋግጣችኋል፡፡ እኔም ሁለታችሁም እናት መሆናችሁን አምኛለሁ፡፡ ስለዚህ ልጁ ለሁለት ተሰንጥቆ እኩል፣ እኩል እንድትካፈሉት ፈርጃለሁ፤” ብለው ወሰኑ፡፡

ውሳኔው እንደተላለፈ፣ አንደኛዋ ሴት ብትስማማም ሌላኛዋ ግን “በቃ ይቅርብኝ፣ ልጄ አይደለም፤ ትውሰደው” አለች፡፡ ይሄን ጊዜ ኃብተጊዮርጊስ “ልጁን ለመካፈል የተስማማችውን ሴት እንድትቀጣ ፈርደው ሲያበቁ፣ በልጇ መጨከን አቅቷት ‹ልጄ አይደለም› ለማለት ለበቃችው ሴት የእናትነት መብቷን አጎናጽፈዋታል፡፡

ከመቶ ዓመት በኋላስ?
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የደቡብ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ስለእርሳቸው ሰሞኑን ብዙ ያነጋገረን ፍርደ-ገምድልነት ከማውራቴ በፊት ባለፈው ሰሞን ተወርቶ የከሰመውን ገመናቸውን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ኢሕአዴግ በታሪኩ ያስተማረን ነገር ቢኖር፣ ለፓርቲው ታማኝ እስከሆኑ ድረስ የማይስተሰረይ ሃጢያት ብሎ ነገር የለም፡፡ ራሱ ኢሕአዴግ በቅርቡ በመሃላ እንዳረጋገጠልን የመንግስት ሌቦች ከመብዛታቸው የተነሳ፣ የሃገሪቱ ዋነኛ ችግር ሙስና ሆኗል፡፡ (በርግጥ እንደዛም ሆኖ ድህነት ቀንሷል፤ እኔም ብሆን በዚህ እስማማለሁ - ሙስና እስካለ ድረስ ድሃ የነበሩ ባለስልጣናት ሃብታም መሆናቸው አይቀርም፡፡)

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የካቲት 2004 ላይ በተካሄደው የደኢሕዴን ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የሲዳማ ቡና ላኪዎች ማሕበር ባለአክሲዮን ናቸው፣ ሚሊዮን ብሮች መዝብረዋል የሚል ትችት ቀርቦባቸው÷ ‹ከተከሰስኩ ብቻዬን አይደለም ወ/ሮ አዜብ መስፍንም መከሰስ አለባት› ብለው ግምገማውን ረግጠው ወጥተዋል በሚል የተሰማውን የውስጥ አዋቂዎች ወሬ በርካታ ድረዓምባዎች ‹ነገሩ እንዴት ነው?› ብለውበታል፡፡ (ያኔ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ችግር ሙስና መሆኑን በይፋ ሊያውጅ አንድ ወር ይቀረው ነበር፡፡) ነገርዬው እላይ ቤት በማነካካቱ ነው መሰለኝ ፍርዱ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ተፈርዶባቸው የማያውቁት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በክልላቸው የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪ ሰዎች ላይ ለመፍረድ ግን እምብዛም የተቸገሩ አይመስልም፡፡

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በአንድ ወቅት ለethiopiafirst ድረዓምባ ስለብሔር ፌዴራሊዝም ጠቃሚነት ሲያብራሩ እንዲህ ብለው ነበር፡-

“በዚህች አገር ላይ የነበርን ዜጎች ሁለት ዓይነት ዜጎች ነበርን፡፡ አንደኛ፡- እኛ ገዢ ነን ብለው የሚያምኑ፤ የገዢ መደቦች ያሉባት፤ ሁለተኛ፡- በሃገራቸው፣ በመሬታቸው፣ በምድራቸው የማይኮሩ፤ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው ተቆጥረው የሚኖሩባት አገር ነች፡፡ ይሄ ሁኔታ ነው የተቀየረው አሁን፡፡…. ይህንን ይዘን ግን …በመከባበር፣ በመደጋገፍ፣ በእኩልነት መንፈስ አንዲት ታላቅ እና ጠንካራ ኢትዮጵያ መገንባት እንችላለን፡፡”

እርሳቸው ‹አንደኛ፤› ብለው የተናገሩትን ስሰማ ትዝ የሚለኝ ያለፈ ነገር አይደለም፡፡ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ እንደዘረኝነት አትቁጠሩብኝና ‹አሁን፣ በኢትዮጵያ የገዢው ፓርቲ መደብ (ብሔር) ማነው?› ብዬ ብጠይቃችሁ በእያንዳንዳችሁ አእምሮ ውስጥ የሚውጠነጠነው የተለያየ መልስ ነው የሚል ስጋት የሚያድርብኝ ይመስላችኋል? በፍፁም እንዳይመስላችሁ፤ ሁላችንም የምንረዳው ሐቅ አንድ ነው፡፡

ለመሆኑ እርሳቸው ራሳቸው ‹በመከባበር፣ በመደጋፍ፣ በእኩልነት መንፈስ› ትገነባለች የሚሉን ኢትዮጵያ “አንተ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆንክ በዚህ ክልል መኖር አትችልም፤” ብሎ ደብዳቤ በሚጽፍ ክልላዊ አስተዳደር እና የብሔር ፌዴራሊዝም ነው ብለው ያምናሉ? እርሳቸው ቢያምኑስ እኛ እንድናምናቸው ይፈልጋሉ?

ዛሬ የጉሬ ፌርዳ ሰዎች ናቸው በአስተዳደራቸው ቀጭን ትዕዛዝ ከቀያቸው በቋንቋቸው ጦስ የተሰናበቱት፡፡ ነገስ፤ ማነሽ ባለተራ?
------
ምንም እንኳን የፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ የዳኝነት ታሪክ ብዬ የተረኩላችሁን አንድ መጽሃፍ ላይ እንዳነበብኩት በመጨረሻ ባስታውስም:: ታሪኩ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ የጠቢቡ ሰለሞን ታሪክ ሆኖ ተገኝቷል::

1 comment:

  1. FYI-check this story, read it from no 17-28. you will see the true story Of ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ .http://www.wordproject.org/am/11/3.htm

    ReplyDelete